የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና  ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ
የምስሉ መግለጫ,የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ

ከ 5 ሰአት በፊት

ለሁለት ዓመት የተደረገውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ በፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ተፈርሟል። በዚህም ስምምነት መሠረት ትግራይ ለብቻዋ አድርጋው የነበረው ምርጫ ፉርሽ እንዲሆን እና የተመሠረተው መንግሥትም እንዲፈርስ ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት ክልሉ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ እና የተለያዩ ፖርቲዎች ጥምረት የሆነው ጊዜያዊ መንግሥት እያስተዳደረው ይገኛል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለሚቋቋመው ጊዜያዊ መስተዳደር የሰጠው የሥልጣን ጊዜ ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ሲሆን፣ በዚያው ወቅትም አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል።

የጦርነት ቀጣና በነበረችው የትግራይ ክልል እና ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች በሚቀጥለው ዓመት 2016 ዓ.ም. ምርጫ ለማካሄድ እንደታቀደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጹ ይታወሳል።

ቦርዱ ይህንን የገለጸው በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የ2015 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት የአፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ግንቦት 03/ 2015 ዓ.ም. ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።

የቦርዱ ባለሙያዎች በትግራይ ክልል ካሉ የፖለቲካ አመራሮች እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ምርጫ ለማካሄድ ስለሚቻልበት ሁኔታ መወያየታቸው ተገልጿል።

በትግራይ ምርጫ መቼ ሊካሄድ ይችላል? የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እውቅና ይመለስልኝ ጥያቄ፣ እንዲሁም በቅርቡ በድጋሚ ስለተደረገው የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ ዙሪያ ቢቢሲ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ቢቢሲ፡ በቅርቡ ትግራይ ክልልን ጨምሮ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሌሎች ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሆናችሁ ገልጻችኋል። ለምሳሌ በትግራይ ክልል ምርጫውን ለማካሄድ ምን ዓይነት ዝግጅት እየተደረገ ነው?

ብርቱካን፡ ከትግራይ ክልል አኳያ እስካሁን ያደረግነው ዝግጅት የቅድሚያ ምዘና (assessment) ነው።

ምርጫ ለማካሄድ፣ መሬት ላይ አስቻይ ሁኔታዎች እና ዝግጁነቶች አሉ ወይ? የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው ተመልሰዋል ወይ? የሰላሙ ሁኔታ ምን ይመስላል? የሲቪል ማኅበረሰቡስ፣ የፓርቲዎች ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን የሚገመግም ቡድን ልከናል።

[ቡድኑ] እኛ ብቻ ሳይሆን አጋሮቻችን የተሳተፉበት የመስክ ምልከታ አድርጎ ነበር።

በፍጥነት በአሁኑ ወቅት ምርጫ ለማደራጀት የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ ነው በአብዛኛው የሰበሰብነው መረጃ የሚያሳየው።

ነገር ግን ሁኔታዎች ሊሻሻሉ ይችላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይሄንን ከስር፣ ከስር የምንከታተለው ይሆናል ማለት ነው።

ነገር ግን ሪሶርስን (አቅምን) በተመለከተ በአብዛኛው ከመንግሥት በኩል ችግር ይገጥመናል ብለን አናምንም። እስካሁን በሄድንበት ሂደት ምርጫ መደራጀት የሚኖርበት ጊዜ እንደ ዋና ወይም ቅድሚያ እንደሚሰጠው ተግባር መወሰድ አለበት።

ከትግራይ ምርጫ አኳያ ሪሶርስ (አቅም) ችግር ይሆናል ብዬ አላይም። ዜጎች በነጻነት ሃሳባቸውን ለመግለጽ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ እንዲሁም የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መኖር አለባቸው።

የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ መሆን አለበት። የፓርቲዎች በአማራጭነት ለመቅረብ ያላቸው ዝግጁነትም እንደዚያው። ከፓርቲዎች አኳያ ብዙ እንቅስቃሴዎችን አይተናል።

