የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ
የምስሉ መግለጫ,የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

ከ 4 ሰአት በፊት

ከቀናት በፊት ከቻይና የተመለሱት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለይፋዊ ጉብኝት ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ላይ ወደ ሩሲያ ሞስኮ ማቅናታቸውን የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር አስታወቁ።

ሚኒስትሩ የማና ገብረ መስቀል በትዊተር ላይ እንደገለጹት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር ወደ ሩሲያ የተጓዙት በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግብዣ የአራት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ነው።

ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ እና የባህልእና ስፖርት ኮሚሽነር አምሳደር ዘመዱ ተክሌ አብረዋቸው ተጉዘዋል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ሳምንት በቻይና ለቀናት የቆየ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ወደ አገራቸው ከተመለሱ ከቀናት በኋላ ነው ወደ ሩሲያ ያመሩት።

ባለፉት ዓመታት በሩሲያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀረበውን ሩሲያን የሚያወግዝ የውሳኔ ሃሳብ ከተቃወሙት ጥቂት አገራት መካከል ኤርትራ አንዷ ናት።

ባለፈው ሳምንት 32ኛ የነጻነት በዓሏን ያከበረችው ኤርትራ ባለፉት ዓመታት ከምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት መልካም የሚባል አይደለም።

ምዕራባውያኑም በአካባቢው በሚከሰቱ ግጭቶች ውስጥ ኤርትራ ሚና አላት ከማለት በተጨማሪ በአገሪቱ ውስጥ በዜጎቿ ላይ ጭቆናን ትፈጽማለች በሚል ይወቅሷታል።

በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሠራዊቷን አሰማርታ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ፈጽማለች ተብላ በሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና በምዕራባውያን ስትወገዝ ቆይታለች።

በዚህም የተነሳ ኤርትራ ከምዕራባውያን ይልቅ ኤርትራ ከቻይና፣ ከሩሲያ እና ከአረብ አገራት ጋር ግንኙነቷን እያጠናከረች ትገኛለች።

ኤርትራ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከቻይና እና ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች ሲሆን፣ የፕሬዝዳንት ኢሳያስም ጉብኝት የዚህ ማሳያ ነው።

ፕሬዝዳንቱ በቻይና ካደረጉት እንዲሁም አሁን በሩሲያ ከሚያደርጉት ጉብኝት ቀደም ብሎ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኤርትራ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ነበር።

ከወራት በፊት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ እናዲሁም የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በኤርትራ ጉብኝት አድርገው ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።