
ከ 6 ሰአት በፊት
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ውስጥ በሚገኘው ጉኖ ቀበሌ የሚገኘው የሻመና አካባቢ በሁሉም ወራት ለምለም ነው። ከዓመት ዓመት አረንጓዴ ነው።
የሻመና አብዛኛው ነዋሪ ገበሬ ነው። ከእርሻው ቀለቡን አዘጋጀቶ የተረፈውን ወደ ገበያ ይዞ ይወጣል።
የዚህ አካባቢ ነዋሪዎች ዋነኛ ችግር ግን መንገድ ነው። በተለይ በዝናብ ወራት መንገድ አይታሰብም።
ለነገሩ፣ መንገድ የሻመና ብቻ ሳይሆን የዳውሮ ዞን ነዋሪዎች ትልቁ ችግር ነው።
ከሰባት ዓመታት በፊት የተጀመረው እና ወላይታን ከዳውሮ ጋር ያገናኛል የተባለው የአስፓልት መንገድን ጨምሮ በዞኑ ከዓመታት በፊት የተጀመሩ ግንባታዎች ዛሬም አልተጠናቀቁም።
በጉኖ ቀበሌ የሚገኘው የሻመና አካባቢ ችግር ግን ይህ ብቻ አይደለም።
በአካባቢው በቅርብ ርቀት ትምህርት ቤት የለም። ህጻናት ትምህርት ለመከታተል ከቤታቸው ርቀው መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።
ርቀት ብቻ ሳይሆን፣ ህጻናቱ ከዚያ ለመድረስ በእነሱ ጉልበት የማይደፈር ፈታኝ መንገድ ይጠብቃቸዋል።
ወንዝ ማቋረጥ፣ በማይመቹ እና ገደላማ መንገዶች መጓዝ የግድ ይሆባቸዋል። ያ ደግሞ ለቤተሰብ ጭንቅ ነው።
ስለዚህም ያለው አማራጭ ቤት መዋል ብቻ ነው።
በዚህም ሳቢያ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ማግኘት የሚገባቸው በርካታ የጉኖ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት አይላኩም። ወይ ከፍ እስኪሉ ይጠበቃል፣ አሊያም ከትምህርት ጋር እስከ መጨረሻው ይቆራረጣሉ።
ነዋሪው ልጄ ቢማርልኝ ከሚል ቁጭት የዘለለ ምን ማድረግ ይችላል?
ይህ የነዋሪዎቹ ጭንቀት ያሳሰበው የቀበሌው ነዋሪ ባሹ በላይነህ፣ አንድ ነገር በማድረግ የበኩሉን መፍትሄ ለማበጀት ወሰነ።
- ትምህርት በተጀመረባት ትግራይ ጠፍጣፋ ድንጋይ በመጠቀም እያስተማሩ ያሉት መምህር12 ግንቦት 2023
- ባለ ብሩህ አእምሮ ወጣቶችን እያፈሩ ያሉት የኢትዮጵያ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች15 መጋቢት 2023
- በ200 ዩኒቨርስቲዎች ማመልከቻ ያስገባው ጥቁር አሜሪካዊ 9 ሚሊዮን ዶላር ለስኮላርሺፕ ቀረበለት27 ሚያዚያ 2023
መምህር እና ተማሪዎች
ባሹ እንደሌሎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ዋነኛ መተዳደሪያው እርሻ ነው።
ከዓመታት በፊት በሆሳዕና ከተማ በቅድመ መደበኛ መምህርነት ሠልጥኖ በ10 + 2 ተመርቋል።
በዚህ ‘ወረቀት’ ሥራ ለማግኘት ብዙ ተንከራቷል።
ዳውሮን ብቻ ሳይሆን በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች ላይ ሥራ ፍለጋ ኳትኗል። አልተሳካለትም።