ምዝገባ ሂደት ላይ የነበሩ፣ ሂደታቸው የተቋረጠባቸው እነዚህን ሂደቶች እየጨረሱ ይገኛሉ። ከእኛ ፈቃድ ወስደው አዳዲስ ፓርቲዎችም እየተደራጁ ነው፤ ይሄም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሂደቱ ይጠናቀቃል ብለን እናምናለን። የሲቪል ማኅበራትም ራሳቸውን እንደገና ለማደራጀት እየሞከሩ ነው።

ነገር ግን ሲቪል ማኅበራቱ በአብዛኛው የገለጹልን፣ አሁን ያሉበት ሁኔታ ወደ ምርጫ ሥራቸውን ፊታቸውን ለማዞር አስቸጋሪ እንደሆነ ነው።

ቢቢሲ፡ አስቸጋሪነቱ ከምን አንጻር ነው? ከመሠረተ ልማቶች አለመሟላት፣ ከፖለቲካው ምኅዳር አኳያ?

ብርቱካን፡ [የሲቪል ማኅበራቱ] በአብዛኛው የገለጹልን የተፈናቃዮች ሁኔታ ወደ ምርጫ ለማተኮር ጥሩ ዕድል ገና እንዳልፈጠረ ነው። በርካታ ተፈናቃዮች እንዳሉ የሰብዓዊ እርዳታ እገዛ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ዜጎች መኖራቸው ነው።

እንዲሁም ሲቪል ማኅበራቱም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስለቆዩ ራሳቸውንም ለማደራጀት እና ከሕዝብ ጋር ተገናኝቶ ሰላማዊ የሆነ ፖለቲካዊ ውይይት ለማድረግ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመጥቀስ እነዚህን ጉዳዮች አንስተዋል።

ቢቢሲ፡ ከወራት በፊት በተደረሰው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሟል። ይህም ስምምነት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከስድስት ወር አስከ አንድ ዓመት ውስጥ በኃላፊነት ሊቆይ እንደሚችል አስቀምጧል። ምርጫው በዚያ ጊዜ ገደብ ውስጥ መድረስ አይችልም ማለት ነው?

ብርቱካን፡ አይደረስም ከሚለው የመጨረሻ ድምዳሜ ላይ አልደረስንም። የማቴሪያል ዝግጅት ቀድሞም አድርገናል። አጠቃላይ ምርጫን በተመለከተ የሎጂስቲክስ፣ የህትመት የመሳሳሉት ብዙ ከባድ ነገር አይደሉም። ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የተፈናቃዮች እና የፀጥታው ጉዳይ በትግራይ ከተስተካከለ መልሰን ወደ ምርጫ ዝግጅት እና ወደ ማስፈጸሙ እንሄዳለን።

በአፋጣኝ ልናደርግ የምንችልበትም ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብዬ ነው የማምነው። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ጊዜ ከማብቃቱ በፊት ምርጫ ሊደረግ አይችልም የሚል ድምዳሜ ላይ ምርጫ ቦርድ በነበረው ግምገማ አልደረሰም። ከስር ከስር ሂደቶች ሲለወጡ የምንከታተለው ይሆናል ማለት ነው።

ቢቢሲ፡ በእናንተ ግምገማ መሠረት አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ አይፈቅድም ወይም ላይፈቅድ ይችላል? ምርጫውን ለማስኬድ የሚያስችላችሁ ነገር እንዲፈጠር እናንተ ምን እያደረጋችሁ ነው? ከመንግሥት ጋር ሊሆን ይችላል ወይም ከሌላ አካላት ጋር የምታከናውኗቸው ተግባራት ይኖሩ ይሆን?

