June 26, 2023 – EthiopianReporter.com

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳና የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በባህር ዳር ከተማ የተደረገውን ውይይት በጋራ ሲመሩ

ፖለቲካ

ሲሳይ ሳህሉ

June 25, 2023

የትግራይና የአማራ ክልሎች ሕዝቦች በባህል፣ በሃይማኖት፣ አገርን በጋራ ከጠላት በመከላከልና በመገንባት የረዥም ጊዜ የቆየ ታሪክ ባለቤቶች መሆናቸው በስፋት ይነገራል፡፡ የሁለቱ ሕዝቦች ክልሎች ሕዝቦች አብሮነት ታሪካዊ መሆኑ ቢነገርም፣ በፖለቲካ ልሂቃን የሥልጣን ሽኩቻ የተነሳ ጉርብትናው እንደታሰበው መሆኑ ቀርቶ ለሁለት ዓመታት የለየለት ጦርነት ውስጥ ተገብቶ የከፋ የሕይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደልና ከፍተኛ የሀብት ውድመት ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደሚባለው የሁለቱ ክልል ሕዝቦች በመካከላቸው የከፋ የሚባል ምንም ዓይነት ፀብና ቂም የላቸውም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ልዩነታቸው እየሰፋ የመጣ ሲሆን፣ ለሁለቱም ክልሎች ሕዝቦች ትልቁ ቁርሾ እየሆኑ ያሉት የወልቃይትና የራያ አካባቢዎቸ የወሰን፣ የማንነትና የይገባኛል ጥያቄዎች ናችው፡፡

በቅርቡ የተጀመረው የአማራና የትግራይ ክልሎች መቀራረብ ተስፋና ሥጋት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የአማራ ክልል ባለሥልጣናት

ለሁለት ዓመታት የዘለቀውና የአፋር ክልልን ጨምሮ ሁለቱን ክልሎች ያደቀቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ፣ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ሰላማዊ አየር እየነፈሰ ቢመስልም፣ የሁለቱ ክልሎች ይህ የዋለ ያደረ የይገባኛል ጥያቄ አሁንም በቀጣይ የሚታሰበውን ሰላም ጥላ እያጠላበት ነው፡፡ በዚህም  የተነሳ የፌደራል መንግሥት ሁለቱን ክልሎች የሚያማክል ሕጋዊ መንገድ እንዲፈታ ካላደረገና ችግሩ በሕግ መቋጫ እንዲያገኝ ካልተደረገ፣ ሌላ ዙር ጦርነት ላለመከሰቱ ዋስትና አለመኖሩ ብዙዎችን ያስማማል፡፡

በቅርቡ የተጀመረው የአማራና የትግራይ ክልሎች መቀራረብ ተስፋና ሥጋት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያችው ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ጨምሮ በርካቶች ሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው ቦታዎች፣ በሕገ መንግሥቱና ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት መፍትሔ ያገኛሉ ቢሉም፣ ጉዳዩን በሕገ መንግሥት ለመፍታት የተያዘው ዕቅድ በራሱ ጊዜ የሚወስድ መሆኑንና ችግሩ በፍጥነት ዕልባት እንዲያገኝ ግፊቶች እየተደረጉ ነው፡፡ በእርግጥ የሁለቱን ክልሎች ወደ ሰላም የመምጣት ጉዳይ በተለይም በአዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች የሚፈልጉትን ያህል ማንም የሰላምን ዋጋ መረዳት አለመቻሉ ይነገራል፡፡

አቶ አብርሃ ጎበዛይ ከአላማጣ ከተማ ወደ አዲስ አበባ የመጣው በጥር 2015 ዓ.ም. ነበር፡፡ አቶ አብርሃ በ30ዎቹ የዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ የመጣው የሰሜን ኢትዮያ ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መገታቱን ተከትሎ ነው፡፡ ከእናቱ ጋር ከሚኖርበት አካባቢ ግማሹን  በእግሩ ግማሹን በመኪና እያቆራረጠ በአራት ቀናት አዲስ አበባ እንደደረሱ ይናገራል፡፡ ‹‹አዲስ አበባ ለመምጣት ምንም አሳማኝ ምክንያት አልነበረኝም፤›› ይላል፣ ‹‹ተገድጄ የመጣሁት እባብ ያየ በልጥ ይደነብራል እንደሚባለው፣ ለሁለት ዓመት የዘለቀው ጦርነት ዳግም ይከስት ይሆናል የሚል ሥጋት አድሮብኝ፤›› ነው ሲልም ያክላል፡፡ በ60ዎቹ መጨረሻ ዕድሜ ላይ ከሚገኙት እናቱ ጋር  ለሁለት ዓመታት ያሳለፈው ሕይወት  የሰቀቀን ጊዜ እንደነበር ይናገራል፡፡

