
ከ 42 ደቂቃዎች በፊት
ከትግራይ እስከ ሶሪያ፣ ከዩክሬን እስከ ሱዳን አሰቃቂ የጦር ወንጀሎች ይፈጸማሉ።
ሲፈጸሙ የሚያሳዩ ምሥሎችም አልፎ አልፎ ይቀረጻሉ።
የተቀረጹት ምሥሎች በማኅበራዊ የትሥሥር መድረኮች ይታተማሉ።
ለምሳሌ በዩትዩብ፣ በፌስቡክ ወይም በኢኒስታግራም።
እነዚህ ድርጅቶች ግን ተንቀሳቃሽ ምሥሎቹን ሳይውል ሳያድር ያግዷቸዋል።
ለምን ሲባል የድርጅቶቹን ፖሊሲ የሚጥሱ ስለሆኑ የሚል ምላሽ ይሰጣል። ይህ ትክክለኛ ምላሽ ነው።
ለሕሊና የሚከብዱና የሰዎችን ስሜት ሊያውኩ የሚችሉ ምሥሎች በፍጥነት ይወርዳሉ፤ ይሰረዛሉ።
ነገር ግን ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ እንደ ቁልፍ ማስረጃ ሊቀርቡ የሚችሉ የጦር ወንጀልን የሚያሳዩ ምሥሎች አብረው ለምን ይወገዳሉ?
ቢቢሲ ባደረገው የምርመራ ዘገባ ይህ እየሆነ ያለው ምሥሎቹን የመሠረዙ ተግባርና ኃላፊነት የተሰጠው ለማሽን በመሆኑ እንደሆነ ደርሶበታል።
ሜታ ኩባንያ የማስወገዱን ሥራ የሚሠራለት በአመዛኙ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ነው።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ደግሞ አንድ ምሥል ‘አስነዋሪ-ጸያፍ-ዘግናኝ’ መሆኑን እንጂ የጦር ወንጀል ማስረጃ ይሁን አይሁን መለየት አይችልም።
አሁን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እያሳሰበ ያለው በርካታ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚያሳዩ ምሥሎች በዚህ የተነሳ ሳይሰነዱ እስከናካቴው እየጠፉ መሆኑ ነው።
እነዚህ ምሥሎች ከማኅበራዊ ትሥሥር መድረኮች መውረዱን ይውረዱ፤ ነገር ግን መሰነድ ይለባቸውም ወይ?
‘እኛ ማስረጃዎችን አንሰርዝም’ ዩትዩብ
- “ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በምዕራብ ትግራይ የዘር ማጽዳት እየተካሄደ ነው” ሂዩማን ራይትስ ዋችከ 5 ሰአት በፊት
- አሜሪካ የብድር ጣሪያዋን አሻሻለችከ 3 ሰአት በፊት
- ባለፉት ወራት በእግር ኳሱ ዓለም ከታዩ አነጋጋሪ ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹከ 5 ሰአት በፊት
እነ ሜታና ዩትዩብ እነዚህ ‘አሰቃቂ ምሥሎች’ ለሕዝብ ጥቅም-ለፍትሕ መስፈን የሚጠቅሙ ከሆነ ከገጾቻቸው እንደማያስወግዷቸው ይናገራሉ።
ይህን ለማጣራት ቢቢሲ በዩክሬን በንጹሐን ላይ የተፈጸመ አሰቃቂ ግድያን የሚያሳይ ቪዲዮ ፌስቡክ ላይ እና ዩትዩብ ላይ ለመጫን ሞክሮ ነበር።
በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሁለቱም ድርጅቶች አስወግደውታል።
የዚህ ዋናው ምክንያት ሥራው በሰው ሠራሽ አስተውሎት ስለሚታገዝ ነው።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የማኅበራዊ ሚዲያውን የሚዘውቱት ግዙፍ ድርጅቶች በአስቸኳይ እነዚህ ጠቃሚ ሰነዶችን የሚጠብቁበት መንገድ መሻት አለባቸው ይላሉ።
አለን ረስብሪጀር የሜታ ኩባንያ የቁጥጥር ቦርድ ውስጥ አባል ነው።
