June 2, 2023 – DW Amharic 

በገዳሙ ሁለት የጥበቃ መሣሪያ ብቻ ነበር ያሉት ከ2006 ዓ.ም አንስቶ የገዳም አገልጋይ እንደነበሩ የሚናገሩት አባት በገዳሙ ውስጥ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ማሰልጠኛ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ የግጭቱ መነሻ ያሉትንም ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

«እስክንድር ነጋ እዚያ ቦታ ላይ ይገኛል ብለው መከላከያ እንዲገባ አድርገው ነው ይሄ ሁሉ ፍጅት የመጣው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አሉ እዚያ ውስጥ ማለት ነው።ገና መከላከያ ወደገዳሙ እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ሰዓት ዙርያውን የከበባ ስራ በሚሰራበት ሰዓት ገዳሙ ሊጠቃ ነው ሲባል ከዙሪያው የገቡ በርካታ አርሶ አደሮች አሉ ገዳሙን ለመታደግ መጀመሪያ የነበረው በሁለትና ሦስት ሰዎች የነበረው ግጭት ወደ ተቋም አድጎ የገዳሙ አማኝ የሆኑ ለገዳሙ የሚቆረቆሩ ወጣቶች ወደ ቦታው ገብተዋል።

ገዳሙ ጥቃት በሚፈጸምበት ሰዓት አለመግባባትም የተፈጠረ ለዚያ ነው።አንዱ ጋ የተተኮሰው ሌላ ጋ እየወደቀ እርበርሱ እያጋጫቸው ነው ይህን ያህል ጥፋት የመጣው።»የወረዳው አስተዳደር በገዳሙ ላይ ጉዳት አልደረስም ሲል በመግለጫው ቢያመለክትም አገልጋዩ እንደሚሉት ከግንቦት 18 ቀን፣ 2015 ዓ ም ጀምሮ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረኤሊያስ ወረዳ በሥላሴ አንድነት ገዳምና አካባቢ ጉዳት ደርሷል፡፡

«የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ቤተልሄሙ ላይ ከባድ መሣሪያ ወድቋል እየነጠረ ነው ይመለስ የነበረ። የተጎዱ ቤተክርስቲያኖች የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንና ሊጥ የሚቦካበት የተግባር ቤቱ ሦስቱም ጉልላት ወድቋል።ከዛ ውጭ ግን ነባር ቤተክርስቲያኖች በጣም ትላልቆቹ አንደኛው ላይ ከሀያ ምናምን ጊዜ በላይ አንደኛው ወደ አስራ አምስት ከባባድ የጦር መሣሪያዎች ወድቆባቸው እየነጠረ ይመለስ ነበር።አልፈነዳም።እሱም አለ ተቀምጧል ይሄ ነገ በታሪክ የሚታይ ስለሆነ።» ከአካባቢው በተገኘው መረጃ መሠረት በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ወታደራዊ ተሸከርከርካሪዎች ቢኖሩም የተኩስ ድምፅ ግን አይሰማም።