ብርቱካን፡ በእኛ [በምርጫ ቦርድ] በኩል መዘጋጀት ያለብንን ዝግጅቶች እያከናወንን ነው። ጽህፈት ቤታችንን በደንብ በአቅም ማጠናከር አለብን። በነገራችን ላይ አሁን ያሉን የትግራይ ጽህፈት ቤት ሠራተኞች ሕዝበ ውሳኔ በተካሄደበት ወላይታ ዞን መጥተው ልምድ እንዲቀስሙ አድርገናል። በእኛ በኩል የሚያስፈልገውን ተግባራት እየሰራን ነው።

ቢቢሲ፡ ከትግራይ ሳንወጣ ህወሓት የሕጋዊ ሰውነት ዕውቅናው እና የተወረሱ ንብረቶቹ እንዲመለሱለት መጠየቁ በምርጫ ቦርድ ተቀባይነት አላገኘም። ቦርዱ ያለው ሕጋዊ አማራጭ እንደገና መመዝገብ እንደሆነ ለህወሓት ገልጿል። ህወሓትም በምላሹ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ተቀባይነት የለውም ብሏል። ቀጣዩ ነገር የሚሆነው ምንድን ነው?

ብርቲካን፡ በድጋሚ መመዝገብ አንፈልግም የሚለው ለእኛ በጽሁፍ የደረሰንም ሆነ ለምርጫ ቦርድ የተገለጸ ምንም ነገር የለም። ምርጫ ቦርድ ካስተላለፈው ውሳኔ በኋላ ለእኛ የደረሰን መረጃ የለም። ተስፋ የምናደርገው በውሳኔያችን መሠረት ማሟላት የሚገባቸውን ፎርማሊቲዎች [መስፈርቶች] አሟልተው ይመዘገባሉ የሚል ነው። ወይም በውሳኔያችን ቅሬታ ካላቸው ፍርድ ቤትም ሊሄዱ ይችላሉ እሱም ሌላ አማራጭ ነው። በእኛ በኩል ምንም የተገለጸልን ነገር የለም ሂደቱን የምንከታተለው ይሆናል።

ብርቱካን ሚደቅሳ

ቢቢሲ፡ በቅርቡ ሰኔ 12/2015 ዓ.ም. ወደተካሄደው የወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ እንሂድ። በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን የተደረገው ሕዝበ ውሳኔ በድጋሚ የተካሄደ ነው። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?

ብርቱካን፡ ከዚህ ቀደም ጥር 29/ 2015 ዓ.ም. ተደርጎ የነበረው ሕዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባም ሆነ ውጤት በወላይታ ዞን የተሰረዘበት እና ድጋሚ ሕዝበ ውሳኔ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በተለይም የመራጮች ምዝገባ ሂደትን በተመለከተ ከፍተኛ የሆነ የሕግ ጥሰት እንደተፈጸመ ቦርዱ በማረጋገጡ ነው።

ውጤቱንም ሆነ መረጃዎቹ እውነተኝነታቸውን ለመቀበል አዳጋች ሁኔታ ላይ በመገኘቱ ሕዝበ ውሳኔው ድጋሚ እንዲደረግ ተወስኗል። እነዚህ ጥሰቶች በተለይም በመራጮች ምዝገባ ላይ የተፈጸሙ የማጭበርበር፣ ሐሰተኛ መረጃ የመጠቀም፣ ሐሰተኛ ሰነድ መጠቀም የመሳሰሉት ተግባራት ለሕዝበ ውሳኔው መደገም ምክንያቶች ነበሩ።

ቢቢሲ፡ ድጋሚ በተደረገው ሕዝበ ውሳኔስ የጎላ ችግር ታይቶ ይሆን?

