እስራኤል የኢትዮጵያውያን አይሁዶችን ችግር የሚፈታ ከፍተኛ ኮሚቴ ማቋቋሟ ተገለጸ
(አዲስ ማለዳ) እስራኤል ከኢትዮጵያ የሄዱ ቤተ እስራኤላውያንን ችግር የሚከታተል እና ምላሽ የሚያሰጥ በሚኒስትር ደረጃ የሚመራ ኮሚቴ ማቋቋሟ ተገለጸ፡፡
የኮሚቴውን መቋቋም ባሳለፍነው እሁድ በነበረው ሳምንታዊ የካቢኔ ስብሰባ ላይ ይፋ ያደረጉት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትንያሁ፤ ‹‹ከኢትዮጵያ የመጡ እህት ወንድሞቻችን ችግር እንዲፈታ የተቋቋመው ኮሚቴ ከሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም እግዛ ያገኛል፡፡›› ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
አክለውም፤ ‹‹ብዙ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ሆኖም ኮሚቴው ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ያሉባቸውን ችግሮች በሂደቱ እንዲፈቱ ይሠራል፡፡›› ነው ያሉት፡፡
በቅርቡ በእስራኤል የሚኖሩ ቤተእስራኤላውያን የአገሪቱ መንግሥት ኢትዮጵያ የቀሩ ቤተሰቦቻቸውን ለማምጣት በጀት እንዲመድብ እና ሌሎች የሚያነሷቸውንም ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ በአደባባይ የተቃውሞ ሰልፍ አሰምተዋል፡፡
በዚህ ወር ውስጥም ከኢትዮጵያ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ሲሞክሩ በመንገድ ላይ ሕይወታቸውን ላጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራኤላውያን፣ በእየሩሳሌም የመታሰቢያ ዝግጅት የተካሄደ ሲሆን፤ በርከት ያሉ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዝግጅቱን ታድመዋል ተብሏል፡፡
ከ4 ሺሕ ያላነሱ ቤተ እስራኤላውያን ከ1970 እስከ 80ዎቹ ባሉት ዓመታት ከኢትዮጵያ ተነስተው ሱዳን ውስጥ ወደተዘጋጀው የመቀበያ ጣቢያ በእግር ለመግባት ሲሞክሩ በምግብ እጥረት እና በበሽታ መሞታቸውም ተጠቅሷል፡፡
90 ሺሕ ገደማ ቤተእስራኤላውያን በ1980 ወደ እስራኤል እንደገቡ እና በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላይ አገሪቱ ሕዝብ 2 በመቶ የሚሆኑ 160 ሺሕ ገዳማ ቤተ እስራኤላውያን መኖራቸው ተመላክቷል፡፡
ሆኖም እስራኤል በሚኖሩ አትዮጵያውያን አይሁዶች የዘረኝነት ጥቃት እንደሚደርስባቸው እና ሌሎች ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ አሰራሮች ሰለባ እንደሚሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