እናቱ አሁን በደቡብ ወሎ ሐይቅ ከተማ ከሚኖሩት አባቱ ጋር ሲለያዩ ለእናቱ የደረሳቸውን የእርሻ መሬት እያረሰ ይኖር እንደነበረ የሚናገረው አብርሃ፣ በጦርነቱ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ምንም ዓይነት ሰብል ማግኘት ባለመቻሉ አዲስ አበባ መጥቶ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የቀን ሠራተኛ የሚፈልጉ ሰዎችን ለማግኘት ማልዶ እንደሚወጣ፣ ነገር ግን የሚገኘው ገንዘብ እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ ተመልሶ እናቱ ጋ መሄድ እንደሚፈልግ በትካዜ ይናገራል።

‹‹እናቴ ቤት ሄጄ ቢያንስ ሰላም ከሆነ እርሻው ባይደርስ የጓሮ አትክልት አለማለሁ፡፡ ዋናው ግን አሁን ሄጄ ሰላም ማግኘትና ከእናቴ ጋር በሰላም መኖር ነው የምፈልገው፡፡ አዲስ አበባ ለእኔ አትሆነኝም፤›› ብሏል፡፡ ‹‹ባለፈው ሳምንት ፖለቲከኞቹ ተነጋግረዋል፣ ቢሰምርልን ጥሩ ተስፋ ነበር፤›› ይላል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሰል ታሪኮችን መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ከሰሞኑ  የሁለቱ ክልሎችን የሰላም ተስፋ ካጫሩት ክስተቶች ውስጥ የአማራና የትግራይ ክልሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በአካል ተገናኝተው መነጋገራቸው ነበር።

ከሁለት ሳምንት በፊት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የተመራ የትግራይ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በባህር ዳር ከተማ ከአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ከፍያለው ይልቃል (ዶ/ር)፣ ከክልሉ አመራሮችና ከሕዝቡ ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ከሁለት ዓመታት የከፋ ጦርነት ማግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው የመከሩት የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች፣ የሁለቱን ክልሎች ሕዝብ የበፊትና ቀጣይ ዕጣ ፈንታን የተመለከቱ ንግግሮች ማድረጋቸው በበርካታ የመንግሥት ሚዲያዎቸ ታይቶ ነበር፡፡

በዚህ መድረክ አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ፈለግንም አልፈለግንም በጉርብትና መኖራችን ስለማይቀር ይህ ጉርብትና ደግሞ የወንድማማችነት፣ የፍቅርና የመልካም ጉርብትና መሆን አለበት›› በሚል ዕሳቤ ወደ ባህር ዳር ማቅናታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹አንዱ ወደ ሌላው ክልል ሲሄድ የባዕድነት ስሜት ሳይሆን የወንድማማችነት ስሜት እንዲፈጠር አበክረን እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ይልቃል (ዶ/ር)፣ የትግራይ ሕዝብ ለአማራ ሕዝብ ወንድሙ፣ ጎረቤቱ፣ የተጋባና የተዋለደ መሆኑን በመጥቀሰ የማይለያይ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹አብሮ ለሺሕ ዘመናት እንደኖረው ሁሉ ወደፊትም አብሮ በሰላም ይኖራል፣ ለዚህ ምቹ ሁኔታ ደግሞ አሁን ያለነው አመራሮች በኃላፊነትና በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅብናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ልዩነቶች ይኖራሉ፣ ያሉትን ልዩነቶች ግን በሕግ፣ በሰላምና በመነጋገር መፍታት የአማራ ሕዝብ ፍላጎት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ሊቀመንበርና  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ የሁለቱ ሕዝቦች ዘላቂ ሰላም ማምጣትን በተመለከተ ሪፖርተር ላነሳላቸው ጥያቄ ሲያብራሩ፣ ‹‹ሁለቱ ሕዝቦች የሚናገሩት ቋንቋ አማርኛና ትግርኛ ሆነ እንጂ፣ በመሠረቱ ወደኋላ መለስ ብለህ ያለውን ታሪክ ካየህ ሁለቱም የግዕዝ ልጆች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ግዕዝ አማርኛና ትግርኛ ሆኖ ሲመጣ ሁለት መሰሉ እንጂ፣ ከጅምሩ አንድ ሕዝብ አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ነበሩ፡፡ በሒደት ግን የተለያዩ ገዥዎች አንድ የነበረውን ሕዝብ ሁለት ዓይነት በማድረግ ከፋፍለው በመተረክ አላስፈላጊ ልዩነት ፈጥረውበታል፤›› ይላሉ፡፡