ብርቱካን፡ የሕዝበ ውሳኔው ሂደት፣ የመራጮች ምዝገባም ሆነ የድምጽ አሰጣጥ በሰላማዊ ሁኔታ፣ ሥርዓቱን በጠበቀ ሁኔታ ጉልህ የሆነ ከባድ ችግር ሳያጋጥም በትክክለኛ ሁኔታ ተጠናቋል። ከዚያም በኋላ ያሉ ተግባራት የቆጠራ፣ ጊዜያዊ ውጤትን በየጣቢያዎቹ የማሳወቅ ሂደቱም ተጠናቋል።

ውጤቶቹንም ሆነ የድምጽ መስጫ ወረቀቶቹንም ወደ ምርጫ ቦርድ 12 ማዕከላት የማምጣት ሥራም መጠናቀቁ ተገልጿል። በአጠቃላይ ሂደቱ ከባድ የሚባል እንዲሁም ሂደቱን እና ውጤቱን ከዚህ ቀደም እንዳጋጠመን በመሠረታዊነት ተጽዕኖ ሊያሳድርበት የሚችል ችግር አላጋጠመም።

ቢቢሲ፡ ሕዝበ ውሳኔው በድጋሚ ሲደረግ ከወጭ፣ ሠራተኞችን ከመመደብ አንጻር አድካሚ ከመሆኑ አንጻር ምርጫ ቦርድ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል የሚሉ አሉ። ሆኖም ከዚህ ቀደም የተደረጉት የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ እንዲሁም የአሁኑ የወላይታ ሕዝበ ውሳኔዎች ጋር ተያይዞ ከደቡብ ክልል ጋር መቆየት እንፈልጋለን የሚለው አማራጭ ብዙ ቅስቀሳ አይደረግበትም። ከዚያ በተጨማሪ ግን አዲስ ክልል ለመመሥረት የመንግሥት ፍላጎት እንዳለ እና ብልጽግና ፓርቲ አቅጣጫ አስቀምጦ አዲስ ክልል የመመሥረት ፍላጎት እንዳለው ይገልጻል። ስለዚህ ይሄ ሂደት መንግሥት የወሰነው ነው። መንግሥት ብዙ የሄደበት ነው እና ምርጫ ቦርድ ይህንን ሂደት ሕጋዊ ወደማድረግ ይሄዳል እንጂ ብዙም ውጤት የለውም ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ። እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ብርቱካን፡ በዚህ አስተያየት አልስማማም። እኛ የሕዝበ ውሳኔ ሥርዓቱን እና አፈጻጸሙን በእጅጉ ዋጋ እንሰጠዋለን። ዋጋ መስጠታችን በተግባርም በወጪም፣ በድካምም ተደጋጋሚ ሙከራዎች የሚደረጉት ሂደቱ ትርጉም ያለውና ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ነው ብለን ስለምናምን ነው። ኃላፊነታችንን ለማረጋገጥ ደግሞ እንደ ምርጫ ቦርድ ያለብን ኃላፊነት ስለሆነ ነው። ሰዎች እንግዲህ በብዙ ምክንያት ምን ዋጋ አለው? ያው ውጤቱ ይታወቃል ብለው አስተያየት ሊሰጡ ይችላሉ።

ነገር ግን ምርጫ ቦርድ ሂደቱን ሲያስፈጽም በዚያ መንፈስ ወይም ምልከታ አይደለም። ከደቡብ ክልል ጋር መቆየትን በተመለከተ ደግፎ የሚከራከር ባለመኖሩ ውሳኔው በአንድ በኩል ያዘመመ ነው የሚል ነገር ተነስቷል፤ እኛም መራጮች ግራ ቀኙን መዝነው ያላቸውን አማራጮች እና በሕይወታቸው እና በኑሯቸው ላይ የሚኖረውን ውጤት ተመልክተው መረጃ ላይ ተመርኩዘው እንዲወስኑ ሁለቱም አማራጮች መብራራት እና መገለጽ እንዳለባቸው እናምናለን።

ያንን በተደጋጋሚ ከሲዳማ ጀምሮ ዕድሉን ሰጥተናል። ነገር ግን ፍላጎት አሳይቶ ወደፊት መጥቶ የሚከራከር በተለይም የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ በሚደረግበት ጊዜ ማንም አልነበረም። ከዚያ በኋላ ግን የተለያዩ ክርክሮችን በማዘጋጀት በተለይም በዚህኛው ሕዝበ ውሳኔ ላይ በሦስት መገናኛ ብዙኃን ላይ ሰዎች እና ፓርቲዎችን ጋብዘን ክርክሮችን፣ የውይይት ሃሳቦችን አቅርበናል።

