Muluken Muchie 

 · ሐዋርያ – Hawarya 

 · በሀገር ልጅነት እንተዋወቅ፣

ቁጥር፣ 2

ከዚህ በፊት ባቀረብኩት ትርክት ላይ ራሴን እንዳስተዋወቅሁት ኃይሉ አንተነህ ተብዬ ልጠቀስ እችላለሁ::

ብዙውን ጊዜ ጥዋት ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ከቤቴ ስነሳ ለለሊት ስብሰባ ወጥቸ ካላደርኩና የግድ በዚያው መሄድ ከሌልብኝ በስተቀር ከቅርብ ወንድሞቸ ጋር ነበር አብሬ የምወጣው:: ያን ዕለት ምንም እንኳ ያደርኩት በቤቴ ቢሆንም ጥዋት ላይ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ስንዘጋጅ በሆነ ጉዳይ እኔ ዘገየሁና ድረስብን ብለው ጥለውኝ ሄዱ:: ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ የቆየሁበትን ጉዳይ አጠናቅቄ እየተጣደፍኩ ወጥቸ ስሄድ ከሰፈራችን ብቸኛ መውጫ በር ላይ የሆነ ሰው እጆቹን በግራ ቀኝ ኪሶቹ ከትቶ ሲንቀሳቀስ ዓይኔ ተወርውሮ አየው:: መምጣቴን እንዳወቀ ከታች እስከ ላይ በዓይኖቹ እየተመለከተ ቆም ብሎ ጠበቀኝ:: ሰውየው ለእኔ የቆመ መሆኑ ገና ካየኝ ጀምሮ የሚያሳየው የአካል እንቅስቃሴና አቋቋም ያሳብቅበታል::

ደግሞም ቀደም ባሉት ጥቂት ቀናቶች ውስጥ የሚፈልገኝ ኃይል እንዳለ ስለተነገረኝ ለዚህ ገጠመኝ ዝግጅት ሳደርግ ሰንብቻለሁ:: ካለበት ቦታ ደርሸ ፊት ለፊት እንደተያየን የደህና አደርክ ሰላምታውን በጭዋ አንደበት ካቀረበልኝ በኋል ስሜን ጠርቶ አንተ ነህ ወይ አለኝ:: በአውንታ እንደመለስኩለት እጁን ለሰላምታ ዘርግቶ ለአጠፌታው የዘረጋሁለትን እጄን በመጨበጥ ሞቅ አድርጎ ተዋወቀኝ:: ጠብቅ ተብዬ ስጠብቀው የዋልኩት ያደርኩት ሰው መሆኑን ተረዳሁ:: ክፍል እንዳልዘገይ አብረን እየተራመድን ብርቱውን መልክቱን አበሰረኝኝ:: አብዮታዊው መንግሥት ለከፍተኛ ተልዕኮ እንደሚፈልገኝና በአብዮታዊ ሰደድ ሥር መታቀፍ እንዳለብኝ ገለፀልኝ:: ስሜቱን በማይጎረብጥ ሁኔታና አቀራረብ ሃሳቤንና አስተያየቴን ከገለፅኩለት በኋላ ቀጣዩን እርምጃ ነግሮኝ ወዲያውኑ ተለየኝ::

ከተለየኝ በኋል ቀኑን ሙሉ ስለጉዳዩ ሳነሳ ስጥል፣ የሚመለከተውን የፓርትዬን አካል ሳማክር ዋልኩ:: ይህን ግለሰብ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ እንደማየውና አንዱን ዕለትም በአካባቢው በብዙ መልኩ በኢሕአፓ ወገናዊነት ከሚገመት (በእርግጥም ጠንካራ አባል ነበር) ግለሰብ ጋር ከመሸ በኋላ ጨለማ ተገን አድርጌ “አምስተኛ ሻምበል” በሚባለው አንዱ የጎርጎራ መውጫ በር በኩል ለሥራ ስንቀሳቀስ አብረው እየተጫወቱ ሲንቀሳቀሱ ማየቴን አስታወስኩ::

