
ከ 7 ሰአት በፊት
ሩሲያ በአሜሪካው ከፍተኛ የሪፐብሊካን ባለስልጣን ሊንድሴይ ግራሃም ላይ የእስር ትዕዛዝ አወጣች።
የምክር ቤት አባሉ የሩሲያ ወታደሮች በጦርነቱ መገደላቸውን አስመልክቶ ደስታቸውን ገልጸውበታል የተባለ አርትዖት የተደረገበትን ቪዲዮ ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት መውጣቱን ተከትሎ ነው ይህ የተሰማው።
ባለስልጣኑ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኪዬቨ ተገኝተው ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱን ተከትሎም የወጣው ይህ ቪዲዮ ሁለት የተለያዩ ክስተቶችን በአንድ ላይ ያጣመረ ሲሆን የተለቀቀውም በዩክሬን ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ነው።
ፖለቲከኛው አገራቸው ለዩክሬን ጦርነት የምታደርገውን እርዳታ “እስከ ዛሬ ካፈሰስነው ምርጥ ምክንያት” ነው ሲሉ ገልጸውታል።
የሩሲያ ወታደሮችም “እየሞቱ ነው” ሲሉም አክለዋል።
የምክር ቤት አባሉ የወጣባቸውን የእስር ትዕዛዝም እንደ “ክብር መለዮ” እንሚያጠልቁት ተናግረዋል።
“በዩክሬን ላይ ያለኝ ቁርጠኛ አቋም የፑቲንን አገዛዝ ስቦ ማስቆጣቱን ሳውቅ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ” ሲሉም ሩሲያ የእስር ትዕዛዝ ካወጣችባቸው በኋላ ፖለቲከኛው ሰኞ ዕለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
አክለውም “እያንዳንዱ የሩሲያ ወታደር ከዩክሬን ግዛት እስኪወጣ ድረስ ለዩክሬን ነጻነት እቆማለሁ” ብለዋል።
“በመጨረሻም የፑቲንን አገዛዝ የጦር ወንጀለኛ ብዬ በመጥራቴ ሊያስሩኝ እና ለፍርድ ሊያቆሙኝ ለሚፈልጉ ለሩሲያ ‘ወዳጆቼ’ ይኼው አለሁላችሁ። ይህንን ካደረጋችሁ ለአለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እጄን እሰጣለሁ” ሲሉም አክለዋል።
ሩሲያ ቪዲዮው በተለቀቀበት ወቅት የምክር ቤት አባሉን አስተያየት ተችታ ነበር።
የክሬምሊን ቃለ አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “እንዲህ ያሉ የምክር ቤት አባላት ለአገሪቱ ትልቅ ነውር ከማምጣት የባሰ ነገር አለ ብሎ ማሰብ ይከብዳል” ብለው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ዩክሬን ሙሉውን እና አርትዖት ያልተደረገበትን ቪዲዮም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለጥፋለች።
- ሰው ሲሞት በዘፈን እና በጭፈራ የሚሸኘው የደቡብ ኢትዮጵያው ማኅበረሰብከ 8 ሰአት በፊት
- ግዙፉ አይፎን አምራች ኩባንያ ለአዲሱ ‘ሞዴል’ ከመለቀቁ በፊት ሠራተኞቹን በጥቅማጥቅም እያንበሻበሸ ነውከ 8 ሰአት በፊት
- ከፑቲን ‘ምግብ አብሳይነት’ ተነስቶ በዩክሬኑ ጦርነት ውስጥ ቁልፍ ሰው የሆነው ግለሰብ26 ግንቦት 2023
ቪዲዮው እንደሚያሳየው የምክር ቤት አባሉ አስተያየቶቹን የሰጡት በሁለት የተለያዩ ስብሰባዎች ሲሆን በፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ቢሮ አርትዖት ተደርጎ ተጣምሮ በተከታታይ ይታያል።
በመጀመሪያው ቪዲዮ ላይ አሜሪካ ለዩክሬን ያደረገችው ዕርዳታ የሩሲያን ወታደራዊ ዘመቻ በመግታት የተሳካለት መሆኑን በመግለጽ “እስከ ዛሬ ካወጣንበት ምርጥ ምክንያት” በማለት አወድሰውታል።
በኋላም በተለዬና ከመጀመሪያው ጋር ግንኙነት የለውም በተባለው ቪዲዮ ዩክሬን የሩሲያን ጥቃት መቋቋም የምትችለው ለሦስት ቀናት ብቻ ነው ብለው ያምኑ እንደነበር አስታውሰው ይልቁንም “ሩሲያውን እየሞቱ ነው” ብለዋል።
አርትዖት ያልተደረገበት ቪዲዮ መውጣቱንም ተከትሎ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዩክሬን የምክር ቤት አባሉን ከትችት ለመከላከል እየሞከረች ነው ብለዋል።
ሊንድሴይ ግራሃምንም ንግግራቸው ከአውድ ውጭ ተወስዶም ከሆነ በይፋ እንዲናገሩ የሩሲያው ሚኒስትር ጠይቀዋቸዋል።
የምክር ቤት አባሉን በዋነኛ ተፈላጊዎች ዝርዝር ውስጥ ያስቀመጠው የሩሲያ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ፖለቲከኛው ምን አይነት ወንጀል እንደፈጸሙ አላተተም።
ነገር ግን ባለፈው ሳምንት የሞስኮ የፌደራል የምርመራ ኮሚቴ “በሩሲያውያን ግድያ ላይ የአሜሪካ ምክር ቤት አባሉ ትርክት” ላይ ምርመራ መጀመሩን አሳውቋል።
የምክር ቤት አባሉ በፓርቲያቸው ውስጥ በውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ጦረኛ አካሄድ አላቸው ከሚባሉት አንዱ ናቸው።
የደቡብ ካሮላይናው ሕግ አውጪ ለዩክሬን እርዳታ ልገሳን በተመለከተ ከፍተኛ ድጋፍ በመስጠት የሚታወቁ ሲሆን ሩሲያን “በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል” ሲከሷትም ይሰማሉ።