
31 ግንቦት 2023
ከዚህ ቀደም የተደረሱ የተኩስ አቁም ስምምነቶችን በተደጋጋሚ ተጥሰዋል በሚል የሱዳን ጦር ከተኩስ አቁም ውይይቱ ራሱን ማግለሉ ተነገረ።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የተኩስ አቁም ስምምነቶችን በመጣስ የከሰሰው የሱዳን ጦር በሰላም ንግግሩ ተሳታፊ አንሆንም ማለታቸውን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በተደረሰው የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሆስፒታሎች እና ከመኖሪያ ህንጻዎች ለቀው እንዲወጡ የሚደነግግ ቢሆንም አንዱንም ተግባራዊ አላደረጉም ሲል ጦሩ ወቅሷል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱን በተደጋጋሚ በመጣሳቸው ጦሩ እዚህ ውሳኔ ላይ እንደደረሰም ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የመንግሥት ባለስልጣን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ሰብዓዊ እርዳታን ተደራሽ ያደርጋል ተብሎ ከነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ጦሩ ራሱን ማግለሉንም ሮይተርስ የሱዳን የዲፕሎማቲክ ምንጭን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በሱዳን ጦር መሪ መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል ጦርነቱ የተቀሰቀሰው ሚያዝያ 7/ 2015 ዓ.ም ነበር።
- በሱዳን ሆስፒታሎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ተጠቆመ27 ግንቦት 2023
- ለአንድ ወር የዘለቀው የሱዳን ጦርነት16 ግንቦት 2023
- በሱዳን የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ እየተፋለሙ ያሉት ሁለቱ ጄነራሎች18 ሚያዚያ 2023
የሚሊዮኖች ህይወት ስጋት ውስጥ በገባበት በዚህ ግጭት መሃል ሁለት ጄኔራሎች በባላንጣነት በጽንፍ ስፍራ ተቀምጠዋል።
የሱዳን ጦርም ሆነ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጦሩ ራሱን ስለማግለሉ በይፋ የሰጡት አስተያየት የለም።
ሁለቱን ተፋላሚ ኃይሎች እያሸማገሉ ያሉት አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ ሁለቱም ወገኖች የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ስምምነቱን በአምስት ቀናት ለማራዘም መስማማታቸውን ሰኞ ዕለት አስታውቀዋል።
ሆኖም ጦርነቱ የሱዳን መዲና ካርቱምን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ተፋፍሞ ቀጥሏል። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በካርቱም ያለው የጦር ሰፈሩ ጥቃት እንደደረሰበት አስታውቋል።
ጦሩ በበኩሉ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በኤልኦቤይ ከተማ ላይ ሊያደርስ የነበረውን ጥቃት ማክሸፉን ገልጿል።
አንድ ወር ባለፈው በሱዳን ጦርነት ቢያንስ 700 ሰዎች ተገድለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሱዳናውያን ተፈናቅለዋል።