
31 ግንቦት 2023, 16:51 EAT
በኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ ሕይወታቸውን ያጡ መንገደኞች አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት ተጓዦቹ ለደረሰባቸው መከራ እና ስቃይ የሚሆን ካሳ ቤተሰቦቻቸው ካሳ እንዲጠይቁ ተወሰነ።
አሜሪካዊው ዳኛ ግንቦት 22/ 2015 ዓ.ም መንገደኞቹ ለደረሰባቸው ስቃይ የተጎጂ ቤተሰቦች ቦይንግን ካሳ መጠየቅ ይችላሉ ሲሉም ብያኔያቸውን አስተላልፈዋል።
“መንገደኞቹ ወደ ሞት እያመሩ እንደሆነ ያውቁ እንደነበር በምክንያት መደምደም ይቻላል” በማለት የኢሊኖይ ዳኛ ጆርጅ አሎንስ ተናግረዋል።
ቦይንግ በበኩሉ መንገደኞቹ ስቃይ ሳይደርስባቸው ነው ወዲያውኑ በአደጋው ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡት በሚል ተከራክሯል።
በበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ተሳፍረው የነበሩ መንገደኞች አውሮፕላኑ ሊከሰከስ እንደሆነ ስለማወቃቸው “ምክንያታዊ ማስረጃ” አለ ሲሉም ዳኛው ውሳኔያቸውን አሳውቀዋል።
በዚህም ብያኔ መሠረት የተጎጂ ቤተሰቦች በቅድመ አደጋው ለደረሰው ሰቆቃ እና ስቃይ ቦይንግን ካሳ መጠየቅ ይችላሉ።
የተጎጂ ጠበቆች በበኩላቸው አደጋው ከመድረሱ በፊት የአውሮፕላኑ ሠራተኞችም ሆነ ተሳፋሪዎች ንቁ እንደነበሩ እና አውሮፕላኑ እየተከሰከሰ እንደሆነ ለማወቃቸው ምንም ክርክክር የለውም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
መጋቢት 01/2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ናይሮቢ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር አደጋው የደረሰው።
በዚህ አደጋ ከ35 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ የ157 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።
በ737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሱት የኢትዮጵያው አየር መንገድ እና የኢንዶኔዢያ ላየን ኤር አውሮፕላን አደጋዎችን ተከትሎ ቦይንግ የአብራሪዎቹን አቅም ጥያቄ በማስገባት እና ጥፋቱን ወደ ሌሎች አካላት በማዛወር ትችት ሲቀርብበት ነበር።
- ቦይንግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች ጋር ስምምነት ላይ ደረሰ11 ህዳር 2021
- ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ምክንያቱ የቦይንግ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ችግር መሆኑ ተገለጸ23 ታህሳስ 2022
- ቦይንግ ከኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ አውሮፕላን አደጋዎች ጋር በተያያዘ በማጭበርበር ክስ ለፍርድ ቀረበ 26 ጥር 2023
ከሁለት ዓመት በፊት የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ኃላፊነቱን እንደሚወስድ እና ተጠያቂነቱንም እንደሚቀበል ማስታወቁ ይታወሳል።
በምላሹም የተጎጂ ቤተሰቦች ኩባንያው ላደረሰው ጉዳት በፍርድ ቤት ቅጣት እንዲጣልበት ላለመጠየቅ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ባለፈው ዓመት በቴክሳስ የሚገኙ ዳኛ በቦይንግ 737 ማክስ አደጋዎች ሕይወታቸውን ያጡ 346 መንገደኞች በሕግ ዐይን “የወንጀል ሰለባዎች” መሆናቸውን ብያኔ ላይ መድረሳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
“የቦይንግ ወንጀል በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ አስከፊው የተቋም ወንጀል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል” ሲሉም በውሳኔያቸው ላይ መጻፋቸውን ይኸው ዘገባ አስነብቧል።
የአሜሪካ የፍትሕ ቢሮ ከአውሮፕላን አምራቹ ጋር ከሁለት ዓመት በፊት በተደረሰው ስምምነት ከ737 ማክስ ዲዛይን ጉድለት ጋር በተያያዘ በማጭበርበር ሴራ በወንጀል እንዳይከሰስ ከለላ ሰጥቶታል።
በምላሹም ቦይንግ ለአሜሪካ መንግሥት፣ አደጋ ለደረሰባቸው አየር መንገዶች እና ለተጎጂዎች የሚሆን 2.5 ቢሊዮን ዶላር የቅጣት ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።
ከአራት ዓመት ገደማ በፊት ለደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-ማክስ 8 አደጋ ምክንያት የቦይንግ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት (ኤምካስ) ችግር መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ከወራት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።
ለ157 ሰዎች ህልፈት የሆነው የበረራ ቁጥር ኢቲ 302ን አደጋ አስመልክቶ ሚኒስቴሩ ሲካሄድ የነበረው ምርመራ የማጠቃለያ ሪፖርቱን ታኅሣሥ 14/2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው ይህንን ያሳወቀው።
በሪፖርቱም መሠረት ለአውሮፕላኑ አደጋ ምክንያት ቦይንግ የገጠመው ኤምካስ (ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም” የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ችግር እንደሆነም ገልጿል።
ቦይንግ 737- ማክስ- 8 ለሁለት የአውሮፕላን አደጋዎች ምክንያት እና ለበርካታ ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑን ተከትሎ በዓለም ላይ ያሉ አውሮፕላኖቹ እንዳይበሩ እግድ መጣሉ ይታወሳል።
በቦይንግ አስፈላጊው ማስተካካያ ተደርጎ ተገቢው ምርመራ እና ሙከራ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ አውሮፕላኑ ወደ አገልግሎት መመለሱን ገልጿል።