
ከ 5 ሰአት በፊት
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብተ ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዋች የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በምዕራብ ትግራይ የዘር ማጽዳታ ወንጀል እየተፈጸመ ነው አለ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የሰላም ስምምነት ከፈረሙ በኋላ የአማራ ኃይሎች ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በተመተባበር የትግራይ ተወላጆች በኃይል ከምዕራብ ትግራይ እንዲለቁ እያደረጉ ነው ብሏል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጥቅምት 2013 ዓ.ም. ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአማራ ኃይሎች እና በአካባቢው የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ ተወላጆች ላይ የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል በመፈጸም የዘር ማጽዳት ፈጽመዋል ብሏል ቡድኑ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም በቅርቡ ባካሄደው ጥናት ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ድርጊት ተጠያቂ የተደረጉት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እና በላይ አያሌው የተባሉ ግለሰቦች አሁንም ከሕግ ውጭ በማሰር፣ በማሰቃየት እና የትግራይ ተወላጆችን በኃይል በማፈናቀል ተግባር መሰማራታቸውን አመልክቷል።
- የህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን በትግራይ ምርጫ ‘በአስቸኳይ’ እንዲካሄድ ጠየቁ30 ግንቦት 2023
- በትግራይ የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች እና የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች ጥያቄ23 ግንቦት 2023
- አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ ተጨማሪ ተቆጣጣሪዎች እንዲሰማሩ ጠየቀች3 ግንቦት 2023
የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ላቲሻ ባደር፤ “የጥቅምቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት የማቆም ስምምነት በምዕራብ ትግራይ ዞን የትግራይ ተወላጆችን የዘር ማጽዳት ማስቆም አልቻለም” ብለዋል።
ምክትል ዳይሬክተሯ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተጎጂዎች ፍትሕ የመስጠት እውነተኛ ቁርጠኝነት ካለው ጥቃት አድራሾቹን አስቁሞ ገለልተኛ መርማሪ ቡድን በአካባቢው ምርመራ እንዳያደርግ ክልከላውን ማቆም አለበት ብለዋል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ለዚህ ምርመራው ከመስከረም 2015 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ባሉት ወራት 35 የዐይን እማኞችን፣ ተጎጂዎችን እና የእርዳታ ሰጪ ድርጅት ሠራተኞችን ጨምሮ 35 ሰዎችን በስልክ አነጋግሯል።
በስልክ ቃላቸውን የሰጡ ሰዎች የአማራ ኃይሎች እና የአካባቢው አስተዳደሮች በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን በኃይል ከአካባቢው ከማፈናቃላቸው በፊት በሁመራ፣ ራዊያን እና አደባይ ከተሞች አስረው አቆይተዋቸው እንደነበረ ገልጸዋል።
የዐይን እማኞች እና ተጎጂዎች ሰዎች ይፋዊ ባልሆኑ ቦታዎች ጭምር ያለ በቂ ምግብ እና መድኃኒት ታስረው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
“የሕክምና አገልግሎት አልነበረም።…ሰዎች ከታመሙ፤ እስኪሞቱ ድረስ በዚያው እንዲቆዩ ይደረግ ነበር” ሲል በሁመራ ማረሚያ ቤት ታስሮ የነበረ የ28 ዓመት ወጣት ለመብት ተሟጋች ቡድኑ ተናግሯል።
ኅዳር 9 እና 10 የአማራ ኃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ከምዕራብ ትግራይ ወደ ማዕከላዊ ትግራይ ስለማዘዋወራቸው በሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ላይ ተመላክቷል።
እስካሁን ድረስ ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችን አሃዝ በትክክል ማወቅ ባይቻልም፣ እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም. ድረስ የተባበሩት መንግሥታት በብዛት ከምዕራብ ትግራይ ከተፈናቀሉት አብዛኛዎቹ 47 ሺህ ስደተኞችን መዝግቧል።
በእስር ላይ ያሉ ሰዎች ግድያ
በአማራ ኃይሎች ታስረው የነበሩ እና ከእስር ያመለጡ የዐይን እማኞች ቃላቸውን ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሲሰጡ ሰኔ ወር ላይ በሁመራ ማረሚያ ቤት ታስረው የነበሩ ቢያንስ 6 እስረኞች ተገድለዋል።
አንድ የዐይን እማኝ እስረኞች ከሁመራ ማረሚያ ቤት ካመለጡ በኋላ አንድ እስረኛ የተገደለበትን ሁኔታ ለሂዩማን ራይትስ ዋች ተናግሯል።
ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ የጣለውን ከፍተኛ ዝናብ ተገን በማድረግ 16 እስረኞች ማምለጣቸውን ተከትሎ፣ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት እና የፋኖ ታጣቂዎች ሊያመልጥ ይችላል ብለው የገመቱትን ‘ባምቢኒ’ ተብሎ በቅጽል ስሙ የሚታወቅ እስረኛ ለሌሎች ማስተማሪያ በሚል ገድለው አስክሬኑን ለእስረኞች ማሳየታቸውን የዐይን እማኙ ተናግሯል ብሏል የመብት ተሟጋቹ።
በሌላ አጋጣሚ በሁመር ማረሚያ ቤት ታስረው የነበሩ የ70 ዓመት አዛውንት የሆኑት ካላዩ ስዩም የተባሉ የቀድሞ መምህር እና ሳዕረ በሪሁ የተባለ ሌላ የሃይማኖት መሪ በድብድባ መገደላቸውን ተናግሯል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑት ፀጥታ ኃይሎችን እና ባለሥልጣናትን ከሥራ በማገድ ምርመራ አድርጎ እንደ አግባቡ በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ ጠይቋል።
ቡድኑ በዚህ አደገኛ የመብት ጥሰት ተጠያቂ የሚደረጉትን ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ ኮማንደር ደጀኔ ማሬ እና በላይ አያሌው የተባሉ ግለሰቦች ላይ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቋል።
የምዕራብ ትግራይ አካባቢ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በይገባኛል ከሚወዛገቡባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም. የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ኃይሎች ቁጥጥር ስር ገብቶ ወልቃይት ጠገዴ በሚል በክልሉ ስር ይገኛል።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነትን ተከትሎ የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራሉ መንግሥት የአማራ ኃይሎችን ከምዕራብ ትግራይ እና ከሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች እንዲያስወጣ እየጠየቀ ነው።
ለረጅም ጊዜ የቆየ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን ምዕራብ ትግራይን ጨምሮ ሌሎችንም አካባቢዎች የሚያስተዳድረው የአማራ ክልል መስተዳደርም ጥያቄው ሕጋዊ መፍትሔ እንዲሰጠው ሲጠይቅ ቆይቷል።
የፌደራል መንግሥቱም የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምላሽ እንደሚያገኙ እንደሚደረግ በተለያዩ ጊዜያት ገልጿል።