አረጋዊ (ዶ/ር) መሪዎች የግል ጥቅማቸውን ለማስፋት ሲሉ የሆነ ያልሆነውን ትርክት እያስፋፉ ጥላቻ እንዲፈጠር ስለማድረጋቸው ያስረዳሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን ፖለቲከኞችና መሪዎች፣ አዋቂ ነን የሚሉ ሰዎች ለራሳቸው ሲሉ የሚያደርጉት መገፋፋት እንጂ ሕዝቡ በጥላቻ ዓይን አይተያይም ብለዋል፡፡ ለዚህም ማሳያ ብለው የጠቀሱት አንድ ቦታን ‹‹ጠገዴ›› እና ‹‹ፀገዴ›› በሚል የተፈጠረውን የስም ልዩነት ለማስታረቅ፣ ‹‹ከአማራ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከትግራይ አቶ ዓባይ ወልዱ ወደተባለው አካባቢ ሕዝቡን እናስታርቅ በሚል ሕዝቡን ለስብሰባ ሲጠሩ፣ ሕዝቡ እኛ መቼ ተጣላን እናንተው ታረቁ ብሎ እንደመለሳቸው አስታውሳለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የሚጣሉትም በግልጽ የሚታወቁት ፖለቲከኞቹ ናቸው፡፡ ሕዝቡ እኮ ፖለቲካውን ራቅ ብሎ የሚመለከት እንጂ የሚያጣላ ነገር የለውም፣ ይህ በግልጽ የሚታይ ነገር ነው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም በሁለቱ ሕዝቦች መካከል አንድነት እንጂ ምንም የሚያጣላ መሠረታዊ የሆነ ችግር እንደሌለ በመጥቀስ፣ ምናልባት ሕዝቦቹ የአስተዳደር ብልሹነት የፈጠረው ችግርና ጥያቄ ካለ በመመካከር፣ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ሕዝበ ውሳኔ እስከ ማካሄድ የሚደርስ ዕርምጃ ድረስ መሄድ እንደሚያስፈልግ፣ በዚህ ዓይነቱ መንገድ የሚያምን ፖለቲከኛና መሪ እንደሚያስፈልግ አረጋዊ (ዶ/ር) ያብራራሉ፡፡

‹‹ስለዚህ ሕዝብ ለሕዝብ ቁጭ ብሎ ከተነጋገረ ሕዝቡ የራሱ የሆነ የዕርቅ መንገድ አለው፡፡ ችግሩን ሕዝቡ እንዲፈታው መደረግ ይኖርበታል፣ ካሳም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ መካካስም ያስፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡

ሪፖርተር ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረበላቸው የቀድሞ የብአዴን ከፍተኛ አመራር የነበሩትና የአማራ ፖለቲካን በመተንተን የሚታውቁተ አቶ ቹቹ አለባቸው፣ ‹‹ሁለቱ ክልሎች ከሰሞኑ የፈጠሩት መቀራረብ ዘገየ ካልተባለ በስተቀር፣ ከማንም በላይ የጉዳዩ ሰለባ የነበሩት ሁለቱ ክልሎች በራሳቸው ተነሳሽነትም ይሁን በሌላ ኃይል ጫና ቀድመው መነጋገርና መምከር ነበረባቸው፤›› ይላሉ፡፡ ከኦሮሚያና ከትግራይ ክልሎች ይልቅ የትግራይና የአማራ ክልሎች ተቀራራቢ ነበሩ ይላሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ዘግይቶም ቢሆን ለሁለቱ ሕዝቦች ሌላ ምርጫ ስለሌለ መቀራረቡና መነጋገሩ ጥሩና በጎ ጅምር ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል ብለዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ይህ መቀራረብ በሌሎች አካላት ግፊት ነው ወይስ ከልብ? የሁለቱ አካላት ተነሳሽነት ነው የሚለው ጉዳይ ብዙ አሳሳቢ ነገር አለው፤›› ሲሉም ሥጋታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹በተለይ ሥልጣን ላይ ያሉት አመራሮች በእውነት መቀራረብን የመጨረሻ መፍትሔ አድርገው ወስደው ከልብ ለመነጋገርና ለመቀራረብ ነው? ወይስ በስተጀርባ ሌላ ነገር አስቀምጦ ለመቅረብ የሚደረግ የሚለው ጥያቄ አጭሮብኛል፤›› ያሉት  አቶ ቹቹ፣ በአጠቃላይ የመቀራረቡ ነገር በጣም ዘግይቶ የመጣ ቢሆንም፣ የሁለቱ ክልሎች መሠረታዊ ችግር ምንድነው የሚለውን ቁጭ ብሎ መነጋገርና መግባባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ለመፍጠር በአማራና በትግራይ ክልሎች ምሁራን መካከል ያለው ጫፍ የረገጠ ዕይታ ግን ቀላል ይሆናል ብዬ አልገምትም፤›› የሚሉት አቶ ቹቹ፣ በመተማመን ላይ ያልተመሠረተ ግንኙነት ዳግም ሌላ ፀብ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡  በመሆኑም ጅምሩ በጎና ወደ ዋና መስመር ለማስገባት የተጀመረው መንደርደሪያ በጣም ጥሩ ጅማሮ ቢሆንም፣ መግባባት ላይ ለመድረስ ትልቅ መሰናክል ይገጥመዋል የሚል ሥጋት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

