
ከ 7 ሰአት በፊት
በሰሜን ኮሶቮ በተቀሰቀሰ ግጭት የኔቶ ሰላም አስከባሪዎች ላይ ጉዳት ደረሰ።
ፖሊስና የኔቶ ሰላም አስከባሪ አባላት የሰርብ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ባደረጉት ጥረት ነው 25 ሰላም አስከባሪዎች ላይ ጉዳት የደረሰው።
የዚህ ግጭት መነሻ የሆነው በሰሜን ኮሶቮ በተደረገ የአካባቢ ምርጫ የአልባኒያ ብሔር ተወላጅ ከንቲባ ሆኖ መመረጡን ተከትሎ ነው።
በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰርቦች የሚኖሩ ሲሆን ይህንን ምርጫ አንሳተፍበትም በማለታቸው ምርጫው ተካሄዶ የአልባኒ ብሔር የሆኑት ከንቲባ እንዲመረጡ ሆነዋል።
ይሁንና በምርጫ የተሳተፈው ጠቅላላ ሕዝብ ከ4 በመቶ የሚበልጥ አይደለም።
ይህ የአልባኒያ ተወላጅ ከንቲባ ሆኖ መመረጥ ያስቆጣቸው ሰርቦች ከንቲባው ወደ ማዘጋጃ ቤት ቢሯቸው እንዳይገቡ ሲከላከሉ ነው ግጭት የተፈጠረው።
አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት የኮሶቮ ባለሥልጣናት በሰሜን ኮሶቮ ለተፈጠረው ክስተት ተጠያቂ ናቸው በሚል አውግዘዋቸዋል።
ኮሶቮ ከሰርቢያ ነጻነቷን በፈረንጆቹ 2008 ዓ/ም ያወጀች ሲሆን ሰርቢያ ግን የኮሶቮን ነጻነት አሁንም ድረስ ዕውቅና አትሰጠውም።
በኮሶቮ ከ90 በመቶ የሚበልጠው ሕዝብ የአልባኒያ ብሔር ያለው ነው። ይሁንና በሰሜን ኮሶቮ አብዛኛው ሕዝብ የሰርብ ብሔር ተወላጅ ነው።
ይህም በመሆኑ በሰሜን ኮሶቮ በሰርቦችና በአልባኒያዎች መካከል ለዓመታት የዘለቀ ፍጥጫ ይስተዋላል።
የኮሶቮ ነጻ አገር መሆን በአሜሪካና በአውሮጳ ዕውቅናን ያገኘ ሲሆን በሩሲያ የምትደገፈው ሰርቢያ ግን ለኮሶቮ ነጻነት በጭራሽ ዕውቅና ሰጥታ አታውቅም።
ለዚህም አንዱ ምክንያት በሰሜናዊ ኮሶቮ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ሰርቦች መሆናቸው ነው።
በትናንቱ ግጭት ከጣሊያንና ከሃንጋሪ የተውጣጡ ሰላም አስከባሪዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ኔቶ አስታውቋል።
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ 5 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
- ዶናት ጋጋሪው፣ የሎሚ ጭማቂ አዟሪው፣ ሰሊጥ ቸርቻሪው ጣይብ ኤርዶዋን ማን ናቸው?28 ግንቦት 2023
- ሰው ሲሞት በዘፈን እና በጭፈራ የሚሸኘው የደቡብ ኢትዮጵያው ማኅበረሰብከ 8 ሰአት በፊት
- የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርገውን ሕግ በፊርማቸው አጸደቁ29 ግንቦት 2023
ሰርቢያዎችን ይበልጥ ያስቆጣቸው የአልባኒያ ተወላጅ ከንቲባ ሆኖ መመረጡ ብቻ ሳይሆን የኮሶቮ ፖሊስ ለተቃውሞ የወጡ ሰርቦችን መስመር ለማስያዝ የሄደበት ርቀት ነው።
ፖሊስ ብረት ለበስ ተሽከርካሪ ጭምር ተጠቅሞ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ሲሞክር ታይቷል።
የኮሶቮ ጠቅላይ ሚኒስትር አልቢን ኩርቲ ግን ፖሊሶቹ በሕጋዊ መንገድ የተመረጠን ከንቲባ ነው የተከላከሉት ሲሉ የሰርቦችን ቁጣ ምክንያታዊ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
