Muluken Muchie 

 · ሐዋርያ – Hawarya  

· በሀገር ልጅነት እንተዋወቅ፣

ኃይሉ አንተነህ ብላችሁ ልትጠሩኝ ትችላላችሁ::

የዘመናዊ ትምህርት ዕድል ያገኘሁት መማር ስላለብኝ ሳይሆን ባላባቶቹና ተወላጆቹ ዘመዶቸ የዘመናዊ ትምህርት ውጤቶች እያደናቀፏቸውና እያስጠቋቸው ስለመጡ ተምሬ ይህን መቋቋም እንድችል ነበር:: የሆነው ግን ተቃራኒ ነው፣ ተምሬ አጠቃኋቸው፣ ስለ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱን ተቃውሜ ያሰቡትን ሁሉ መና አስቀረሁት::

በትምህርት ገበታ በጣም ፈጣንና ስሉ ነበርኩ:: አጭር ማስረጃ ለመስጠት በዘመኑ የስድስተኛና የስምንተኛ አገር አቀፍ ፈተናዎችን በተናጠል በፐርሰንታይል ደረጃ 100% በማምጣት ነበር ያለፍኩት፣ ራስን ማሞጋገስ ባህል ባይሆንም ቀለሜዋ ነበርሁ ልላችሁ ነው::መሃከለኛውን የትህርት ደረጃ እንደተያያዝኩት የ1966ቱ አብዮት ፈነዳ:: ከደርግ ሥልጣን መያዝ በኋላ በተነሱ ጥያቄዎችና የተማሪ አመፅ፣ በየሰፈሩና በልዩ ልዩ አልባሌ ቦታዎች እንደ ቋያ እሳት ይንቦገቦግ በነበረው የውይይት መድረኮችና ስብሰባዎች እየተጠቀስኩና እየተጠራሁ የተሳተፍኩ ሲሆን የጎሕን መፅሄት “አይኔ በፈቀደ” እንዳከፋፍል ከእውቁና ዝነኛው መምህራችን ከአዳነ ዘለቀ ኃላፊነት ተሰጦኝ ሃላፊነቴን ተጠቅሜ እየመረጥኩ አከፋፍል ነበር:: ብዙ ሳይቆይ በመደበኛነት ጀማሪ የኢሕአፓ ምልምል ሁኜ በፓርቲው እቅፍ ውስጥ ወደቅሁ:: ይህ ሁሉ የሚሆነው ጎርጎራ ውስጥ ነው:: በዘመኑ ጎርጎራ ከተለያዩ አካባቢዎች፣ ማለትም ክጯሂት፣ ከቆላድባ፣ ከጀንዳ፣ ከሮቢትና ከጉራምብ (መሃል ደምቢያ)፣ ከደልጊ፣ ከቁንዝላ፣ ከደንገልበር፣ ወዘተ የሚመጡ የመለስተኝና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚተሙበት ውብ ጊዜ ነበር::

በመደበኛነት በኢሕአፓ ድርጅታዊ መዋቅር ከዋልኩ በኋላ በጣም ፈጣን በሆነ ሁኔታ በፓርቲው የአካባቢ መዋቅር ውስጥ ማለፍና ኃላፊነት መውሰድ ችያለሁ:: ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ የሚችሉ ቢሆንም በዋናነት ግን አንደኛ በንድፈ ሃሳብ ጥናት ፈጣንና አመርቂ የሆነ ውጤት በማሳየቴ: ሁለተኛ ከሰፊው የአርሶ አደር ኅብረተሰብ አብራክ የወጣሁ መሆኔና በውስጡ በብቃት በመንቀሳቀስ ኃላፊነቴን ልወጣ የምችል ከመሆኔ በላይ በእኔ ላይ የደህንነት ስጋቱ ዝቅተኛ ስለነበር (ኋላ ላይ አደጋው ያለፈኝ ባይሆንም) ይመስለኛል::

