June 14, 2023 – EthiopianReporter.com 

ዜናፖለቲካ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

June 14, 2023

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ ሥልጣን እንደመጣ፣ በአገሪቱ ያሉና የማያሠሩ የሕግ ድንጋጌዎችን ለማሻሻልና ለመለወጥ (Judicial Reform) የተጀመረውን ሥራ ለማከናወን፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ኤጀንሲ (USAID) በሰጠው 22 ሚሊዮን ዶላር (1.2 ቢሊዮን ብር) ድጋፍ፣ ከአራት ዓመታት በላይ ሲሠራ ቆይቶ ሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. መጠናቀቁ ይፋ ተደርጓል፡፡

እ.ኤ.አ. በየካቲት ወር 2019 የኢትዮጵያ መንግሥት ኤጀንሲው በሕግ ማሻሻያ (ሪፎርም) ላይ እንዲያግዘው ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበልና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን፣ ማለትም ከፌዴራልና ከክልሎች ፍርድ ቤቶች፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከዓቃቢያነ ሕግ ቢሮዎች፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ከተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመተጋገዝ፣ የሪፎርሙ ሥራ ሲከናወን መክረሙን፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ኤጀንሲ (USAID) የቀድሞ ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ቶማስ ስታል ተናግረዋል፡፡

የፍትሕ (Justice) ፕሮጀክት ፕሮግራም በሚል መጠሪያ ከአራት ዓመታት በላይ ሲከናወን የቆየውን የሕግ ማሻሻያ (Judicial Reform) ሥራ፣ በኢትዮጵያ እንደ ‹‹ተምሳሌታዊ›› እና ለቀጣይ ሥራዎች መነሻ እንደሚሆን ሚስተር ስታል ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የአስተዳደር ሕግን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሕግን፣ የፀረ ሽብር ሕግንና የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅን ከመደገፉም በተጨማሪ፣ ከጎንደርና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ከ3000 ለሚበልጡ ፈቃደኛ ለሆኑ ቡድኖች ዕርዳታ ማድረጉም ተገልጿል፡፡ በሴቶች መብቶች፣ ፆታዊ ጥቃትና የጥላቻ ንግግሮች ላይ መሠረት ያደረጉ 180 የሬዲዮ ፕሮግራሞችንና አንድ መቶ ክፍል ያላቸው የቴሌቪዥን አስተማሪ ድራማዎች መሥራት መቻሉንም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥበትን ስትራቴጂ እንዲያዘጋጅና የምርመራ አሠራሩን እንዲያሻሽል ድጋፍ ማድረጉን፣ መንግሥትም ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ማሰርን እንዲያቆም፣ የሕግ ማሠልጠኛ ተቋማት በሁሉ ነገር የተደራጁ እንዲሆኑና ፍርድ ቤቶች በአግባቡና በትክክለኛው መንገድ እንዲሠሩ ድጋፍ መደረጉንም ምክትል ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን የበቃች ለማድረግ (በፍትሕ ዘርፍ) ማለትም ሕግን የተከተለ አሠራር እንዲኖር፣ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ፣ በፍትሕ ተቋማት ላይ አራት ቢሊዮን ዶላር ወይም 220 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ መጠናቀቅን አስመልክቶ በሸራተን አዲስ በተደረገው ፕሮግራም ላይ የቀድሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊንና እሳቸውን ተክተው የተሾሙት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረትን ጨምሮ የክልል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