በዚህ መሃል “በጎ ነገር ለመሥራት አሰብኩ” የሚለው ባሹ፣ በአካባቢው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ የተፈጠረውን ጉድለት ለመሙላት ብቻውን አንድ ነገር ለማድረግ ወሰነ።
ቀጣዩ ጉዳይ ቦታ ነው፤ ‘ትምህርት ቤት’ የሚሆን። ለዚህም ከቤተሰቦቹ ከወረሰው መሬት ቀንሶ በራሱ ወጪ ዳስ በመሥራት የመማሪያ ክፍል አዘጋጀ።
ባሹ ካለው 500 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ቀንሶ ከእንጨት እና ከሳር ለሠራው የመማሪያ ዳስ ተማሪዎች የሚቀመጡበት አግዳሚ ወንብሮችንም አዘጋጅቷል።
ጥቁር ሰሌዳ እና ጠመኔ ደግሞ በቀበሌው ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንደተበረከቱለት ተናግሯል።
ቀጣዩ ተግባር ተማሪዎችን ማግኘት ነው።

ባሹ ባለፈው መስከረም ወር በቻለው መጠን በሻመና የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን አንኳኳ። ወላጆቻቸውን በማናገር የትምህርትን ጥቅም አስረዳቸው።
የልጆቻቸው ከትምህርት ወደ ኋላ መቅረት ‘ምን ያህል ችግር ሊፈጥር እንደሚችል’ በማብራራት፣ ወላጆች እራሳቸው ፍላጎቱ ካላቸው ፊደል በመቁጠር እንደሚረዳቸው፣ እሱም የሚያውቀውን ለማካፈል ፈቃደኛ መሆኑን ገለጸላቸው።
ባሹ ዕቅዱን ለወላጆች አስረድቶ አብዛኞቹን ማሳመን ቻለ።
በዚህም ባለትዳሩ ባሹ ከአካባቢው ልጆች ጋር የራሱንም ሁለት ልጆች በመቀላቀል ማስተማር ጀመረ።
“[ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ] ብዙ ልጆች አሉ። አባቶችም እናቶችም መማር አልባቸው የሚለውን ሁሌ አስብ ነበር” የሚለው ባሹ በዚህ መንገድ 35 ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር ጀመረ።
ባሹ በአሁኑ ወቅት ከአራት ዓመት ህጻን እስከ አርባ ዓመት ጎልማሳ ተማሪዎች አሉት። አስራ ስምንቱ ደግሞ ሴት ናቸው።
መምህራቸው የሚሰጠው ትምህርት ከአካባቢው እውቀት የሚነሳ ነው።
ተማሪዎች የዳውሮ ቋንቋን ሥነ ጽሁፍ እንዲሁም እንግሊዝኛ እና በአካባቢው የሚዘወተሩ ቅርጻ ቅርጾችን ይማራሉ።

ከሰኞ እስከ አርብ ህጻናቱ የሚማሩ ሲሆን፣ ሰኞ እና ረቡዕ እስከ አራት ሰዓት ተምረው ሲለቀቁ፣ በእነዚህ ቀናት ከአራት ሰዓት በኋላ ጎልማሶች ወደ ባሹ ዳስ ገብተው ይማራሉ።
ጎልማሶቹን ቁጥሮችን መለየት እንዲሁም መደመር እና መቀነስ የሚያስተምራቸው ሲሆን፣ ይህ ለወጥ እያመጣ እንደሆነ ባሹ ይናገራል።
ህጻናቱ ከፊደል ጋር እየተዋወቁ ነው። ጎልማሶች መጻፍ እና ማንበብ እየሞከሩ ነው፤ ያለሰው እርዳታ ስልክ መደወል እና ባንክ ቤት በፊርማቸው መገልገል መጀመራቸውን ይገልጻል።
ይህ ውጤት ጎኖ ቀበሌ በሚገኝበት ገና ወረዳ ዕውቅና ተሰጥቶታል።
የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ወርቅነህ ነዋሪው በራሱ ተነሳሽነት አስደናቂ ተግባራት እየፈጸመ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ህጻናትን በገዛ ፍቃድ በራስ ይዞታ፣ በራስ ጉልበት እና ጊዜ ማስተማር የተለመደ ባይሆንም በእሱ ተጀምሯል” የሚሉት ኃላፊው “በመደበኛ ትምህርት ቤት ቅደመ መደበኛ ተማሪዎች የሚያገኙትን ትምህርት ሁሉ እያስተማረ ነው” ሲሉ አክለዋል።
ባሹ ትምህርቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተማሪዎች ላይ ለውጥ እየተመለከተ እንደሆነ ጠቅሷል።
“ህጻናቱ ፊደልን ቀስ በቀስ እያወቁ ነው” የሚለው መምህሩ፣ ይህ እጅግ ከፍ ያለ ደስታን እንደፈጠረለት ይናገራል።
ከተማሪዎቹ ወላጆችም ዘወትር ምርቃት እና አድናቆት እየቀረበለት ነው።
ጎልማሳ ተማሪዎቹ ደግሞ “‘ሞባይላችን ላይ ያለውን ከአንድ እስከ ዘጠኝ ቁጥር መለየት ችለናል። መደወል ችለናል’ ይሉኛል። ‘ባንክ ቤት ሄደን መፈረም ችለናል’ ይሉኛል። በዚህም እያመሰገኑኝ ነው።”
“ጥሩ ትምህርት አስተምሬ ወደፊት ለአገር የሚጠቅሙ ልጆች እንዲወጡ እፈልጋለሁ” የሚለው ወጣቱ መምህር የዳሱን ክፍል ከፍ አድርጎ፣ የተማሪዎችን ቁጥር ጨምሮ መቀጠል እንሚፈልግ ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።
ይህ ፍላጎቱ አሁን እውን ሆኗል።

‘የተሻሻለው’ የመማሪያ ክፍል
ባሹ ባለፉት ስምንት ወራት በብዙ ውጣ ውረድ በዳስ ውስጥ ተማሪዎችን ሲያስተምር የቆየበት ክፍል ቀን ወጥቶለታል።
ጥረቱን የተመለከቱ እና በንግድ የሚተዳደሩት አቶ ወልደጊዮርጊስ ይልቃል የተባሉ ግለሰብ ከአዲስ አበባ ከ700 በላይ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው የባሹን ትምህርት ቤት አሻሽለው አሰርተዋል።
በመሬቱ ላይ ሁለት የቆርቆሮ ክፍሎችና አንድ የአስተዳደር ቢሮ ሠርተው ከትምህርት ቁሳቁስ ጋር አስረክበዋል።
በተጨማሪም ለተማሪዎች የትምህርት መገልገያ የሚሆኑ መሳሪያዎችን ከመለገስ ባሻገር፣ ባሹ ለሚሰጠው የመምህርነት አገልግሎት የድርጅታቸው ቅጥረኛ ሆኖ ደሞዝ እንዲያገኝ አድርገዋል።
“[ባሹ] ከእርሻ ሥራ እና ሕይወቱን ከሚመራበት ጊዜ ቀንሶ ነው ልጆቹን እያስተማረ ያለው። በእኛ ድርጅት በኩል መንግሥት በሚከፍለው የደመወዝ ልኬት መሠረት በድርጅታችን በኩል ቋሚ ቅጥር ፈጽመንለታል” ሲሉ አቶ ወልደጊዮርጊስ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ባሹን ያናገረው ድጋፍ ሳያገኝ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በሚያገለግልበት ጊዜ ነበር። እናም ከዳስ ወደ ክፍል ተሸጋግሮ፣ ለጥረቱም ክፍያ ማግኘት ከጀመረ በኋላ ቢቢሲ መልሶ ባሹን አግኝቶታል።
“ትምህርት ቤቱ ከዳስ ወደ ቆርቆሮ በመቀየሩ የተሰማኝ ደስታ ወደር የለውም። ትምህርት ቤቱ በቆርቆሮ በመሥራቱ ተማሪዎችም ዘላቂ ትምህርት ያገኛሉ። እኔ በበጎነት ሥራውን ጀምሬ ሌላ በጎ አድራጊ አግኝቼ ትምህርት ቤቱ በመቀየሩ ደስ ብሎኛል” ብሏል።
ጨምሮም “ትምህርት ቤቱ ዳስ በነበረበት ጊዜ ጎርፍ፣ ነፋስ ወይም ዝናብ ያነሳብኛል ብዬ እሰጋ ነበር። አሁን ግን ያ ስጋት የለም።”

አቶ ወልደጊዮርጊስ የባሹን በጎ ተግባር የተመለከቱት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነው።
በበጎ ሥራው የተደነቁት ባለሃብቱ ባሹን አፈላልገው ካገኙት በኋላ “ሳይውሉ ሳያድሩ” ወደ አካባቢው እንዳቀኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ድርጅታችን ይህንን ያህል ትርፍ እያገኘ ያለበት ወቅት አይደለም፣ ገና በምሥረታ ደረጃ ላይ ነው ያለው” የሚሉት አቶ ወልደጊዮርጊስ የባሹን በጎ ተግባር ግን አይተው ማለፍ እንዳልመረጡ ጠቅሰዋል።
የመማሪያ ክፍሉን ከማሻሻል ባሻገር ለእያንዳንዱ ተማሪ የትምህርት ቁሳቁስ ተበርክቶላቸዋል።
ይህንን ሥራ ለመከናወን ወደ 162 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው ትምህርት ቤት እንዲኖር ፍላጎት የነበረው የሻመና አካባቢ ነዋሪ ትምህርት ቤቱ ሲገነባ ከፍተኛ ርብርብ አደርገዋል።
የመማሪያ ክፍሎቹን መሥራት ሲጀመር የአካባቢው ነዋሪ በሃሳብ እና በጉልበት ተረባርቦ በመሳተፉ ክፍሎቹ በ72 ሰዓታት ውስጥ ተሰርተው እንደተጠናቀቁ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ መስክረዋል።
ባሹ ትምህርት ቤቱ ዳግም በቆርቆሮ ሲሰራ መጀመሪያ ከነበረበት ቦታ በተጨማሪ በግምት እስከ 300 ካሬ ሜትር የእራሱን መሬት ፈቅዷል።
የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተሻሽሎ የተገነባው ትምህርት ቤቱ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት መስፈርቶችን ያሟላ እንደሆነ ገልጸዋል።
ወረዳው መጽሐፍትን እንደሚያቀርብ እና የተማሪዎች ቁጥር ሲጨምር ተጨማሪ መምህራንም ይቀጠራልም ብለዋል።
ኃላፊው ጨምረውም የአቶ ወልደጊዮርጊስ ተግባር “በጎነት ድንበር እንደሌለው ነው ያሳዩት…” በማለት ባለሃብቱ ለሌሎችም ምሳሌ ይሆናሉ ብለዋል።
የበጎ ፍቃደኛው ትምህርት ቤት በገና ወረዳ ያሉት እና በመደበኛ ትምህርት ቤት ውስጥ የተካተቱን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ወደ 29 ከፍ አድርጎታል።
በወረዳው በዚህ ዓመት 4 ሺህ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን፣ የባሹ ተማሪዎችም እዚህ ቁጥር ላይ ተጨምረዋል።
የባሹ ምኞት ግን ከዚህም የሚርቅ ነው።
“የተማሪዎቼን ቁጥር ከፍ አድርጌ፣ ሌላ ረዳት ከጎኔ አድርጌ ለማስተማር አስባለሁ። የተሻለ መምህር ሆኜ፣ ሰርተፍኬቴን ወደ ዲፕሎማ፣ ወደ ዲግሪ አሳድጌ ሕዝቤንም ህጻናትንም ማገልገል እፈልጋለሁ” ብሏል።
