የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

ከ 3 ሰአት በፊት

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገሪቱ ተጨማሪ ገንዘብ እንድትበደር የሚፈቅደውን ስምምነት አጸደቀ።

ይህ ስምምነት ላይ ከመደረሱ በፊት የዓለማችን ታላቅ ኢኮኖሚ ብሔራዊ ዕዳዋን ሳትከፍል ትቀራለች የሚል ስጋትንም አጭሮ ነበር።

አሜሪካ ብድሯን መክፈል የሚያስችላትን የመንግሥት የዕዳ ጣሪያ ከፍ በማድረግም ዓለም ልትገባበት የነበረውን የፋይናንስ ቀውስ ማስቀረት ተችሏል ተብሏል።

ውሳኔው በሁለቱም ፓርቲዎች በኩል ተቃውሞ ቢቀርብበትም በአጠቃላይ 314 ለ117 በሆነ ድምጽ አልፏል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሕግ አድርገው ከመፈረማቸው በፊት የአሜሪካ የላይኛው ምክር ቤት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ድምጽ መስጠት አለበት።

የአሜሪካ መንግሥት በመጪው ሰኞ ግንቦት 28/ 2015 ዓ.ም. ያስቀመጠውን የብድር ገደብ እንደሚመታ ተተንብይዋል።

አሜሪካ የብድር ጣሪያዋን ካላሻሻለች ያለባትን 31.4 ትሪሊየን ዕዳ ያለመክፈል ዕጣ ይገጥማታል በሚልም ሕግ አውጭዎች ሰሞኑን ሲሟገቱ ነበር።

የአሜሪካ ብድር አለመክፈል ደረጃ ላይ መድረስ የዶላርን አቅም በማዳከም የዓለምን የምጣኔ ኃብት ሥርዓትም ያቃውሳል የሚል ስጋት እንዲያንዣብብ አድርጎት ነበር።

አሜሪካ ዕዳዋን ለመክፈል ግምጃ ቤቱ ቦንዱን በቅናሽ መሸጥ እንዲሁም ሌሎች ሥር ነቀል እርምጃዎች የአገሪቱ ኢኮኖሚ ድቀትን ሊያስከትል ይችላልም በሚል ተፈርቶ ነበር።

ረቡዕ አመሻሽ ላይ 165 የዲሞክራት የምክር ቤት ተወካዮች ከ149 ሪፐብሊካን ጋር በአንድነት የብድር ጣሪያውን ከፍ ለማድረግ የቀረበውን ባለ 99 ገጽ ረቂቅ ሕግ አጽድቋል። በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ በከፍተኛ ድምጽ ረቂቁን አሳልፎታል።

ሪፐብሊካኖች የታችኛውን ምክር ቤትን በበላይነት በሚቆጠጣሩበት ሁኔታ እንዲሁም ዲሞክራቶች በከፍተኛው ምክር ቤት እና በዋይት ሃውስ ውስጥ ባላቸው የበላይነት ለሳምንታት ያህል አንድ ውጤት ላይ መድረስ አቅቷቸው ነበር።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ኬቨን ማካርቲ ቅዳሜና እሁድ ፓርቲዎቹ የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ማድረግ አስችለዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን ውሳኔውንም ተከትሎ ባወጡት መግለጫ አፈ ጉባኤው በቅን ልቦና ተደራድረዋል በሚል አመስግነዋቸዋል።

“ሁለቱም ወገኖች የሚፈልጉትን ሁሉ አላገኙም። ከማስተዳደር ኃላፊነት አንዱ ይህ ነው” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።