
30 ግንቦት 2023
ከሳምንት በፊት ፀጋ በላቸው የተባለች ወጣትን የጠለፈው የፖሊስ አባል ለሽምግልና የሚልካቸውን ሽማግሌዎች የወጣቷ ቤተሰቦች እንዲቀበሉ እያስፈራራ መሆኑን ቤተሰቦች ገለጹ።
የፀጋ በላቸው ታላቅ እህት የሆነችው ነጻነት በላቸው በእህቷ ጠለፋ የሚጠረጠረው ግለሰብ ወደ ወንድሟ ደውሎ ሽማግሌ ተቀበሉ እያለ እያስፈራራ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግራለች።
ተጠልፋ የደረሰችበት ያልታወቀችው ፀጋ ቤተሰብ እንደሚሉት ልጃቸውን ጠልፎ በመወሰድ የተጠረጠረው ግለሰብ የፖሊስ አባል እና የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ የግል ጠባቂ ነው ይላሉ።
ፖሊስ በበኩሉ ጠለፋውን በተመለከተ አቤቱታ ከደረሰው ጀምሮ ክትትል እያደረገ እንደሚኝ ገልጾ፣ በጠለፋ ወንጀሉ የተጠረጠረው ግለሰብ ‘በዲሲፕሊን’ ጉድለት ከሥራ ከመገለሉ በፊት የፖሊስ አባል እና የሐዋሳ ከንቲባ አጃቢ ነበር ይላል።
“በሕይወት ማግኘት የምትፈልጉ ከሆነ ‘እሺ’ በሉ”
ወጣቷን በመጥለፍ የተጠረጠረው ግለሰብ ወደ ፀጋ ታላቅ ወንድም ስልክ ደውሎ ቤተሰቧ እርሱ ያለውን “የማይፈጽም ከሆነ ሕይወቷን እንደሚያጠፋ” መዛቱን ነጻነት ለቢቢሲ ገልጻለች።
“ታላቅ ወንድሜ ጋር ደውሎ ‘እሷን በሕይወት ማግኘት የምትፈልጉ ከሆነ እኔ የምለውን እሺ ብላችሁ ተቀበሉ’ እያለ አስፈራርቷል” በማለት ትናገራለች።
ነጻነት እንደምትለው የፀጋ ቤተሰብ ጠላፊው የሚልካቸውን ሽማግሌዎች በመቀበል ጉዳዩን ከሕግ ይልቅ በባህላዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ እያስፈራራ ነው።
ግለሰቡ ለፀጋ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብም ፀጋ ግን ከሌላ ሰው ጋር ትዳር ለመመስረት በዝግጅት ላይ መሆኗን ነጻነት ትናገራለች።
“በቤተክርስቲያ የትዳር ትምህርት ተምራ ጨርሳለች። በቅርብ ጊዜ ውስጥም ከእጮኛዋ ጋር ትዳር ለመመሥረት በዝግጅት ላይ ነበረች።”
ነጻነት ታናሽ እህቷ ትውልድ እና እድገቷ ወልቂጤ ከተማ መሆኑን ገልጻ፤ በባንክ ተቀጥራ ኑሮዋን በሐዋሳ ካደረገች አንድ ዓመት አካባቢ ሆኗታል።
ነጻነት እህቷ የተጠለፈችው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ግንቦት 15/2015 ዓ.ም. ከሥራ ቦታ ወደ መኖሪያ ቤቷ እየቀናች በነበረበት ወቅት መሆኑን እና የእህቷን መጠለፈ ከአራዮቿ መስማቷን ትገልጻለች።
“ፀጋ ውጪ የማደር ልምድ የላትም። አከራዮቿ ቤት አለማደሯን ሲመለከቱ ወደምትሠራበት ቦታ ሄደው ሲያጧት እኛ ጋር ደወሉ። እኛም ጋር ምንም እንደሌለ ሲረዱ ለፖሊስ አመለከቱ” በማለት ትናግራለች።
“ከመጠለፏ በፊት ስጋት ነበራት”
ፀጋ ከመጠለፏ በፊት የምትፈራው የሚከታተላት ሰው እንዳለ ትናገራት እንደነበረ እህቷ በማስታወስ “ምንም አይነት ትውውቅ የላቸውም። በሩቅ ነው የምታየው። በተለያየ ስልክ እየደወለ፤ በአካል እየመጣ ማስቸገረ ከጀመረ አንድ ወር ያህል ቢሆነው ነው” በማለት ከግለሰቡ ጋር ትውውቅ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ገልጻለች።
“የእሷን መግቢያ እና መውጫ በተመለከተ መረጃ የምትሰጥ አብራት የምትሰራ ሴት መኖሯን ትነግረኝ ነበር። ይሄን መረጃ ለፖሊስ ከነገርኩ በኋላ ልጅቷን ለመያዝ ሄደው የልጅቷ ስልክ ላይ ፀጋ የወጣችበትን ሰዓት የነገረችበትን እንዲሁም እሱ እንደጠለፋት የሚያሳይ የጽሑፍ ልውውጥ አገኙ” በማለት ትናገራለች።
ፀጋ በግለሰቡ ክትትል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደነበረች የምትናገረው እህቷ ነጻነት፤ ስጋቷን ለፀጥታ አካላት ሪፖርት እንድታደርግ ብትመክራትም ሳታደርግ ቆይታለች።
ለዚህም ምክንያቷ የነበረው “የባለሥልጣን ጠባቂ ስለሆነ በፀባይ ብትይዢው ይሻልሻል” በሚል ምክር ስጋቷን ለፖሊስ ሪፖርት አለማድረጓን እህቷ ተናግራለች።
የቤተሰብ አባላቱም ቢሆኑ የፀጋን መጠለፈ ለፖሊስ ሪፖርት ቢያደርጉም በፀጥታ ኃይሎችን በቂ ትኩረት ሳያገኝ መቆየቱን ነጻነት ተናግራለች።
“አባቴ ታሞ ሆስፒታል ነው። እናታችን ደግሞ ልጄን አምጡ እያለች ጭንቅ ውስጥ ነን።…የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ጉዳይ አቤት እንዲልልን ነው የምንፈልገው።”
ጉዳዩን በተመለከተ ቢቢሲ የነጋገራቸው የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር መልካሙ አየለ ፖሊስ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ምርመራ እያካሄደ ነው ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ከፀጋ መሰወር ጋር በተያያዘ እስካሁን ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 6 ሰዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በፌስቡክ ገጹ ለጉዳዩ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ የተበዳይ ቤተሰብም ውጤቱን በትዕግሥት እንዲጠባበቅ ጠይቋል።