· በሸገር ከተማ እየተካሄደ ባለው የግል ቤትና የእምነት ተቋማት ቤቶች ማፍረስ ተግባር፣ እንዲሁም የንፁሃን ዜጎች ግድያ አስመልክቶ ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የተሰጠ መግለጫ
========
“ህገ-ወጥ አሰራርን ተከትሎ ህግን ማስከበር አይቻልም”
*****
ከጥቂት ወራት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ መቋቋምን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ የግለሰቦች የመኖሪያ ቤትና የእምነት ተቋማት ቤቶች የማፍረስ ተግባር በስፋት እየተካሄደ ይገኛል። በዚህም ምክንያት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቤቶችና መንደሮች ሙሉ በሙሉ የፈረሱ ሲሆን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም እንዲፈናቀሉና ቤት አልባ ሆነው ጎዳና ላይ እንዲወድቁ ተደርጓል። ቁጥራቸው የተለያየ ቢሆንም ብዛት ያላቸው መስጂዶች፣ ቤተ ክርስቲያኖችና፣ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች የሃይማኖት መብቶችን በሚዳፈርና የአማኞችን ክብር በሚነካ መንገድ በአፍራሽ ግብረ ኃይል በግዳጅ እንዲፈርሱ ተደርገዋል።
ይህ የቤትና የእምነት ተቋማት ማፍረስ ተግባር በመሬት ወረራ እና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገነቡ ቤቶችን እና የእምነት ተቋማት ቤቶች ላይ ብቻ ያተኮረ፣ የከተማዋን ማስተር ፕላንና የህግ ማስከበር ተግባር እንደሆነ የከተማው እስተዳደር ይገልፃል። ነገር ግን ከነዋሪዎች ቅሬታ፣ ጉዳዩን በቅርበት ከተከታተሉና ምርመራ ካከናወኑ የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ተቋማት ሪፖርት እንዲሁም ፓርቲያችን በራሱ ካደረገው ግምገማ በመነሳት በሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው የቤትና የእምነት ተቋማት ቤቶች የማፍረስ ተግባር ህጋዊነትን ያልተከተለ፣ በተሳሳተ ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ፣ ወቅታዊነትን ያላገናዘበ፣ አማራጭ መፍትሄዎችን ያላካተተ፣ በአድሏዊ መንገድ እየተፈፀመ ያለና ብዙ ሺህ ዜጎችን ለማህራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያጋለጠ ህገወጥ ተግባር መሆኑን ተገንዝበናል።
ይህ የግል ቤቶችና የእምነት ተቋማት ቤቶች ማፍረስ ተግባር ሲጀመር በቂ ጥናትና ልየታ ያልተካሄደበት እና በህጋዊም ሆነ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገነቡትን የግልና የእምነት ተቋማትን ቤቶች ሳይለይ በጅምላ እንዲፈርሱ ያደረገ ነው። ከዚህም ባለፈ የግል ቤትና የእምነት ተቋማት ቤቶችን ወደ ማፍረሱ ተገግባር ሳይካሄድ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር ህጉ በሚያዘው መሰረት አስፈላጊውንና በቂ ውይይት ሳይደረግ፣ አስፈላጊው ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥበት በማን አለብኝነት እየተፈፀመ ያለ ተግባር ነው። የግል ቤትና የእምነት ተቋማት ቤቶች የማፍረስ ተግባሩ አድሏዊነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር የተስተዋለበት መሆኑን ከነዋሪዎች ቅሬታና ከሰብዓዊ መብት ተቋማት እየወጡ ካሉ መረጃዎች መገንዘብ ተችሏል።
ኦፌኮ እንደ ፓርቲ ህገወጥ የመሬት ወረራ መስፋፋትን የሚቃወም ሲሆን፣ የከተማ መሪ እቅድን ያልተከተሉ ህገወጥ ቤቶች መገንባታቸውንም አይደግፍም። ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው ግን መንግስት በህገመንግስቱና በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የተረጋገጡትን ዜጎች በቂ የመኖሪያ ቤትና የቤት መስሪያ ቦታ ከሙስናና ከተንዛዛ ቢሮክራሲያዊ አሰራር በፀዳ መልኩ የማግኘት መብትን ሳያከብርና መንግስታዊ ግዴታውን ሳይወጣና ህጋዊ መስመሮችን በአግባቡ ሳይዘረጋ የተወሰደ ግብታዊ እርምጃ መሆኑ ነው።
የመሬት አስተዳደር ፖሊሲው ግልፅነት የጎደለውና ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጠ ነው። መሬት በህገመንግስቱ መሠረት የህዝብና የመንግሰት ነው ቢባልም በተግባር ግን መሬት የገዢው ፓርቲና የባለሟሎቹ የግል መጠቀሚያ ሆኗል። መንግስት ፍትሃዊ የመሬት አስተዳደርና ምቹ አሰራር ያለመዘርጋቱ ዜጎች ኢመደበኛ መንገድ እንዲከተሉ አስገድዷል የሚል እምነት አለን። በህጋዊ መንገድ የቤት መስሪያ ቦታ ማግኘት ያልቻሉትና የአንገት ማስገቢያ በማጣት ወደ ኢመደበኛ ተግባራት የገቡት ላይ ህጋዊነት በጎደለው መንገድ እርምጃ መውሰድ ከሞራልም ከህግም አንፃር ተቀባይነት ያሌለው ነው። ከዚህም በላይ ዛሬ ህገወጥ ተብለው እንዲፈርሱ እየተደረጉ ያሉ የግልና የእምነት ተቋማት ቤቶች ግንባታ ላይ የመንግሰት አስተዳደር አካላት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የተባበሩና