

ዜና ምርጫ ቦርድ የሕወሓትን ሕጋዊ ሰውነት እንደገና እንዲመልስ ንግግር መጀመሩ ተሰማ
ቀን: June 25, 2023
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕወሓትን ሕጋዊ ሰውነት ጥያቄ እንደገና እንዲመልስ ለማድረግ፣ ከመንግሥት ጋር ንግግር መጀመሩን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ገለጸ፡፡ ምርጫ ቦርድ ሕወሓትን እንደገና ላለመመዝገብና ሕጋዊ ዕውቅና ላለመስጠት ያሳለፈው ውሳኔ፣ ትክክል ያልሆነና ፖለቲካዊ መሆኑን ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡ ጉዳዩ በቅርቡ በንግግር ዕልባት ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ አንድ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሥር የማኅበራዊ ልማት ሽግግር ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ክንደያ ገብረ ሕይወት (ፕሮፌሰር)፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከምርጫ ቦርድ ጋር ቴክኒካዊ ንግግር የሚያደርግበት ምክንያት የለም ብለዋል፡፡ ከዚያ ይልቅ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ስለሆነ ከመንግሥት ጋር በተጀመረው ፖለቲካዊ ውይይት እንደሚፈታ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህም ሆኖ ምርጫ ቦርድ የሕወሓትን ዕውቅና አልመልስም ቢል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድና ለመሞገት ወይም እንደ አዲስ ፓርቲ ለመመዝገብ ጥረት ታድርጋላችሁ ወይ ተብለው የተጠየቁት ክንደያ (ፕሮፌሰር)፣ ሁለቱም አማራጮች እንደማይሆኑ ነው የተናገሩት፡፡
‹‹እኛ የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት የተፈራረምነው ከመንግሥት ጋር ነው፡፡ ይህ ጉዳይም የስምምነቱ አንድ አካል ነው፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት ፓርላማው ሕወሓትን ከሽብርተኝነት መዝገብ ሰርዟል፡፡ እኛ ከፓርላማው በታች ከሆነው ከምርጫ ቦርድ ጋር የምንጨቃጨቅበት ምክንያት የለም፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
‹‹ጉዳዩ ፖለቲካ ነውና ከመንግሥት ጋር ንግግር ጀምረንበታል፤›› የሚሉት ክንደያ (ፕሮፌሰር) ‹‹ከመንግሥት ጋር ጥሩ መግባባት ያለን በመሆኑ በቅርቡ ይፈታል ብለን እንጠብቃለን፤›› በማለት ሒደቱ የሚገኝበትን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተጀመረ በሦስተኛ ወሩ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ ነበር፣ ሕወሓትን ከፓርቲ ሕጋዊ ዕውቅና መዝገብ እንዲሰረዝ ማድረጉን ይፋ ያደረገው፡፡ ይህ የቦርዱ ውሳኔ ከፓርቲው ዕውቅና መሰረዝ በተጨማሪ፣ አመራሮቹ በዚህ ስም መንቀሳቀስ እንደማይችሉና የፓርቲው ንብረቶችም ለዕዳ መክፈያ፣ ለሥነ ዜጋና መራጮች ትምህርት እንዲውሉ ያደረገም እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተደመደመ በኋላ፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ሕወሓት ህልውናዬ ይመለስ የሚል ጥያቄ ለቦርዱ አቅርቦ ነበር፡፡ ሕወሓት ላቀረበው የህልውና ይመለስልኝ ጥያቄ ግን ቦርዱ ይሁንታ እንደማይሰጥ በማስታወቅ፣ ዕውቅናውን የከለከለበትን መነሻም ይፋ ማደረጉ አይዘነጋም፡፡
ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ሕወሓት ኃይልን መሠረት ካደረገ የአመፅ ተግባር ቢቆጠብም፣ ነገር ግን በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 98/1/ረ መሠረት እንደገና ሕጋዊ ሰውነቱን ለመመለስ የሚያስችል ድንጋጌ የሌለ በመሆኑ፣ የሕወሓትን ዕውቅና ለመመለስ እንደማይችል ቦርዱ አስታውቆ ነበር፡፡ ቦርዱ በዚህ ምላሽ ለሕወሓት እንደገና ዕውቅና የምሰጥበት የአዋጅ መሠረት የለም ከማለት በተጨማሪ፣ የአመራሮቹን መንቀሳቀስም ሆነ የንብረት ጥያቄ እንዳልተቀበለው ይፋ አድርጓል፡፡ አመራሮቹ እንዳይንቀሳቀሱና ንብረቶቹ እንዲከፋፈሉ የሚሉ ውሳኔዎች፣ ከፓርቲው ህልውና መሰረዝ ጋር በቀጥታ የተገናኙ መሆናቸውን ነው ቦርዱ ያመለከተው፡፡
ሕወሓት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በመቃወም ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡ የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ከመንግሥት ጋር ተደራድሮ የፈረመው ሕወሓት እንደሆነና ስምምነቱን የመተግበር ኃላፊነትም ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቻ የሚተው እንዳልሆነ አሰታውቀው ነበር።
‹‹የሁሉም ነገር መነሻ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ነው። የስምምነቱ ፈራሚ ደግሞ ሕወሓት ነው። በመሆኑም ሕወሓት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሁሉንም የሚያፈርስ ነው። የስምምነቱ ትግበራንም የሚያስር ነው፤›› በማለት የተናገሩት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በመቃወም ለፌዴራል መንግሥትና ለአፍሪካ ኅብረት ቅሬታ ማቅረባቸውን ተናግረው ነበር።
አሁን ግን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት በዚሁ ጉዳይ ከመንግሥት ጋር ንግግር መጀመሩን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ጉዳዩ በቅርቡ ዕልባት እንደሚያገኝ ነው ተስፋቸውን የገለጹት፡፡ የሕወሓት ዕውቅና መነፈግ ጉዳይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ውዝግብ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡ ዕውቅና መነፈጉ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ገለል ለማድረግ ታስቦ ብቻ ሳይሆን፣ ለረዥም ዓመታት ያከማቸውን ንብረትና ሀብትም ለመውረስ ታስቦ ነው የሚል መላምት ከሕወሓት ደጋፊዎች በኩል ሲሰማ ነበር፡፡