እዚያ ላይ እንደ አንድ ችግር የማየው በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ያለውን የክልል አደረጃጀት የማይደግፉ ማለት ነው፣ መጥተው እንዲከራከሩ እና ሃሳባቸውን እንዲገልጹ በምንጠይቅበት ወቅት ያንን ከማድረግ ይልቅ ሂደቱን በአጠቃላይ ቦይኮት (አለመሳተፍ) ማድረግን ይመርጣሉ። ይህ ደግሞ ለዜጎችም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ይጠቅማል ብለን አናምንም።

እነሱ የፈጠሩትን ክፍተት ለመሙላት የተለያዩ ምሁራን፣ በጉዳዩ ላይ የጻፉ፣ ያነበቡ እና ዕውቀቱ ያላቸው ቀርበው ሃሳብ እንዲገልጹ፣ ሲቪል ማኅበረሰባትም በደንብ እንዲሳተፉ አድርገን በተወሰነ ደረጃ ሕዝቡ ያለውን አማራጭ እንዲያውቀው፣ ጥቅም እና ጉዳቱንም እንዲገነዘበው በእኛ በኩል የሚጠበቅብንን አድርገናል።

ለወደፊቱ የሚደረጉ ሕዝበ ውሳኔዎች ከዚህም የላቀ ተሳትፎ ፣ ክርክሮች እናደርጋለን።

ከዚያ አኳያ ሃሳብን ከማሳወቅ ብቻ ሳይሆን የሂደቱን እውነተኝነት፣ ዜጎች ያለምንም ተጽእኖ ፍላጎታቸውን መግለጽ እንደሚችሉ ከማረጋገጥ አንጻር፣ ታዛቢዎች እንዲገኙ ከማድረግ አኳያ፣ ሌሎችም የምርጫን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ አሠራሮችን ከማረጋገጥ አኳያ ከአንደኛው ሕዝበ ውሳኔ ወደ ሁለተኛው እየተሻሻለ መጥቷል።

አሁን የተደረገው ሦስተኛው የወላይታ ሕዝበ ውሳኔ በድጋሚ መካሄዱ ራሱ የሚያሳየው ምርጫ ቦርድ ሂደቱን የመቆጣጠር፣ ትክክለኛነቱን የማረጋገጥ፣ ተሳስቶ ሲገኝ ደግሞ ያንን በማስረጃ የማረጋገጥ አቅሙ እየጎለበተ መምጣቱን ነው።

እነዚያ ችግሮች ድጋሚ እንዳያጋጥሙ አዳዲስ አሰራሮችን አምጥተናል። በድጋሚው ሕዝበ ውሳኔውም ላይ እንዳየነው አሰራሮቹ ከሞላ ጎደል ውጤታማ ነበሩ ማለት ይቻላል።

ቢቢሲ፡ ለምሳሌ የሲዳማ ክልልነትን ጥያቄ በምንመለከትበት ወቅት በርካታው ማኅበረሰብ ክልሉ እንዲመሠረት ፍላጎት እንደነበረው እና እስከ ግጭት ያደረሰ ሁኔታ መፈጠሩ ይታወሳል። ደቡብ ምዕራብን በምናይበት ወቅት እርስዎም እንዳሉት ምርጫ ቦርድ እስከ መድገም ድረስ ሄዷል ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ። ግን ከሕዝብ ይልቅ ክልሎቹ እንዲመሠረቱ የመንግሥት ፍላጎት ይንጸባረቅባቸዋል የሚሉ ሃሳቦች ይነሳሉ። ይህ ደግሞ ታች ያለውን ሕዝብ ጥያቄን ከመመለስ ይልቅ ድጋሚ ሌላ ወቅት ጠብቆ ሌላ ዓይነት ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል የሚሉ አሉ። ሕዝበ ውሳኔዎቹ በትክክል የሕዝቦችን ድምጽ እና ሁኔታ ስለማያንጸባርቁ ችግሮቻቸውን በትክክል አይፈቱም ከሚል አኳያ ይህ ጥያቄ ይነሳል።

