
ከ 7 ሰአት በፊት
ሩሲያ የዩክሬንን መዲና ኪዬቭን ለሦስተኛ ምሽት የአየር ጥቃቷ ኢላማ ካደረገች በኋላ በኪዬቭ ፍንዳታዎች የተሰሙ ሲሆን በርካታ ሕንጻዎችም በእሳት ተያይዘዋል።
ባለሥልጣናት እንዳሉት እሳቱ የተፈጠረው የዩክሬን የአየር መከላከያ ከ20 የሚበልጡ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ኢላማቸውን ሳይመቱ ከተጠለፉ በኋላ በወዳደቁ ስብርባሪዎች ምክንያት ነው።
በዚህም እስካሁን የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ ተዘግቧል።
ቀደም ባሉት ሁለት ምሽቶችም በኪዬቭ ላይ በተፈፀሙ ጥቃቶች ሁሉንም ሚሳይሎች እና ድሮኖችን መትቶ መጣሉን የዩክሬን አየር ኃይል አስታውቋል።
ሆኖም በሌሎች ክልሎች የአየር ኃይል ሰፈርን ጨምሮ የተወሰኑ አካባቢዎች ተመትተዋል።
ሰኞ ዕለት የምዕራብ ኸሜልንትስኪይ ግዛት ባለሥልጠናት እንደተናገሩት በወታደራዊ ሥፍራ አምስት አውሮፕላኖች ወድመዋል።
ባለሥልጣናቱ ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም የአየር ማረፊያው መንደርደሪያ አሁን ላይ ተጠግኗል ብለዋል።
ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ለዩክሬን የተለገሰውን አሜሪካ ሰራሹን የአየር መከላከያ አወድሰዋል።
ፕሬዚደንቱ ሰኞ ዕለት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት የአየር መቃወሚያዎቹ የሩሲያን ሚሳይሎች ሙሉ በሙሉ ተመትተው መውደቃቸውን አረጋግጠዋል ብለዋል።
“ ሩሲያ እስከመጨረሻው ማለትም እስከምትሸነፍ ድረስ የክፋትን መንገድ መከተል ትፈልጋለች። ምክንያቱም ክፋት ከሽንፈት ውጭ ሌላ መጨረሻ የለውም። ዓለም ይህ ሽብር እየጠፋ መሆኑን ማየት አለበት” ብለዋል ፕሬዚደንት ዘሌንስኪ።
የሩሲያ ጦር በበኩሉ በኪዬቭ እንዲሁም በሌሎች የዩክሬን ከተሞች ላይ በተፈፀመው ጥቃት ሁሉም የተፈለጉ ኢላማዎች መመታታቸውን ገልጿል።
ይሁን እንጂ ሁለቱም ወገኖች ያሉትን ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ማረጋጋጥ አልቻለም።
- ዩክሬን ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን መልሶ ማጥቃት ለመጀመር ዝግጁ ናት ተባለ27 ግንቦት 2023
- የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ሳይጠበቁ ኬንያ ገቡ29 ግንቦት 2023
- ዩክሬን ለወራት ስትዘጋጅ እና ስትታጠቅበት የቆየችው መልሶ ማጥቃት ምን ሊቀይር ይችላል?16 ግንቦት 2023
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን የጦር ደኅነንት ኃላፊ ጀኔራል ክርይሎ ቡዳኖቭ፣ ለሩሲያ ጥቃት ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጡ አስጠንቅቀዋል።
የኪዬቭ ጦር አስተዳደር በቅርብ የተፈፀሙ ጥቃቶችን ተከትሎ ከ20 በላይ ካሚካዜ ድሮኖች መውደማቸውን የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎችን በመጥቀስ ገልጿል።
የጦር አስተዳደሩ እንዳለው በደቡብ ሆሎሲቭስክይ አካባቢ በሕንጻ ላይ በተነሳ እሳት አንድ ሰው ሲገደል ሦስት ሰዎች ለጉዳት ተዳርገዋል።
“ የሕንጻው ከላይ ያሉ ወለሎች ወድመዋል። በዚህም ሰዎች በፍርሰራሽ ሥር ሊኖሩ ይችላሉ” ሲል የጦር አስተዳደሩ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በዳርንይስኪይ ዲስትሪክት ሁለት የግል ሕንጻዎች በእሳት የተያያዙ ሲሆን በርካታ መኪኖችም ወድመዋል።
የኪዬቭ ከንቲባ ቪታሊይ ክሊትሽኮ በቅርብ የተፈፀሙትን ጥቃቶች “መጠነ ሰፊ” ያሉት ሲሆን ነዋሪዎች ከመጠለያቸው እንዳይወጡ አሳስበዋል።

የሩሲያ የአየር ጥቃት ለጊዜው በመቆሙ ከሦስት ሰዓታት በኋላ የአየር ጥቃት ማንቂያው ደወል ተነስቷል።
ይህ ጥቃት ከግንቦት ወር ጀምሮ ሰኞ ቀን ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችን ጨምሮ በዋና መዲናዋ ኪዬቭ ላይ ለ17ኛ ጊዜ የተፈፀመ ነው።
ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ የፈፀመችው ሩሲያ ካሚካዜ ድሮኖችን እና ክሩስ እና ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን እየተጠቀመች ነው።
ሞስኮ ለረጅም ጊዜ ስትጠብቀው ከነበረው የአጸፋ ጥቃት ዘመቻ በፊት የዩክሬንን አየር መከላከያ ለማዳከም መጉዳት እንደምትፈልግ ተንታኞች ይናገራሉ።
ዩክሬን ለወራት የሚዘልቅ የአጸፋ ጥቃት ለመፈፀም እያቀደች ነው። ሆኖም ወታደሮችን ለማሰልጠን እና ከምዕራባውያን አጋሮቿም የጦር መሳሪያዎችንም ለማግኘትም ረዘም ያለ ጊዜ ወስዳለች።