ችግሩ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሲያስረዳ፣ “ማሽኖቹ አሰቃቂ ምሥል በተመለከቱ ቅጽበት ይሰርዙታል፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሆነና ለሕዝብ ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል ማሽኖቹ ሊያውቁ አይችሉም” ይላል።
እርሱ አባል የሆነበት የሜታ ኩባንያ የቁጥጥር ቦርድ የሚመራው በማርክ ዛከርበርግ ነው።
የቁጥጥር ቦርዱ በሜታ ኩባንያ ውስጥ ልክ እንደ ‘ጠቅላይ ፍርድ ቤት’ ነው የሚታየው። ሜታ ኩባንያ ደግሞ ፌስቡክን እና ኢኒስታግራምን የያዘ ነው።
“አሁን የኩባንያዎቹ ሐሳብ እንዴት አድርገን ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ ቪዲዮዎችን ጠቃሚ ካልሆኑት ጋር እንዲለይ እናስችለው የሚል ነው” ይላል አለን።
አለን ረስብሪጀት ቀድሞ የጋርዲያን ዋና አዘጋጅ ነበር።
ቤን ቫን ሻክ የግሎባል ጁስቲስ የአሜሪካ አምባሳደር ናቸው። “ማንም ኩባንያዎቹ ይዘትን ለምን ተቆጣጠራችሁ ሊላቸው አይችልም፤ ችግር የሚሆነው መረጃው ድንገት ሲሰረዝ ነው” ይላሉ።
ይህ ችግር ኢሆር ዛከርንኮን ገጥሞታል።
ዛኬሬንኮ ተጓዥ ጋዜጠኛ ነው። ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ በንጹሐን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ሲሰንድ ነው የቆየው።
ቢቢሲ ይህን ጋዜጠኛ ያገኘው ከኪየቭ ወጣ ብላ በምትገኝ ከተማ ነበር። በዚህች ከተማ ከዓመት በፊት በሕጻናት ላይ ሳይቀር አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሟል። የሩሲያ ወታደሮች ይህን ግፍ የፈጸሙት ከተማዋን ሸሽተው በመሄድ ላይ ሳሉ ነበር።
ይህ ጋዜጠኛ 17 አስክሬኖቹን ፎቶ አንስቷል፤ የተቃጠሉ መኪናዎችን ሰንዷል።
ይህንን ግፍ የዓለም ሕዝብ እንዲመለከተው ፈለገ። በኢኒስታግራም እና በፌስቡክ ገጽ አተማቸው። ተመልሶ ቢመለከት ጊዜ የሉም።
የት ሄዱ? ማን ሰረዛቸው?
“ሩሲያዊያን ራሳቸው ይህ ዉሸት ነው፤ እኛ ወታደሮችን እንጂ ንጹሐንን አንገድልም ሲሉ ነበር” ይላል ጋዜጠኛው። ነገር ግን በቅጽበት ተሰረዙ።
ቢቢሲ የዚህን ጋዜጠኛ ምሥሎች በድጋሚ በኢኒስታግራም እና በዩትዩብ በመለጠፍ የሚፈጠረውን ለማየት ሞከረ።
በአንድ ደቂቃ ውስጥ ከአራቱ ቪዲዯዎች ሦስቱ ተወገዱ።
ቢቢሲ በድጋሚ ቪዲዮዎቹን በአዲስ አካውንት ለመለጠፍ ሞከረ። ቪዲዯዎቹ የሰብአዊ ጥሰት መፈጸሙን ማስረጃ እንደሆነ በመጥቀስም በፌስቡክ ሊያትማቸው ሞከረ። ሊሳካለት አልቻለም።
ዩትዩብና ሜታ በዚህ ረገድ የሕዝብ ፍላጎት ያለባቸውንና ለሰብአዊ መብት ጥሰት ማስረጃ ሊቀርቡ የሚቸሉ ቪዲዮዎችን አናጠፋም ብሎ ይከራከራል።
ቢቢሲ ማረጋገጥ የቻለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው።
ሜታ ለዚህ በሰጠው ማስተባበያ ‘እኛ ሕጋዊ ጥያቄ ከሕጋዊ ድርጅቶች ከቀረበልን አናጠፋውም፤ ይህንንም ተግባር ለማስቀጠል እንሠራለን” ብሏል።
