
June 11, 2023

June 11, 2023
የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱበት ለወልቃይት አካባቢ በጀት እንዲለቀቅ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄ አቀረቡ፡፡
አባላቱ ጥያቄውን ያነሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የ2016 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት ረቀቂ በጀት ለምክር ቤቱ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡
የወልቃይት አካባቢ በኢሕአዴግ አገዛዝ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ የነበረ ሲሆን፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተከሰተ በኋላ ግን ይገባኛል የሚለው የአማራ ክልል በራሱ በጀት እያስተዳደረው ነው፡፡
ለ2016 ዓ.ም. በቀረበው አገራዊ በጀት ረቂቅ ከፌዴራል ለክልሎች በሚሰጠው የበጀት ድጎማ፣ የትግራይ ክልል ለቀጣዩ በጀት ዓመት 12.5 ቢሊዮን ብር፣ ለአማራ ክልል ደግሞ ብር 45.1 ቢሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የወልቃይት አካባቢ በጀት በየትኛውም ክልል ባለመመደቡ ጥያቄ አስነስቷል፡፡
በምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ አቶ መስፍን እርካቤ የተባሉ የምክር ቤት አባል፣ ‹‹ይህ ሕዝብ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች የመልማትና የማደግ ፍላጎት አለው፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ሕዝብ ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ አካባቢ በጀት ባለመመደቡ ሕዝቡም አመራሩም እየጠየቀ ነው፤›› ‹‹በጀቱ ለአማራ ክልል ወይስ ለትግራይ ክልል ተመድቦ ነው? ወይስ በራሱ በዞኑ ስም ለመመደብ የታሰበ ነገር አለ ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር የፓርላማ አባል አቶ ዳሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በርካታ ተፈናቃዮችንና በጦርነት ውስጥ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራና የራያ ሕዝብ የበጀት ፍላጎት ተሸክሞ ያለው የአማራ ክልላዊ መንግሥት በመሆኑ፣ ለክልሎች በሚሰጠው ድጎማ ይህ እንዴት ታይቷል ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ የወልቃይትን የበጀት ጥያቄ ሲያብራሩ፣ ‹‹የሕዝቡን ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ እናውቃለን፣ ጥያቄውን እናከብራለን፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚና ግን ይኼው ምክር ቤት ያፀደቀውን በጀት ማስተዳደር ብቻ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹እኛ ምንም ዓይነት ሥልጣን የለንም፡፡ በዋነኛነት ግን ለአማራ ክልልም ሆነ ለትግራይ ክልል በጀት በፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀረበልን ቀመር መሠረት እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በመሆኑም የፌዴራል ድጎማ በጀትን ለክልል ማስተላለፍ እንጂ፣ ለዞኖችና ለወረዳዎች በጀት የማስተላለፍ ሥልጣኑም ኃላፊነቱም እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሁኔታውን ከአማራ ክልልና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በስፋት ውይይት አድርገንበታል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ ኃላፊነቱን ሲወጣና በዚያ መሠረት ቀመር ሲሻሻል፣ የተሻሻለው ቀመር ወጥቶ ደግሞ ይኸው ምክር ቤት የሚያፀድቀው በመሆኑ ከዚህ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውጪ መውጣት አንችልም፤›› ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ መፍትሔውን ጠያቂዎቹም ያውቁታል ያሉት አቶ አህመድ፣ ‹‹ሌላው የልማት አጋሮች አምነውትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የተከተለ የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት አለው በማለት የበጀት ድጋፍ የሚያደርግለት መንግሥት በመሆኑ፣ ይኸው ምክር ቤት ከሚያውቀው የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት ውጪ መውጣት አንችልም፤›› ካሉ በኋላ የሕዝቡ ጥያቄ ፍትሐዊ ቢሆንም፣ ‹‹ከዚያ ከወጣን ግን በመላ አገሪቱ ላይ ያልተገባ ነገር ነው የሚሆነው፤›› ብለዋል፡፡