ይህ ካለፈው ዐርብ ጀምሮ የተከሰተው ቀውስ ሰኞ ተባብሶ ከፍተኛ ግጭት የታየው ዝፌካን ከተማ ሲሆን በሕዝብ ተመርጠዋል የተባሉት የአልቤኒያ ብሔር ተወላጅ ከንቲባ ወደ ማዘጋጃ ቤት ሊገቡ ሲሉ ሰርቦች ረብሻ ፈጥረዋል።
በዚህን ጊዜ የኮሶቮ ፖሊስ ከንቲባውን ለመከላከልና ሰርቦችን ለመበተን ሞክሮ አልተሳካለትም።
ይህን ተከትሎ የኔቶ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ጣልቃ በመግባት ፖሊስንና የሰርብ ተቃዋሚዎችን ለመገላገል ሲሞክሩ ታይተዋል።
የኮሶቮ ፖሊስ ተሽከርካሪዎቹ በእሳት እንደተያያዙበት ገልጾ አባላቱም ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።
ኔቶ ግጭቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ሁለቱም ወገኖች ሁኔታዎችን ከማባባስ እንዲቆጠቡ መክሯል።
ይህን ተከትሎ ሰርቢያ ወታደሮቿን ወደ ኮሶቮ ድንበር ማስጠጋቷ የለየለት የብሔር ግጭት እንዳይቀሰቀስ ስጋት አጭሯል።
የኮሶቮ ጠቅላላ ሕዝብ ብዛት 1.8 ሚሊዮን የሚጠጋ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የሰርብ ብሔር ተወላጆች ቁጥር ከ5 በመቶ አይበልጥም።
ይሁንና በሰሜን ኮሶቮ የሰርቦች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
የአልባኒያዎች ስጋት በኮሶቮ የሰርብ ብሔር ተወላጆች ሥልጣን መያዝ በኋላ ለሰርቢያ የሚያደላና የአገሪቷ ነጻነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መንግሥት ሊመሰረት ይችላል የሚል ነው።
ሰርቦች ሥልጣን ከያዙ ትእዛዝ የሚቀበሉት ከቤልግሬድ ነው ብለው አልባኒያዎች ይሰጋሉ።
የሰርቢያ መከላከያ ሚኒስትር ሚሎስ ቩቼቪክ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ቩቺክ ሠራዊት ወደ ኮሶቮ ድንበር እንዳስጠጋና ወታደሩ በተጠንቀቅ እንዲሆን አዘውኛል ብለዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊከን የኮሶቮ መንግሥት ኃይል መጠቀሙን ነቅፈዋል።
መንግሥታት የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ አካል በነበረው የባልካን አካባቢ የሚፈጠሩ የብሔር ግጭቶች ወደለየለት እልቂት እንዳያመሩ ስጋት አላቸው። ለዚህም ነው በነዚህ አካባቢዎች የሚፈጠሩ መጠነኛ ግጭቶች እንኳ ከፍተኛ ትኩረት የሚያገኙት።
የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በፈረንጆቹ በ1990ዎቹ ስትፈራርስ ሰርቢያ በኮሶቮ ተገንጣዮች ላይ በተለይም በአልባኒያ ብሔር ተወላጆች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍታ ነበር።
ይህ አስፈሪ እልቂት በወቅቱ ሊቆም የቻለው ኔቶ በጊዜው ጣልቃ በመግባቱ ነበር።ኔቶ በተመረጡ የሰርብ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት አድርሶ ነበር ወደተራዘመ ድርድር የተገባው።
አካባቢው እስከ ፈረንጆቹ 2008 ድረስ በተባበሩት መንግሥታት ሥር ነበር የሚተዳደረው።
ኮሶቮ፣ በሰሜን በኩል ከሰርቢያ በደቡብ ደግሞ ከአልባኒያና ሰሜን መቄዶኒያ በምሥራቅ ደግሞ ከቡልጋሪያ እንዲሁም በምዕራብ ከሞንቴኔግሮ ትዋሰናለች።