ብርቱካን፡ ሌላ ጊዜ ሌላ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል የሚለው አዎ ይችላል። መነሳቱ እንደ ችግር መታየት ያለበት አይመስለኝም። ምክንያቱም አደረጃጀቶች ከጊዜ ወደጊዜ፣ ክልልነትንም ጨምሮ ዜጎች ከሚያጋጥማቸው ሁኔታ አንጻር እየተመለከቱ ይህ አደረጃጀት ይለወጥን ብለው የመጠየቅ መብታቸው ሁልጊዜም የተከበረ መሆን አለበት። በሕገ መንግሥቱም ዲሞክራሲያዊ አሰራር እንዲኖረን እስከፈለግን ድረስ ማለት ነው።

አሁን የተደረገው ሕዝበ ውሳኔ የሕዝቡን ፍላጎት ይገልጻል፣ አይገልጽም የሚለው የሕዝብ ፍላጎት መጨረሻ ላይ የሚገለጸው በድምጽ ሳጥን ላይ ተቆጥሮ በሚገኝ ውጤት ነው።

ያንን ሳናደርግ አጠቃላይ በየትኛውም አገር የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ሕዝብ ይሄንን ይፈልጋል፣ ያንን አይፈልግም የሚለውን የተለያዩ አስተያየቶች ሊነገሩ ይችላሉ።

ምርጫም ሆነ ሕዝበ ውሳኔ የሚያስፈልገን በአንጻራዊነት በተረጋገጠ እና በተጨባጭ ሁኔታ ቆጥሮ ለማሳወቅ ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር የሚጠጋጋ ምዘና እንዲኖር ለማድረግ ያለን ብቸኛ መንገድ ይሄ ስለሆነ ነው።

ምናልባት ሃሳባቸውን ያልገለጹ ዜጎች አሁንም አሉ የሚባል ከሆነ፣ የሕዝቡ ፍላጎትም ወደፊት የሚጠየቅ ከሆነ እንዲሁ ጥያቄው ተነስቶ የሚስተናገዱበት መንገድ መኖር አለበት።

ለምርጫ ቦርድ ሂደቱ ላይ አተኩረን በብዙ ልፋት እና ወጪም ጭምር ሂደቱን ትክክለኛ ለማድረግ የምንሰራው አንዱ ዋናው ምክንያታችን ይኸው ነው። ሥርዓቱ የዜጎች ፍላጎት በተለያየ ጊዜ የሚገልጹበት መንገድ፣ ሂደቱ በትክክለኛ ግልጽ እውነተኛ ሲሆን በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ጥያቄዎች በተለያየ ሁኔታ ተደራጅተው እንዲቀርቡ ዕድሉን ይሰጣል።

ዕድሉን መስጠት ብቻ አይደለም በሚመጡበት ጊዜ ጥያቄው የሕዝቡን ፍላጎት በትክክል የሚመዝን ሥርዓት እና የአሰራር ተቋም እንደሚኖር አመኔታ ይጨምርላቸዋል።

ያ ትልቅ እመርታ ነው ብለን እንወስዳለን። በዚህ ሂደት ውስጥ የተለየ ፍላጎት ኖሯቸው ያንን ፍላጎት ለመግለጽ ራሳቸውን ያላደራጁ፣ ድምጻቸውን በጣም ያላሰሙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቢኖሩ ይሄ የመጨረሻው ለዘላለም የሚቆይ አሰራር ነው ብዬ አላምንም። በግልም፣ እንደ ተቋምም እንደዚያ አናምንም በሕግም አተረጓጎምም ቢሆን በዚያ መልኩ ነው ማየት ያለብን።