
June 11, 2023

‹‹የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ያገለለ የምክክር ሒደት ውጤታማ የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ነው›› የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተሳታፊዎች ልየታን በሚያካሂድበት ወቅት የምክክር ሒደቱ ዋናኛ ባለድርሻ አካላት የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔን፣ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የሲቪክ ማኅበራትን ከግምት አስገብቶ ተሳታፊ ሲያደርግ፣ የጋዜጠኞችን የሙያ ማኅበራትንም ሆነ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን የሚወክለውን ምክር ቤት መዘንጋቱ፣ የአካታችነትን መሠረታዊ መርህን የሚቃረን መሆኑንና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ያገለለ የምክክር ሒደትም ውጤታማ የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ሊሆን ስለሚችል፣ ሒደቱ እንደገና ሊጤን እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አሳሰበ፡፡
ኮሚሽኑ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ምክክር ያደረገ ቢሆንም፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን እንደ ተቋም ከመጋበዝ ይልቅ፣ ሌሎች ሲወያዩ የዜና ሽፋን እንዲሰጡ ብቻ የሚጋብዝ መሆኑ ትልቅ ጉድለት መሆኑን የገለጸው ምክር ቤቱ፣ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኩል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በአንክሮ እየተከታተለ መሆኑንና ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ከኖሩ ቅራኔዎችና ቁርሾዎች ጀምሮ፣ በየጊዜው ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት ውድመት ምክንያት ስለሆኑ ጉዳዮች ድረስ ነቅሶ በማውጣት ሕዝባዊ ውይይትና ምክክር በማድረግ መፍትሔ ያበጃል የሚል እምነት እንዳለው ጠቁሟል፡፡
ኮሚሽኑ ላለፉት ሁለት ዓመታት ራሱን በማደራጀትና ለምክክሩ አስፈላጊ የሆኑ የቅድም ዝግጅት ሥራዎችን ሲሠራ የቆየ መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅትም ወደ ተሳታፊዎች ልየታ ሒደት መግባቱን እንደተረዳም አክሏል፡፡
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተዓማኒነትና ውጤታማነት ከሚለኩበት መሥፈርቶች መካከል አንዱ የተሳታፊዎች ልየታ ሒደትና አተገባበር ዋናውን ቦታ እንደሚይዝ የገለጸው ምከክር ቤቱ፣ ዜጎች በአገራዊ ምክክር ሒደት ውስጥ በውክልናም ሆነ በቀጥታ እንዲሳተፉ ሲደረግ፣ የምክክር ሒደቱን አሳታፊነትና አካታችነት ለማረጋገጥ ያግዛል ብሏል፡፡
አገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሒደቱ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ለሕዝብ ሲተላለፍ (የቀጥታ ሥርጭቶችን ጨምሮ) መከተል ስለሚገባው ሥነ ምግባር፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በጥናት የተደገፈ ደንብ እያዘጋጀ መሆኑን ጠቁሞ፣ አገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ከዘጋቢነት ሚናቸው ባለፈ፣ በሙያ ማኅበራቱና በምክር ቤቱ የተወከሉ ሙያተኞች ሐሳብ በአግባቡ እንዲንፀባረቅ እንዲደረግና ሒደቱም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙዎችን የሐሳብ መዋጮ ከግምት እንዲያስገባ ጠይቋል፡፡
በመጨረሻም በቅርቡ የተከበረው የዘንድሮው የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን ‹የወደፊቱን መብት መቅረፅ፣ የንግግር ነፃነት ለሁሉም የሰብዓዊ መብቶች መከበር አንቀሳቃሽ ነው› በሚል መሪ ቃል በመሆኑ፣ ዜጎች በእንዲህ ያለ አገራዊ የምክክር መድረኮች ላይ ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ ማበረታታትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ ዕውቅና ላገኙ ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ሁሉ መከበር ሚዲያው ያለውን የማይተካ ሚና ለማጉላት መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነፀና በኃላፊነት ስሜት ሕዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በኢትዮጵያ እንዲጎለብት የሚሠራና የሕዝብ፣ የንግድ፣ የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃንን የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማኅበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በርስ የቁጥጥር ሥርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ተቋም መሆኑን አስታውቋል፡፡