June 21, 2023 – EthiopianReporter.com

የብሔራዊ ምርድ ቦርድ ሰበሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከሕዝብ ውሳኔ አስፈጻሚዎች ጋር ሒደቱን ሲከታተሉ

ዜና በወላይታ ሕዝበ ውሳኔ ባዶ መታወቂያ እየሞላ ለመራጮች ሲያድል የነበረ ግለሰብ መያዙ ተገለጸ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: June 21, 2023

በወላይታ ዞን በተካሄደ ድጋሚ ሕዝበ ውሳኔ በርካታ ባዶ መታወቂያዎች ድምፅ ለሚሰጡ ሰዎች ለማደል አስቦ በመንቀሳቀስ የነበረ እንድ ግለሰብ እጅ ከፍንጅ መያዙ ተገለጸ፡፡

የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን፣ በዕለቱም በሕዝበ ውሳኔው የሚሳተፉ ነዋሪዎችን የመመዝገብና ድምፅ እንዲሰጡ የማድረግ ተግባር ጎን ለጎን ተከናውኗል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በዞኑ የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ከተጠናቀቀ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ግለሰቡ በሶዶ ዙሪያ ድልቧ ዋጭሮ ምርጫ ጣቢያ ባዶ መታወቂያ ይዞ እየሞላ ለመራጮች ሊሰጥ ሲል እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡

በሌላ በኩል በሁምቦ ምርጫ ጣቢያ የቦርዱ ምርጫ አስፈጻሚ ሳይሆን የምርጫ አስፈጻሚ መሆኑን የሚገልጽ የሌላ አስፈጻሚ፣ መታወቂያ በመያዝ ሊገባ ሲል መያዙን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ስድስት ወራት ያልሞላው የነዋሪነት መታወቂያ የያዙ በርካታ መራጮች ለምዝገባና ድምፅ ለመስጠት መገኘታቸው፣ ሌላው በሕዝበ ውሳኔው የተስተዋለ ለየት ያለ ክስተት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አንድ በመራጭነት የመሳተፍ መብት የተሰጠው ዜጋ ድምፅ መስጠት የሚችለው በመኖሪያ ሥፍራው ቢያንስ ለስድስት ወራትና ከዚያ በላይ መኖሩ ሲረጋገጥ እንደሆነ፣ የቦርዱ የምርጫ መመርያው እንደሚደነግግ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ የድምፅ መስጠት ሒደት ከተጀመረ በኋላ ግን በርከት ያሉ መራጮች፣ ከተሰጣቸው ስድስት ወራት ያልሞላው መታወቂያ ይዘው መቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ቦርዱ ስድስት ወራት ያልሞላው የነዋሪነት መታወቂያ ይዘው የቀረቡ መራጮች ከያዙት መታወቂያ በተጨማሪ ነዋሪነታቸውን የሚያረጋግጡበት የሦስት ሰዎች ምስክርነት፣ ወይም ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ድምፅ እንዲሰጡ መደረጉን ገልጿል፡፡

ቦርዱ ድጋሚ ሕዝበ ውሳኔውን የሚያከናውኑ ከአዲስ አበባ 5,215 የምርጫ አስፈጻሚዎችና ከወላይታ 3,845 የምርጫ አስፈጻሚዎች ያሳተፈ መሆኑን፣ በዛ ያሉ ሠልፎች በታዩባቸው አንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች ቦርዱ አሠልጥኖ በተጠባባቂነት የያዛቸውን አስፈጻሚዎችን በተጨማሪነት ማሰማራቱን አስታውቋል፡፡

ድጋሚ ሕዝበ ውሳኔው በዞኑ በተቋቋሙ 1,812 የምርጫ ጣቢያዎች የተከናወነ ሲሆን፣ በዕለቱ እስከ ቀኑ 8 ሰዓት ድረስ 514,620 ነዋሪዎች ድምፅ መስጠታቸውን የቦርዱ መግለጫ ያመለክታል፡፡

ቀደም ሲል በወላይታ ዞን ላይ የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ በመራጮች ምዝገባ ወቅትና በምርጫው ቀን የሕግ ጥሰቶች በማጋጠማቸው ምክንያት፣ ሕዝበ ውሳኔው በድጋሚ እንዲካሄድ ቦርዱ መወሰኑ ይታወቃል፡፡

ቀደም ሲል በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ላይ ከተስለተዋሉ የሕግ ጥሰቶች መካከል በመራጮች ምዝገባ ወቅት የተፈረሙ የመራጮች ፊርማና በምርጫ ቀን የተፈረሙ ፊርማዎች መለያየት፣ ዕድሜያቸው ያልደረሱ ዜጎች እንዲመርጡ ማድረግ፣ ያለ ፊርማ የመራጮች ካርድ የወሰዱ መራጮች መኖር፣ የመራጮች በግንባር ሳይቀርቡ ካርድ መውሰድ፣ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ታጭቀው መገኘታቸው፣ በምርጫው ቀን የማስፈራራትና የምርጫውን ሚስጥራዊነት የመጣስ ድርጊቶች መሆናቸውን የቦርዱ መረጃ ያመለክታል።

የፌዴራል ፖሊስና የፍትሕ ሚኒስቴር ባደረጉት ማጣራት 136 ተጠርጣሪዎችን መለየታቸውን፣ ከነዚህም ውስጥ 94 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለቦርዱ ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ቦርዱ የድጋሚ ሕዝበ ውሳኔውን ውጤት በመጪው ሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ወይም ከዚያ ቀደም ብሎ ሊገልጽ እንደሚችል አስታውቋል፡፡