ከላይ እንደገለፅኩት የከበረና ዝና ካተረፈ የባላባት (ባላገር/ተወላጅ) የኅብረተሰብ ክፍል ከመምጣቴ በተጨማሪ በትምህርት ቤት በሰፊው የምታወቀው ከጥቂት ጓደኞቸ ጋር በትምህርት ጉብዝናዬ ነበር:: ከትግሉ ጋር በተያያዘ ምክንያት ለአንድ ዓመት ትምህርት አቋርጨ በነበረበት ወቅት ከጎርጎራ ርቄ በመንቀሳቀስ ሙሉ የንድፈ ሃሳብ ጥናት ብቻዬን አስገራሚ የንድፈ ሃሳብ ብቃትና የትግል ወኔ ከነበረው “በእምነቱ” ከሚባል የፓርቲው ባለሙያ ካድሬ ጋር አጠናሁ::

ከዚያ በቀጥታ የዚያን አካባቢ የሊግ የበላይ ኮሚቴ በመቀልቀል ለአንድ ሁለት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ከተንቀሳቀስኩ በኋላ ኮሚቴውን በፀሃፊነት(በአገናኝነት) እንድመራው ተደረገ:: በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ወደ ጎርጎራ ተመልሸ ትህርት የቀጠልኩ ሲሆን በዚህ ወቅት ብዙ ጓዶች ታሥረው፣ ወደ ሜዳ ሂደውና ሌሎችም ቀደም ሲል ተሰውተው ስለነበር የአካባቢው ኃላፊነት ከእኔና መሰሎቸ የሚወርድ አልነበረም::

በመሆኑም በውቅቱ ጎርጎራን እንደ አንድ በጣም ጠንካራ የአካባቢ መዋቅር ጨምሮ በጣም ሰፊ ቦታዎችንና መዋቅሮችን በሚወክል የበላይ አካል ኮሚቴ ውስጥ እንድሳተፍ ሆነ:: በዚህ ኃላፊነት ላይ እንዳለሁ የጎርጎራ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠቃላይ የተማሪዎች ተወካይ ሁኜ በመመረጥ በትምህርት ቤቱና በተማሪና አስተማሪ ጉዳይ ላይ የበላይ አካል በነበረው የትምህርት ኮሚቴ አባል ሆንኩ:

: ይህ ኮሚቴ የመምህራን ተወካይ፣ የወላጆችን ተወካይ፣ ከአካባቢው የገበሬ ማህበር ተወካይ፣ የቀበሌ ተወካይና ከመንግሥት ከወታደራዊ ክፍሉ የተወከ ባለሥልጣንን የሚያጠቃልል ሲሆን የትምህርት ቤቱ ዳሬክተር ዋና ፀሃፊ ሁኖ ይመራል:: ይህም ለድርጅታዊ ትግሉ እጅግ አመች ሁኔታ ፈጠረ፣ እንደተፈለገው መንቀሳቀስና መረጃዎችን ማሰባሰብ አስቻለ::

በዚህ ላይ እንዳለሁ ሰደዶች(የደርግ የደኅንነትና የምልመላ መዋቅር) አይናቸውን ጣሉብኝ፣ ሊያጠምዱኝ እንደፈለጉ ከሚመለከታቸው የድርጅቱ የደህንነት ክፍል ተነገረኝ:: የማይታለፉ እድሎችና ፈተናዎችም ተፈፀሙ:: ከዚያ ቀደም ብሎ ጎርጎራ ውስጥ በሰደድ የአካባቢው ከፍተኛ መዋቅር ውስጥ ወሳኝ የሆነ የድርጅቱ መረብ ነበር:: ከሀ-ፐ የነበረውን የአካባቢ የፖለቲካ ኡደት ኢሕአፓ ይቆጣጠረው ነበር::

—-

በዚሁ እንቆይ፣ ከቀጠልኩ ብዙ እንጨዋወት ይሆናል፣