የደቡብ አፍሪካና የሩሲያ መሪዎች

ከ 2 ሰአት በፊት

ደቡብ አፍሪካ በነሐሴ ወር ለምታዘገጀው የብሪክስ አገራት ጉባኤ ላይ ለሚገኙ የውጭ አገር ባለስልጣናት ዲፕሎማሲያዊ ያለመከሰስ መብት አወጀች።

ይህም በጉባኤው ላይ እንደሚሳተፉ ለሚጠበቁት ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጉብኝት መንገድ ያመቻቻል ተብሏል።

የደቡብ አፍሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ሰኞ እለት በወጣው መመሪያ መሰረት ያለመከሰስ መብቱ በብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የሚሳተፉ ባለስልጣናትንም ይጨምራል ብለዋል።

ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን ያካተተው የብሪክስ ጉባኤ ከመጪው ሃሙስ እንደሚጀምርም ተገልጿል።

‘ዲፕሎማሲያዊ ያለመከሰስ መብቶች እና ልዩ መብቶች’ በሚል የታወጀው ይህ መመሪያ ያለመከሰስ መብቱ ለተባበሩት መንግሥታት ባለስልጣናት እና ባለሙያዎች፣ ለየትኛውም ልዩ ኤጀንሲ ወይም ድርጅት እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ በተጠራ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ወይም ስብሰባ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የማንኛውም አገር ተወካዮችን ያካትታል።

የአለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ የሆኑት ክሌይሰን ሞኒዬላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አዋጅ “የተለመደ” እና እንዲህ አይነት አዋጆች በደቡብ አፍሪካ ተመሳሳይ አለም አቀፍ ጉባኤ በተደረጉ ቁጥር እንደሚወጡ መናገራቸውን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

አዋጁ የወጣው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ባደረገችው ወረራ ተፈጽመዋል በተባሉ የጦር ወንጀሎች በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሚፈለጉትን ፕሬዚዳንት ፑቲን በዚህ ጉባኤ ላይ ይገኛሉ በሚለው ላይ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ውሳኔ እንዲሰጥ ጫና ከምዕራቡ ዓለም እየቀረበበት ባለው ወቅት ነው።

ደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የሮም ስምምነት ፈራሚ እንደመሆኗ መጠን የጦር ወንጀል ማዘዣውን ተግባራዊ በማድረግ ፕሬዚዳንት ፑቲንን በቁጥጥር ስር ታውላለች ተብሎ ይጠበቃል።

ሆኖም የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ሃይል ሰኞ እለት እንዳስታወቀው ፕሬዚዳንት ፑቲን በብሪክስ ጉባኤ ላይ ቢገኙ በቁጥጥር ስር ለማዋል ስልጣን ስለሌለው እንደማይያዙ አስታውቋል።

የመከላከያ ኃላፊው ሩድዛኒ ማፍዋኒዋ ለአይሲሲ የእስር ትዕዛዝ ዕውቅና ቢሰጡም ሰራዊቱ በአለም አቀፍ ህግ ማዕቀፍ ውስጥ እንደሚሰራ እና የዲፕሎማሲያዊ ያለመከሰስ መብቶችን እንደሚያከብር ተናግረዋል።