June 14, 2023 – EthiopianReporter.com 

በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ የተደረገ ውይይት

ዜና በሕገ መንግሥቱ ላይ የታሰበው ማሻሻያ በገለልተኛ ተቋማት እንዲመራ ተጠየቀ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: June 14, 2023

በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት የማሻሻል ወይም የመቀየር ሒደት የግጭትና የአለመግባባት ጉዳዮችን በቀላሉ ለመፍታት እንዲያስችልና ሁሉንም ማኅበረሰብ አማክሎ በቂ አገራዊ ምክክር ለማድረግ፣ ከሥርዓቱ አገልጋይ ተቋማት ወጥቶ በገለልተኛ ተቋማት እንዲመራ ምሁራን ጠየቁ፡፡

የአገራዊና ቀጣናዊ ትስስር ማዕከል (ሴንሪስ) የተሰኘው አገር በቀል ድርጅት በ1987 ዓ.ም. በፀደቀው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ከተውጣጡ የዘርፉ ምሁራን የሚሳተፉበትን አራተኛ ዙር ውይይቱን፣ ሰኔ 2 እና 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የሕገ መንግሥትና የሰብዓዊ መብት መምህር አቶ ዘለዓለም እሸቱ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ሕገ መንግሥቱ በዝግጅት ምዕራፉ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ባማከለ መንገድ ትርጉም ያለው ተሳትፎ መደረግ እንዳለበት፣ ማሻሻያው ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባም ወጥ በሆነ መንገድ እንዲተገበር ማድረግ አሁን ያለውን የቅቡልነት ጥያቄ መቅረፍ ያስችላል ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ፅንፍ የያዙ የተለያዩ አመለካከቶች በሚንፀባረቁበት በዚህ ወቅት በስፋት መታየት ያለበትና ቅድሚያ ሊታሰብበት የሚገባው ምኑ ይቀየር ከሚለው ባለፈ፣ እንዴትና መቼ ይሻሻል የሚለው የሥነ ሥርዓት ጥያቄ መሆኑን በመጥቀስ የማሻሻያ መንገዱ ከማቀራረብ ይልቅ ልዩነትን እንዳያሰፋ መጠንቀቅ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተለይ ‹‹እኔ የበላይ ነኝ›› በሚል ዕሳቤ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ሳያደርጉ ሕገ መንግሥት ለማሻሻል መሞከር የባሰ ቀውስ እንደሚፈጥር አክለዋል፡፡

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ መሐመድ ንጉሥ ኢብራሒም በሰጡት አስተያየት፣ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል  ከፖለቲከኞች ውጪ ያሉ አካላትና ሕዝቡ ሰፋ ያለ ውይይት ሊያደርግበት ይገባል ብለዋል፡፡ ሕገ መንግሥት ሲባል የሕዝቦች ወይም የአንድ አገር የአብሮ መኖር ዋስትና እንጂ፣ የመንግሥት ሕግ ብቻ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ጠቁመዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ከመንግሥት አካል ውጭ ገለልተኛ በሆኑ አገራዊ ተቋማት አማካይነት እንጂ፣ የአንድ ወቅት የሥርዓት አገልጋይ በሆኑ ተቋማት ከሆነ የሚገኘው ውጤት ከታለመለት ዓላማ ውጪ ሊሆን እንደሚችል ሥጋታቸውን አቅርበዋል፡፡

ለአብነት እንደ ማጠናከሪያ በማለት በቅርቡ የፖሊሲ ጥናትና ኢንስቲትዩት የተባለ የመንግሥት ተቋም ስለፌዴራሊዝም ሥርዓት አካሄድኩት ስላለው ጥናት ተናግረዋል፡፡ በተቋሙ ጥናት መሠረት 1,200 ዜጎች አሁን ያለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት አያስፈልግም የሚል መልስ ሰጥተዋል ተብሎ የቀረበው ጽሑፍ፣ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 1,200 ሰዎች የፌዴራሊዝም ሥርዓት አያስፈልግም ብለዋል የሚል ድምዳሜ ይዞ ወደ ሚዲያ መውጣቱ ተቋማዊ ቁመናው ላይ ጥርጣሬ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡

ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል የተወከሉ ሌላ ተሳታፊ፣ ከላይ የተነሳውን የሕገ መንግሥት የቅቡልነት ጥያቄ አጠንክረው በመግለጽ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ከጅምሩ ሲረቀቅ የተገለሉና ያኮረፉ አካላት ስለነበሩ፣ እንዲሁም ፀድቆም መተግበር ሲጀምር በአግባቡ መተግበር አለመቻሉን በመጥቀስ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሲታሰብ አሁን ባለንበት አገር አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት ወቅት ለማሻሻል ከተሄደ፣ ጊዜው የእኛ ነው የሚሉ ሰዎች ሊጠቀሙበት ይችሉ ይሆናል እንጂ አገራዊ መግባባት ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፤›› ብለዋል፡፡

