አርተፊሻል ኢንተለጀንስ

ከ 4 ሰአት በፊት

በኦፕንኤአይ እና ዲፕማይንድ የተባሉ ስመ ጥር የቴክኖሎጂ ተቋማት መሪዎችን ጨምሮ በርካታ ባለሙያዎች ሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) የሰው ልጆችን ከምድር ሊያጠፋ ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ።

ባለሙያዎቹ ስጋታቸውን በመግለጽ ያወጡት ጽሑፍ በዘርፉ በተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች ድጋፍ ቢያገኝም ስጋቱ የተጋነነ ነው ያሉ ባለሙያዎችም አልጠፉም።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስጋትን እንደ ዓለም አቀፍ የበሽታ ወረርሽኝ እና የኑክሌር ጦርነት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላል ባለሙያዎቹ ያወጡት ጽሑፍ።

ቻትጂፒቲን የፈጠረው ኦፕንኤአይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳም አልትማን፣ የጉግል ዲፕማይንድ ዋና መሪ ዴሚስ ሃሳቢስ እንዲሁም የአንትሮፒክ አስተዳዳሪ ዳሪዮ አሞዴይ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስጋት ውስጥ ከትቶናል ካሉ ባለሙያዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ባለሙያዎቹ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሊያስከትል ይችላል ካሏቸው ችግሮች መካከል የቴክኖሎጂው ውጤቱ ሰዎችን ለመጉዳት ዲዛይን ሊደረግ ይችላል የሚል ነው። ለምሳሌ መድሃኒት ለማምረት የተፈበረኩ ቴክኖሎጂዎች የቼሚካል ጦር መሳሪያ ለመስራት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሊደረጉ ይችላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሐሰተኛ መረጃን በማሰራጨት በማኅበረሰብ ደረጃ ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል።

የባለሙያዎቹ ስጋት ይህም ብቻ አይደለም፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በጥቂቶች እጅ ቁጥጥር ሥር ገብቶ የአምባገነን መንግሥታት መጠቀሚያ ሊሆን ይችላል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ‘ፈጣሪ አባቶች’ የሚል ስም የተሰጣቸው ጂዮፌሪ ሂንተን (ዶ/ር) እና ፕሮፌሰር ዮሹዋ ቤንጊዮ ቴክኖሎጂው በሰው ልጆች ላይ አደጋ ሊሆን እንደሚችል በሚገልጸው ሰነድ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።

ይሁን እንጂ ለሜታ የሚሰሩት እና በዘርፉ ትልቅ ስም ያላቸው ፕሮፌሰር ያን ሊኩን የባለሙያዎቹ ስጋት የተጋነነ ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰሩ አርተፊሻል ኢንተለጀንስን በሰው ልጅ ላይ ያስከትላል የተባለው ‘የዓለም ፍጻሜ’ በርካታ የዘርፉን ባለሙያዎች አላሳመነም ይላሉ።

በፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንቲስት የሆኑት አርቪንድ ናራያናን ከፕሮፌሰር ያን ሊኩን ጋር ይስማማሉ።

ናራያናን ለቢቢሲ ሲናገሩ በአሁኑ ወቅት አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የደረሰበት የቴክኖሎጂ ውጤት የሰው ልጆችን ከምድር ለማጥፋት የሚያስችል አቅም ላይ አይደለም ይላሉ።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ኤሊዛቤት ሪነር ደግሞ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ሰዎችን ከምድር ላይ ሊያጠፋ ይችላል የሚል ስጋት ባይኖራቸውም የቴክኖሎጂ ውጤቱ አሁን ላይ እያሳየ ያለው ችግር ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ተናግረዋል።

ሐሰተኛ ወሬዎች የሚዛመቱበት ፍጥነት እና ብዛት ሊመጨመር እንደሚችል በመግለጽም ይህም የሕዝብ አመኔታን በማሳጣት እኩልነትን ያርቃል ብለዋል።