በአዲሱ የሰደድ አባል እውቂያዬ የተሰጠኝ ቀጣይ እርምጃ አብዮታዊና ድርጅታዊ እንቅስቃሴዬን ለመጀመር በተመደበልኝ ኮሚቴ ውስጥ ገብቸ መሥራት የሚያስችለኝን የቦታና የሰዓት ቀጥሮ መቀበልና መፈፀም ነበር:: በተባለው ቦታ፣ ቀንና ሰዓት ተገኘሁ:: ቦታው እዚያው ከተማ በሚገኝ የመኖሪያ ቤት ውስጥ ነበር:: በሰዓቱ ከቦታው ደርሸ በሩን አንኳኳሁ:: ካሁን ቀደም ምንም ንግግር የሌለኝ ያውቀኛል ብየም የማልገምተው እኔ ግን እዚያው ጎርጎራ ውስጥ በአንደኛ ደረጃ መምህርነቱ የማውቀው አንድ ሽቅርቃሬ /ራሱን ለየት ባለ ሁኔታ ተንከባካቢ ሰው የቤቱን በር ከፍቶ ሰላምታ ከሰጠኝ በኋላ በክበር እንድገባ ጋበዘኝ::

ወደ ውስጥ ስገባ የቤቱ የእንግዳ መቀበያ ክፍል በሰዎች ተሞልቷል:: ሁሉም በጉጉት ሲጠብቁኝ በቆየ ስሜት ሰላምታ ሰጥተውኝ እንድቀላቀላቸው ጋበዙኝ:: በሩን ከከፈተልኝ ጋር ሶስቱ የአንደኛ ደረጃ መምህሮች ናቸው:: ከሶስቱ ሁለቱ አንደኛ ደረጃ እያለሁ የትምህርት ቤቴ መምህራኖች የነበሩ ሲሆን አንደኛው በጣም የሚወደኝና የሳይንስ አስተማሪዬ የነበረ ነው::

ከቀሩት ውስጥ ሁለቱ የጎርጎራ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሲሆኑ አንደኛው አብሮ አደጌና በትምህርቱ በጣም ጎበዝ የነበርና በዚሁ በትምህርት ቤት ደረጃ የሚታወቅ ነበር:: ሁለተኛው ተማሪ በትምህርት ቤት ደረጃና በከተማ ልጅነቱ አውቀዋለሁ እንጅ ብዙም ንግግር የለንም::

ነገር ግን ከዚህ ግለሰብ ጋር ቀደም ባሉት ሳምንታንት ውስጥ አንድ አስገራሚ የሆነ ገጠመኝ ነበረኝ:: ከትምህርት በኋላ ለመሠረተ ትምህርት ፕሮግራም ተመድቤ በዚያው በእኛው ትምህርት ቤት የተወስውኑ ቀናት ምሽቶችን አስተምር ነበር:: ይህ ወገንም እንዲሁ በዚያው ሰዓት በዚሁ ትምህት ቤት ግቢ ውስጥ እንደሚያስተምር አውቃለሁ::

ከተማሮቸ መሃል ከአንዷ ወጣት ተማሪ ጋር በጣም ንፁህ የሆነ ቅርርብ ነበረኝ:: ይች ተማሪ የምትመጣው ከጦር ሰፈሩ ካምፕ ነው:: ቤቴን መጥተህ ካላየህና ካልጋበዝኩህ እያለች ብዙውን ቀን ትማፀነኛለች:: አንዱን ቀን እሽ ብያት ቀጠሮ አድርገን ካምፕ ውስጥ ወዳለው ቤቷ በስሟ አልፌ ሄድኩላት:: ስደርስ በጣም ደስ ብሏት ተቀበለችኝ:: የወታደር ቤት እንደመሆኑ መጠን ቤቷ በጣም ጠባብ ክፍል ናት፣ እንደ ልጅቱ ዘመናዊነትና ውጫዊ ግምት በዚያች ክፍል ውስጥ ትዳር ይዛ ትኖራለች ተብሎ አይገመትም::

ምናልባት ከዚያ በፊት የውትድርናን አኗኗር ስለማላውቅም ሊሆን ይችላል:: ልጅቷ ባሏ ግዳጅ ላይ እንዳለ ገልፃልኛለች:: ብዙ ነገሮችን ግምት ውስጥ አስገብቸ በከፍተኛ የሞራል ልክ ላያ ራሴን ለመጠበቅ ዝግጁ ነኝ:: ወልፈት ላለማለት በእጅጉ ዝግጁ ነበርኩ:: ንፁህ እህትነቷን እንደምወድላት፣ በትምህርቷ መበርታት እንዳለባት፣ ባሏን በሰላም እንዲመልስላት በመመኘትና በመምከር ላይ ሥራዬን አድርጊያለሁ::

ይህ በዚህ እንዳለ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ሁለት ነገሮች ሆኑ:: መጀመሪያ ይህ በጀማሪያው የአብዮታዊ ሰደድ ስብሰባ ላይ ያገኘሁት ተማሪ መጥቶ ሰላምታ ሰጥቷት ትንሽ ከተጨዋውውቱ በኋላ ሄደ:: በደምብ እንደሚተዋወቁ ግልፅ ነው:: በእኔ እዚያ መገኘት ደንታ የሰጠው አይመስልም:: እኔ ግን ይህ ወንድም እዚህ ካምፕ ውስጥ ነው የሚኖረው? ካምፕ ገብቸ ከዚች ውስጣት ልጅ ጋር ሲያየኝ ምን ይሰማው ይሆን የሚሉ ሃሳቦች አእምሮዬን ጠዝጥዘውታል::

ይህ ወጣት እንደሄደ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሙሉ ወታደራዊ ልብስ የለበሰና ሽጉጥ የታጠቀ ጠና ያለና ፈርጣማ ወታደር ወደ አለንበት መጥቶ ቤት ውስጥ በመግባት ከልጅቱ ጋር ሰላምታ ተለዋወጣት፣ እኔንም ክፉ ባልሆኑ ዓይኖቹ ተመለካክቶኝ ተሰናብቶ ሄደ::

በውቅቱ የጫረብኝ ክፉ ስሜት ልጅቱ ቆንጅዬና ተግባቢ ልጅ ስለነበረች ምልባት እንዲህ እየመጡ አጨዋውተዋት የሚሄዱት ወንዶች ቢበዛ በፍትወት ስሜት ፈልገዋት ሊሆን ይችል ይሆናል የሚል ሲሆን ለዚህም ከቶውን ግድ የሌለኝ ጉዳይ ነበር:: በወቅቱ አንድም ልጅ ነኛ፣ ሲበዛ ደግሞ ለትግል የመነንኩ ነበርኩ:: የእኔ ዋናው ተልእኮ ልጅቱን ምክንያት አድጌ ወደ ጦር ሰፈሩ ካምፕ መግባት መቻሌና ለድርጅቱ እንቅስቃሴ ያመች ዘንድ ሁኔታዎችን በመቃኘት ማመቻቸት ብቻና ብቻ ነበር::

ሌላውና የመጨረሻው የአዲሱ ኮሚቴ ተሰብሳቢ ሁኖ ያገኘሁት ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ አስተማሪየ የነበረውና ነፍሰ ሥጋዬ የሚያውቀው መምህር ነበር:: የኮሚቴው ፀሃፊም ይህ ሰው ነበር:: ስለዚህ ግለሰብ ግልፅና ዘርዘር አድርጌ ማቅረብ እፍፈልጋለሁ:: ስሙ አፈወርቅ ጊለይ ይባላል:: ከብዙ ትምህርቶቹ ውስጥ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ የሳይንስ አስተማሪያችን ነበር:: ተግባር ተኮር የሆነና ሙያውን አክባሪ መምህር እንደነበረ አስታውሳለሁ::