ዩትዩብ በበኩሉ ለሕዝብ ጥቅም የሚውሉ እስከሆኑ ድረስ እንደማይሰርዝ ገልጾ ነገር ግን ሰንዶ እንደማያስቀምጥ ገልጧል።
“ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ ሕግ አስከባሪዎች እነዚህን ሰነዶች በአግባቡ የሚያስቀምጡበትን መንገድ መፈለግ ይኖርባቸዋል”

ጥገኝነት ለመጠየቅ ቪዲዯውን ስፈልገው አጣሁት
ቢቢሲ ያናጋገው አንድ ኢማድ የሚባል ሶሪያዊ ይህ ገጥሞታል። አሌፖ ውስጥ ፋርማሲ ነበረው። በ2013 መንግሥት ቦምብ ሲያዘንብ ፋርማሲው ውስጥ ነበር።
ክፍሉ በአቧራ ተሞላች።
የሕዝብ ለቅሶና ኡኡታን ተከትሎ ወጣ። የተበጣጠሱ የሰው አካላት፣ ደም ሰፈሩን ሞልቶታል። ይህ ሁሉ ሲቀረጽ ነበር።
ከዚያ በኋላ ይህ ሁሉ በዩትዩብ፣ በቴሌቪዥን በፌስቡክ ተለጥፎ አይቶታል።
ከዓመታት በኋላ ኢማድ በአውሮፓ ኅብረት አገር ጥገኝነት ሲጠይቅ፣ የታል ማስረጃህ? የምታወራው ነገር እውነት ስለመሆኑ፣ ስለፋርማሲህ እስኪ ቪዲዯ አሳየን ተባለ።
ቪዲዮዎቹ እንደሚሰረዙ በፍጹም አልጠበቀም። ቢፈልግ ቢፈልግ አንድም ሊያገኝ አልቻለም።
እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለመቅረፍ ኔሞኒክን የመሰሉ ድርጅቶች ተፈጥረዋል።
ኔሞኒክ በርሊን መቀመጫውን ያደረገ ድርጅት ነው። የዚህ ድርጅት ዋና ሥራው እንዲህ ዓይነት ሰብአዊ ጥሰት የተፈጸመባቸው ቪዲዮዎችን ከመሰረዛቸው በፊት ቶሎ ግምጃ ቤት ማስቀመጥ ነው፤ መሰነድ።
እስከዛሬ ወደ 700ሺህ ምሥሎችን ሰንደዋል። የሶሪያዊው የኢማድ ፋርማሲ አጠገብም ቦምብ ሲዘንብ የሚያሳየውን ቪዲዮም ቅጂውን አስቀምጠዋል።
እያንዳንዱ ምሥል መቼ እንደተቀረጸ፣ ቦታውና ሌሎች መረጃዎችን የያዘ ነው።
ድርጅቱ ማስረጃዎቹን ለሚፈልጉ ሁሉ ሰንዶ ማስቀመጡን ቀጥሎበታል።
ፈታኙ ሥራ ታዲያ ይህን ሁሉ ምሥል በመልክ በመልክ ማስቀመጥና መመርመር ነው።
ራህዋ የምትኖረው በአሜሪካ ነው። ቤተሰቦቿ ግን በትግራይ ነው ያሉት። በትግራይ የከፉ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ ነበር።
በጦርነቱ ወቅት ባለስልጣናቱ የመረጃ ፍሰቱን በጥብቅ ይቆጣጠሩ የነበረበት ወቅት ነው።
ነገር ግን ማህበራዊ ሚዲያ በተስፋፋበት ሁኔታ ጦርነቶችን ከዓለም መደበቅ አይቻልም። ጦርነቱንም በተመለከተ የተለያዩ ምስላዊ መረጃዎችም ነበሩ።
እንዲህ ዐይነት ምሥሎችን መበርበርና ማሰናዳት፣ እንዲሁም መመርመር ፈታኝ የሚያደርገው ታዲያ ቤተሰቦችንም በዚያ ውስጥ ማግኘት ሊኖር ስለሚያጋጥም ነው።
“ይህ የኛ ተግባር ነው፤ ረዥም ሰዓት ምርመራ እያደረግኩ እቆያለሁ።ያሉኝን ሁሉ መሳሪያዎች በመጠቀም ይዘቶቹን ለማረጋገጥ በምሞክርበት ወቅት [በማህበራዊ ሚዲያ ላይ] የነበሩት መረጃዎች እየቀነሱና እየጠፉ ሲሄዱም ተመለከትኩ። ይህን ሁሉ ስታደርግ ግን ቤተሰብህ ደህና መሆኑን እንኳ አታውቅም” ትላለች ራህዋ።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አንድ መደበኛ የሆነ ሰነድ ማከማቻ መኖር አለበት ሲሉ ይወተውታሉ። የሚሰነዱት ምሥሎችም ከንክኪ መጠበቅ ያስፈልጋል። ተጠያቂነት ማስፈን የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው።