
30 ግንቦት 2023
የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ከዛሬ ረቡዕ ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ እንደሚያደርጉ ተገለጸ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ልዩ መልዕክተኛው ከግንቦት 23 አስከ 29/2015 ዓ.ም. ድረስ በሚኖራቸው ቆይታ፣ በአገራት እና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ አስታውቋል።
አምባሳደር ማይክ ሐመር በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አሜሪካ ከሰየመቻቸው ልዩ መልዕክተኞች ሦስተኛው ናቸው።
ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል በተደረሰው ጦርነት የማቆም የሰላም ስምምነት ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ይነገራል።
አምባሳደር ሐመር በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመው እና ባለፈው ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የተፈረመውን ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ስምምነት አተገባበርን በተመለከተ በአዲስ አበባ እና በመቀለ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሏል።
- የህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን በትግራይ ምርጫ ‘በአስቸኳይ’ እንዲካሄድ ጠየቁ30 ግንቦት 2023
- ከቻይና የተመለሱት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ለጉብኝት ወደ ሩሲያ አቀኑ30 ግንቦት 2023
- ዝውውራቸው አይቀሬ የሚመስለው ራይስ፣ ቤሊንግሃም፣ ኬን፣ ኦሲምሄን እና ሜሲ ወዴት ያቀኑ ይሆን?30 ግንቦት 2023
ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሽግግር ፍትሕ እና የተጠያቂነት ጉዳይን እንዲሁም ትጥቅ ማስፈታትን፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋምን ጨምሮ የስምምነቱ አተገባበር ሂደትን እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች እንደሚያነሱ ተጠቅሷል።
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስቆም ስምምነት ከተደረሰ ስድስት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በርካታ የስምምነቱ ክፍሎች ተግባራዊ መደረጋቸው ይታወቃል።
አምባሳደር ሐመር ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአሜሪካ ከሚገኙ የተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባልት ጋር በወቅታዊው የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
አምባሳደሩ በጂቡቲ በሚኖራቸው ቆይታ ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ አፍሪካ ኮማንድ እና በአፍሪካ ቀንድ ጥምር ኃይል አዘጋጅነት በሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ፎረም ላይ እንደሚሳተፉ ተመልክቷል።
አምባሳደር ማይክ ሐመር በጂቡቲ ቆይታቸው ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መግለጫው አመልክቷል።
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅትን (ኢጋድ) የቅርብ ጊዜያት እንቅስቃሴዎችን ለመቃኘት ከተቋሙ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር እንደሚገናኙም ተመልክቷል።