የማጋለጥ ዘመቻ ተካሂዶ ጥዋት ጥዋት ይሰጥ ለነበረው የብዙሃን ጅምናስቲክ እንቅስቃሴ አቀናባሪና መሪ ነበር:: በዚህ ኮሚቴ ከተገናኘን በኋላ አንዴ ስለ እኔ የሰጠው አስተያየት ሁሌ ሲደንቀኝ ኑሮ ሕወሓት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ጥያቄዬ ተመለሰልኝ:: አንዱን እለት የእለቱን ፕሮግራም አጠናቀን በቃለ ጉባኤ ላይ በማይውል ጉዳይ ላይ ስንጨዋወት ስሜን ጠርቶ “አንተ እኮ ኢሕአፓ እየተጫወተብህ ነው እንጅ እንዴት ያለህ ጎበዝ ተማሪ ነበርክ” አለኝ:: በጣም ደነገጥሁ::

ትልቁ የአብዮታዊ ሰደድ ተወካይ እኔን እንዲህ ከጠረጠረ እንዴት በዚህ ኮሚቴ ውስጥ እንድቀመጥ መፍቀድ ብቻ አይደለም፣ እንዴትስ ነብሴን ማራት ብዬ በፍራት ትክክል አይደልህም ብዬ ተቃውሞየን በብስጭት ለመግለፅ ሞከርኩ:: ረጋና ደርበብ ብሎ በፈገግታ የሚያሳስብ ጉዳይ እንዳልሆነ አድርጎ አለፈው::

ከቃሉ የሰማሁትና የተነገረኝ ትልቅ የአደጋ ምልክት ቢሆንም በአካባቢው ከፍተኛው የአብዮታዊ ሰደድ መዋቅር ላይ ኢሕአፓ ቁጥጥር እንዳለው ስለማውቅ ብዙም ሳልረበሽ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው ጋር ተነጋገርኩበት:: ሕወሓት ሥልጣን እንደያዘ በተከታተልኩት መረጃ መሠረት መምህር አፈወርቅ ጊለይ የሕወሓት ዋና ባለሙዋልና ቀኝ እጅ እንደነበር ተረዳሁ::

ለካንስ ያኔም የሕወሓት የውሥጥ ሰው ስለነበር ነው የእኔን ሌላ ሰውነት አናንቆ ያለፈው:: ምናልባትም ከረጅም የተማሪና አስተማሪነት ግንኙነታችን የተነሳ አሳምሮ ስለሚያውቀኝ ምናልባት እኔም ያው ነኝ በማለት ክፉዬን ጠልቶ ይሆን ብዙም ደንታ ያልሰጠው ብዬ የቆየ ግርምቴን አወራረድሁ::

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ የአካባቢው የኢሕአፓ መዋቅርና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሊገመት እንደሚችለው የሰፋና ደህንነቱ የተጠበቀ ነበር:: ጊዜውን እንዴት አብቃቅቶ መንቀሳቀስ ይቻል እንደነበር ሳስበው ግን ህልም እንጅ የእውን ዕርምጃ አይመስለኝም:: እንደተገለፀው በዚያን ሰዓት በሞት ጥላ ሥር እየተሽሎከለኩ በፓርቲው ከባቢያዊ ከፍተኛ ኮሚቴ ውስጥ መሳተፍና ያን ብርቱ የሆነ ኃላፊነት ተሸክሞ መንቀሳቀስ፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠር የተማሪ ተውካይ ሁኖ ማገልገል፣ “በጠላት” መዋቅር ውስጥ መደበኛና ህጋዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ልዩ ልዩ የህቡእ መዋቅሮችን መምራትና ከዚህም ተርፎ መሠረተ ትምህርት ለማስተማር መብቃትና ልዩ ልዩ መረባዊ ሥራዎችን ማከናወን የሰው አቅም የሚፈቅደው አይመስልም፣ይሁን እጅ የተደረገ ሃቅ ነው::

—-

ጊዜ ከተገኘ ይቀጠላል፣