
ከ 7 ሰአት በፊት
የአፕል ምርቶች አምራች የሆነው ፎክስኮን አዲሱን የአይፎን ሞዴል ለመልቀቅ የሠራተኞች ቅጥር ማስታወቂያ ለጥፏል።
የዓለማችን ግዙፉ የአይፎን ማምረቻ በቻይናዋ ዤንግዡ በገነባው ፋብሪካ ለሚቀጠሩ ሠራተኞች ‘ቦነስ’ አዘጋጅቷል።
ፎክስኮን በሚቀጥሉት 90 ቀናት ለሠራተኞቹ እስከ 424 ዶላር የሚደርስ ድጎማ ለማበርከት ቃል ገብቷል።
ይህ 3 ሺህ የቻይና ዩዋን፤ በሰሞኑ የውጭ ምንዛሪ ሲሳለ ወደ 23 ሺህ ብር ገደማ ማለት ነው።
አልፎም ጓደኛ አሊያም የቤተሰብ አባል ጠቁመው የሚያስቀጥሩ ሠራተኞች ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል።
አይፎን 15 ከፊታችን ባለው መስከረም ለገበያ ይቀርባል የሚል ግምት አለ።
ዋና መቀመጫው ታይዋን የሆነው ይህ ግዙፍ ኩባንያ ‘አይፎን ሲቲ’ በተባለው ማምረቻው ላሉ ሠራተኞች ጥቅማጥቅም እያደለ ነው።
ቢቢሲ ከቻይናው የመልዕክት መላላኪያ ዊቻት አጮልቆ እንዳየው ዘመድ አዝማድ ጠቁመው በስኬት ያስቀጠሩ ሰዎች 500 ዩዋን ሽልማት ያገኛሉ።
- አፕል ከሳተላይት ጋር መገናኘት የሚያስችለውን አይፎን 14 ስልኩን ይፋ አደረገ8 መስከረም 2022
- በሰው አንጎል ውስጥ ‘ቺፕ’ የሚቀብረው የኢላን መስክ ኩባንያ በሰው ላይ ሙከራ ሊያደርግ ነው26 ግንቦት 2023
ነገር ግን አዲስ የሚቀጠሩ ሠራተኞች በፋብሪካው ቢያንስ ለአንድ ወር መሥራት አለባቸው።
ኩባንያው ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
ባለፈው ዓመት ዤንግዡ የሚገኘው ፋብሪካ ሠራተኞች በኮቪድ ዕገዳና በዝቅተኛ ክፍያ ተማርረው ተቃውሞ አሰምተው ነበር።
አንዳንድ ሠራተኞች የኮቪድ ዕገዳውን ጥሰው አጥር ዘለው ከፋብሪካው ሲወጡ ባለፈው ጥቅምት የተለቀቁ ምስሎች አስመልክተዋል።
የቻይና ባለሥልጣናት አይፎን ሲቲ መገኛ በሆነችው ዤንግዡ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥለው የአይፎን 14 ምርቶች መዘግየታቸው ይታወሳል።
አፕል የተሰኘው ግዙፉ የአሜሪካ ኩባንያ ወርሃ ኅዳር ባወጣው መግለጫ አይፎን 14 የዘገየው በዚህ ምክንያት መሆኑን ገልጧል።
ከዚህ በኋላ ነው ኩባንያ አዳዲስ ሠራተኞች ቀጥሮ የተሻለ ጥቅማጥቅም ሊሰጥ ቃል የገባው።
ነገር ግን እንደ ሠራተኛ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሥራ ውሉ “ቃል የተገቡትን ጥቅማጥቅሞች አይገልጥም።”
ሠራተኛው ጨምረው ያለምንም ምግብ ውሸባ ውስጥ እንዳሉ ይናገራሉ።
ለዚህ ምላሽ የሰጠው ፎክስኮን “በቴክኒካዊ ችግር ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው” ብሎ አዳዲስ ሠራተኞች ማስታወቂያ ላይ የተለጠፈውን ሁሉ እንደሚያገኙ ጠቅሷል።
የዤንግዡ አይፎን ፋብሪካ ከ200 ሺህ በላይ ሠራተኞች አሉት።