ተሳታፊ ሆነው ሳለ፤ በነዚህ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ሳይወስዱ ቤቶቹን ወደ ማፍረስ መገባቱ የራስን ስህተት በህጋዊነት ሽፋን ለመደበቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ እንደሆነ እንገነዘባለን። በዚህም ምክንያት ህዝቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ የፈጠረና በሂደቱ ላይ ተቃውሞ እንዲያነሳ እያደረገው ይገኛል። ከቤት ማፍረስ ተግባር ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ አንባጓሮዎች በሸገር ከተማ የተለያዩ ቦታዎች ብዙ ሰዎች በመንግሰት ኃይሎች እንደተገደሉ በቂ መረጃዎች ተገኝተዋል።
የሸገር ከተማ እያካሄደ ባለው የሃይማኖት ተቋማት ቤቶች ማፍረስ ምክንያት የሙስሊሙ ህዝብ ያለውን ተቃውሞ የፊንፊኔን ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በሰላማዊ መንገድ አሰምቷል። ይሁን እንጂ ባለፈው አርብ ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓም ሙስሊሙ ህዝብ ያለውን ተቃውሞ በአንዋር መስጂድ ውስጥ በመሆን በሰላማዊ መንገድ በማሰማት ላይ እያለ የታጠቁ የመንግሰት የፀጥታ ኃይሎች መስጂድ ቅፅር ግቢ ጥሰው በመግባት ከፈፀሙት ትንኮሳና ጥቃት ጋር ተያይዞ የሁለት ንፁሃን ሰዎች ህይወት አልፏል። ይህ የመንግስት ፀጥታ ኃይሎች ተግባር አላስፈላጊና የሃይማኖት ተቋማትንና የእምነቱን ተከታዮችን ክብር ያዋረደ፣ ኃላፈነት የጎደለው የኃይል ተግባር ነው። ኦፌኮ በአንዋር መስጂድ ከተካሄደው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ፣ አካላዊ ጉዳትና እስራት በፅኑ ያወግዛል። በዚህም ህይወታቸውን ላጡና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን እየገለፀ ለሟቾች ቤተሰብና ለመላው ሙስሊሙ ህዝብ መፅናናትን ይመኛል።ከ
ዚህ ጋር ተያይዞ በብልፅግና ፓርቲ መንግስት የአስተዳደር ግድፈትና በተቋማቱ የተወሰዱ ህገወጥ ተግባራትን አስታኮ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ያልተገባ የስም የማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደ ያለ ሲሆን የጉዳዩንም ቅርፅ በመለወጥ ለራሳቸው የፖለቲካ አላማ ለማዋል ያሰፈሰፉ ኃይሎች ተስተውለዋል። ይህን አጋጣሚ በመጠቀምም የኦሮሞን ህዝብ በሃይማኖትና በጎሳ ለመከፋፈል ከፍተኛና የተቀናጀ ጥረት እያደረጉ ያሉ ኃይሎችም አሉ። የነዚህ ኃይሎች ዓላማ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች እንዲስፋፉ በማድረግ የህዝብን አንድነትና ወንድማማችነት ማፍረስ ስለሆነ ህዝባችን በንቃት እንዲከታተላቸው እናሳስባለን።
በመጨረሻም በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን ቅሬታ ለመፍታትና ለችግሩም ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት፣ እዲሁም ከግድያው ጋር የታይዞ የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ:-
1/የሸገር ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል መንግስት የግልቤቶችንና የእምነት ተቋማት ቤቶች ማፍረሱን ተግባር በአፋጣኝ አቁሞ በህጋዊነቱና አተገባበሩ ዙሪያ እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶችን እንደገና እንዲፈትሽ፣
2/ሁኔታዎች ከአሁኑ በላይ ሳይወሳሰቡና የባሰ አደጋ ሳያስከትሉ ከህዝቡና የሃይማኖት ተቋማት ኃላፊዎች ጋርም በመሆን በውይይት መፍትሄ እንዲያበጅ ጥሪ እናቀርባለን።
3/የሸገር ከተማን ጨምሮ የከተሞች ልማትና መሪ እቅዶች የህዝቡን የመኖሪያ ቤት የማግኘት ሰብዓዊ መብትና የሃይማኖት ተቋማትን የማደራጀት መብት ባገናዘበ መልኩ ብዝሃነትን ባከበረና ፍትሃዊነትን በተላበሰ መንገድ እንዲቀረፅ እንጠይቃለን።
4/በአንዋር መስጂድ የተደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ የተፈፀመውን የንፁሃን ዜጎች ግድያ ሁኔታና፣ ከቤት ማፍረስ ጋር ተያይዞ በተለያዩ የሸገር ከተማ ቦታዎች በመንግስት አካላት የተፈፀሙ ግድያዎች በገለልተኛ አካል እንዲጣራና የኃይል እርምጃውን የፈፀሙ የፀጥታ አካላት ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣ ስለሁኔታውም ለህዝቡ ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።
5/ህዝባችንም ያለ አግባብ በሚነዛበት የከፋፋዮች ፕሮፓጋንዳ ሳይደናገር፣ እንደተለመደው አንድነቱንና ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ያለውን የወንድማማችነት መልካም እሴቱን ጠብቆ እንዲቆይ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)
ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓም
ፊንፊኔ፣ ኦሮሚያ