
ከ 4 ሰአት በፊት
የቀድሞ የሩሲያ ሰላይ ነው ተብሎ የተጠረጠረው አሳ ነባሪ (ዌል) በስዊድን የባህር ዳርቻ ላይ መታየቱን ቤሉጋ አሳነባሪን ለመከታተል የሚሰራው ድርጅት አስታወቀ።
በአካባቢው ‘ሃቫልድሚር’ የሚል ስም የተሰጠው ይህ አሳ ነባሪ፣ መጀመሪያ ላይ ሩሲያ ሰራሽ ቀበቶ ተጠልቆለት በኖርዌይ የባህርዳርቻ ላይ የታየው እንደ አውሮፓውያኑ 2019 ነበር።
ከኖርዌይ ሰሜናዊ ክፍል ወደ ደቡብ አቅጣጫ ቀስ እያለ በመጓዝ ዓመታትን አሳልፏል። ነገር ግን ከቅርብ ወራት ወዲህ አሳ ነባሪው ከኖርዌይ ውሃ ለመውጣት እንቅስቃሴውን ጨምሯል።
‘ዋንዌል’ የተባለው ድርጅት የአሳ ነባሪው ድንገተኛ ጥድፊያ ጀርባ ያለው ምክንያት ግልጽ አይደለም ብሏል።
አሳ ነባሪው መጀመሪያ ላይ ኢንጎያ ደሴት አቅራቢያ በሚገኙ የኖርዌይ ጀልባዎች የቀረበው ከአራት ዓመታት በፊት ነበር።
ደሴቱ ከሩሲያ ሰሜናዊ ወደብ ሙርማንስክ በ415 ኪሎ ሜትር ይርቃል።
በተገኘበት ወቅትም ለጎፐሮ ካሜራ ማንጠልጠያ የተገጠመለት ልብስ እንዲሁም ‘የሴንት ፕተርስበርግ መሣሪያ’ የሚል ጽሑፍ ያለበት ልብስ አጥልቆ ነበር።
የአሳ ነባሪው በዚህ መልኩ መገኘት የኖርዌይ የአገር ውስጥ የደኅንነት ተቋምን ምርመራ እንዲያካሂድ የመራው ሲሆን በኋላ ላይም አሳ ነባሪው በሩሲያ ጦር ሳይሰለጥን እንዳልቀረ ተቋሙ ለቢቢሲ ገልጿል።
ከዚያን ጊዜ በኋላ ነበር አሳ ነባሪው ‘ሃቫልዲሚር’ የሚል መጠሪያ የተሰጠው።
‘ሃቫል’ የሚለው ቃል በኖርዌጂያን አሳ ነባሪ ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ‘ዲሚር’ ደግሞ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ስም ተቆርጦ የተወሰደ ነው።
ሩሲያ እስካሁን ‘ሃቫልዲሚር’ የተባለው አሳ ነባሪ በሩሲያ ጦር የሰለጠነ ነው ስለመባሉ ያለችው ነገር የለም።
ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ የባህር እንስሳትን ለሰላይነት ማሰልጠንን የተመለከተ ምንም ዓይነት ፕሮግራም እንደሌላት ገልጻለች።
እንደ አውሮፓውያኑ 2019ም የሩሲያ ተጠባባቂ ኮሎኔል ቪክቶር ባራኔትስ “ ይህን እንስሳ ለስለላ የምንጠቀምበት ከሆነ ‘እባክዎ በዚህ ስልክ ቁጥር ይደውሉልን!’ ከሚል መልዕክት ጋር የስልክ ቁጥር የምናያይዝ አይመስላችሁም?” ሲሉ ተናግረዋል።
- በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሠፈራቸውን የመሠረቱ ኃያላን አገራት17 ግንቦት 2023
- የነዳጅ ዋጋን ከፍ-ዝቅ የሚያደርገው ኦፔክ ማን ነው? ለምንስ ምርት ይቀንሳል?5 ሚያዚያ 2023
- ሞባይል ስልኩ ዉሃ ውስጥ የሰመጠበት ሹመኛ ሙሉ የግድብ ዉሃ እንዲመጠጥ አስደረገ27 ግንቦት 2023
በዋንዌል ድርጅት የባህር ውስጥ ሕይወት ተመራማሪ ሰባስቲያን ስትራንድ፣ አሳ ነባሪው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካሳየው የእንቅስቃሴ ለውጥ ጀርባ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ ብለዋል።
“አሁን ላይ በተለይም ከተፈጥሯዊ አካባቢው ርቆ ለምን በፍጥነት እንደሚንቀሳቀስ አናውቅም።” ሲሉ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ተማራማሪው እንደሚሉት በባህርይው ላይ ካሳየው ለውጥ ጀርባ ሁለት ምክንያት ሊኖሩ የሚችሉ ነገሮች አሉ። “አንደኛው ከፍተኛ የሆርሞን መጠን ሲሆን ይህም ጓደኛ ለመፈለግ የሚገፋፋው ሲሆን ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ከብቸኝነት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ቤሉጋስ የተባሉት አሳ ነባሪዎች ማኅበራዊ እንስሳት በመሆናቸው ሌሎች ቤሉጋ አሳ ነባሪዎችን እየፈለገ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
ቤሉጋ አሳ ነባሪዎች በግሪንላንድ፣ በሩሲያ፣ በአላስካ እና በሰሜን ኖርዌይ አካባቢ በረዷማ በሆነው የአርክቲክ ውቅያኖስ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን የተወሰኑት በበጋ ወቅት ይሰደዳሉ።