እኝህ ተሳታፊ በቅርቡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም አካሄድኩት ብሎ ካቀረበው ጥናት ጀርባ ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ በመጥቀስ፣ በዚህ ጥናት ሊሻሻሉ ይገባል ተብለው የቀረቡት ድንጋጌዎች አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ፍላጎት እንደሆኑ ለመረዳት ችያለሁ ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ወቅታዊ አገራዊ ችግሮች አሉብን፡፡ ነገር ግን እነዚህን አገራዊ ችግሮች በመፍታትና በተረጋጋ መንፈስ በቂ ውይይት ተደርጎበት ወደ ማሻሻል ካልተገባ የባሰ አገራዊ ቀውስ ያመጣል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተወከሉት አቶ አወል ዓሊ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ያላት አገር ናት እያልን፣ ነገር ግን በመንግሥትና በሕገ መንግሥት ልምምዳችን የፊቱን ቀደን እየጣልን በመምጣታችን አሁንም ሕገ መንግሥት እንዴት ይሻሻል የሚል ክርክር ውስጥ ገብተናል፤›› ብለዋል፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች መንግሥት የሚባለው ተቋም በውል ሳይኖራቸው፣ በቅኝ ግዛት በሚተራመሱበት ጊዜ ኢትዮጵያ ከ1923 ዓ.ም. ጀምሮ ሕገ መንግሥት የነበራት አገር ነበረች ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን በእነዚህ ሒደቶች ውስጥ ጥሩ ልምምድ ሳይፈጥሩልን የቀሩት፣ የመጣው የመንግሥት ሥርዓት ሁሉ የነበረውን እየቀደደ አዲስ ሕገ መንግሥት በመፍጠር ላይ በመጠመዱ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ አሁን በተጀመረው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ቢያንስ የማይነኩ የሚባሉ የሕገ መንግሥት አንቀጾች ምንም እንኳ የአተገባበር ችግር ቢኖርባቸውም፣ እንዳሉ እንዲቀጥሉና መሻሻል ያለባቸው አንቀጾች በአግባቡ ውይይት ተደርጎባቸው ሊሻሻሉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ታሪኩ ታደለ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንድ የፖለቲካ ሥልጣን በያዘ አካል ገፊነትና ከፍተኛ ሚና የሚዘጋጅ መሆኑን አውስተው፣ አሁን ለማሻሻል ሲታሰብ ሒደቱ ተመሳሳይ የሆነ መንገድ ተከትሎ የፖለቲካ ሥልጣን በያዘ አካል የሚጣል ከሆነ ከአሥር ወይም ከሃያ ዓመታት በኋላ አዲስ ሥርዓት ሲመጣ ለማሻሻል እንደገና መቀመጥ አይቀርም ብለዋል፡፡ በመሆኑም በሒደቱ ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለማሻሻል ሲገባ ይዘቱና በምን ሁኔታ መታየት አለበት የሚለውን በግልጽ ተቀምጦ መነጋገር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡    

የተሻለ አገርና ዴሞክራሲ እንዲፈጠር ከታሰበ የምሁራን ወይም የፖለቲካ ቡድን ከሚያስጮኸው ጉዳይና የፖለቲካ አቋም ከመያዝ በመውጣት፣ ተቀራርቦ በመነጋገር ከእናሸንፋለን ዕሳቤ በመላቀቅ ለአገር አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መነጋገር መሠረታዊ መሆኑን የተናገሩት፣ በቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሕግ መምህር አቶ አንተነህ አለባቸው ናቸው፡፡

ከጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የተወከሉት አቶ ሙሉዓለም አይቸው እንደሚሉት፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚነሱ ጉዳዮች ብዙ የተባለላቸውና የተጻፈላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን እንዳይሻሻል ከዳረጉት ጉዳዮች መካከል ታሪክንና ሕገ መንግሥቱን ለያይቶ ማየት ባለመቻሉ ነው ብለዋል፡፡ ምንም እንኳ ታሪክና ሕገ መንግሥት የሚገናኙበት መንገድ ቢኖርም፣ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ከቅንነት በመነጨ ዕሳቤ በመደማመጥና ተነጋግሮ የተጣመሙ የታሪክ ጉዳዮችንም ሆነ የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች እንደ ፈርጃቸው ማየት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ በርካታ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የምክክር መድረክ በመጠቀም ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል አወያይቶ በሚመጣው ውጤት መሠረት ቁጭ ብሎ በመነጋገር ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል አስፈላጊ ነው የሚለው ጉዳይ በአመዛኙ ተነስቷል፡፡ ይሁን እንጂ ቀድሞ አገራዊ ምክክር ሳይደረግ ወደ ማሻሻል ከተገባ በማያስማሙና በሚያጋጩ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ሳይደረስ፣ የሚሻሻለው ሕገ መንግሥትም ሆነ ውጤቱ ተመልሶ ላለመግባባት መነሻ ይሆናል ተብሏል፡፡