ሁለቱ ክልሎች የሚጋጩባቸውን ጉዳዮች ለመፍታት የፌዴራል መንግሥት ፍትሕን ለማስፈን ቁርጠኛ ከሆነ፣ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ለተበደለ ፍትሕን ማስፈን ያስፈልጋል የሚል እምነት ይዞ ወደ ሥራ መግባት እንዳለበት የሚያብራሩት አቶ ቹቹ፣ ነገር ግን መንግሥት ይህን ትቶ ዥዋዥዌ የሚያጫውት ከሆነ አንዳቸው በተመቻቸው ቀን ወደ ጦርነት የማይገቡበት ምክንያት ዓይታየኝም ብለዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ፍትሕ ለማምጣት የሕዝቦች ጩኸት መደመጥ እንዳለበትና እውነተኛ የትግራይና የአማራ ሕዝቦች መቀራረብ ከተፈለገ፣ እንቅፋት የሆኑ የወሰን ጥያቄዎች በሕግና በሥርዓት መፈታት አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ ይህን ለማስፈጸም ደግሞ ከሁለቱ ክልሎች በላይ የፌዴራል መንግሥት ትልቅ አቅም አለው ሲሉም አክለዋል፡፡

 የፌዴራል መንግሥት በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ሰላም እንዲያመራ ሕግን መሠረት ያደረገ ዕርምጃ ከወሰደ፣ ሁሉም አካል በሕግ መገዛት ስላለበት ሕጋዊ መፍትሔ በመስጠት ጦርነትን ማስቀረት እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡ ትክክለኛ ፍትሕ ሲሰፍን ሁለቱ ሕዝቦች በሰላም፣ በወንድማማችነት፣ በእህትማማችነትና በጉርብትና ሰላማዊ ኑሮዋቸውን ይቀጥላሉ በማለት አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ ካልገባ ሁለቱ ሕዝቦች ወደ ጦርነት መግባታቸው እንደማይቀር፣ ነገር ግን ሌላ ዙር ጦርነቶች ውስጥ ቢገባ ችግሩ በመጨረሻ የሚፈታው በሰላማዊ ድርድር ነው ይላሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ተሞክሮውም ግጭቶች ሔደው ሔደው መዳረሻችው የሰላም ድርድር በመሆኑ፣ ሁለቱም ክልሎች ተገቢ የሆኑና መጠየቅ ያለባቸውን ጉዳዮች በሥርዓቱ በማንሳት ችግሩ ከፖለቲካ ንክኪ በፀዱ ምሁራን ተቃኝቶ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህ መንገድ ሕዝቡም ፍትሕ ሊያገኝና በተቻለ መጠን ወደ ዳግም ጦርነት የማይገባበት መንገድ በመቀየስ፣ ሁለቱ ሕዝቦች ለዚች አገር ግንባታ በአብሮነት የተጫወቱትን ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም የሚጠበቅበትን በሀቅና በእውነት ላይ የተመሠረተ ምክክርና ንግግር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሁለቱ ሕዝቦች ከሚለያዩዋቸው ችግሮች ይልቅ የሚያቀራርቧቸው፣ ለበርካታ  ዘመናት ይዘዋቸው የተሻገሩ የጋራ እሴቶችና ባህሎችን የሚጋሩ ከመሆናቸውም በላይ ላላቸው ጉርብትናና የተሻለ ሰላም፣ ከማንም በላይ ራሳቸው ቁጭ ብለው ካልመከሩ የሁለቱ ፍትጊያ ራሳቸውን ከማመሳቀል አልፎ ለአገር የሚያመጣው ዳፋ ከባድ እንደሆነ ብዙዎችን ያስማማል። 

በመሆኑም ለዚህ የሚበጀውና መፍትሔ የሚሆነው የፌዴራል መንግሥቱ  ከፖለቲካ የፀዳ ጥረት፣ የክልሎች ፍላጎት መኖር፣ ነገር ቆስቋሽ ፖለቲከኞች ለሕዝብ ሲሉ ከድርጊታቸው መቆጠባቸውና ግልጽ የሆነ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ማካሄድ ቀዳሚ የማድረግ አስፈላጊነትም የብዙዎች ዕሳቤ ነው፡፡