June 27, 2023
በአማኑኤል ይልቃል
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “አስተባባሪነት” የሚሰሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ “በግልጽ ጥያቄ” የሚቀርብ ከሆነ ኦዲት ለማድረግ “ዝግጁ” መሆኑን የፌደራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ። የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ይህንን ያለው ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 20፤ 2015 በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው።
በዚህ የፓርላማ ውሎ ላይ የፌደራል ዋና ኦዲተር፤ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን የ2014 በጀት ዓመት የፋይናንስ ህጋዊነት እና ክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን አቅርቧል። ሃምሳ ዘጠኝ ገጾች ያሉትን የመስሪያ ቤቱን ሪፖርት በንባብ ያቀረቡት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ፤ ከመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
ዋና ኦዲተሯ ከምክር ቤት አባላት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “አስተባባሪነት” የሚሰሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ኦዲት ከማድረግ ጋር የተያያዘው ይገኝበታል። ይህ ጥያቄ የቀረበው አቶ ሙሉቀን አሰፋ ከተባሉ የምክር ቤቱ አባል ነው።
የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል የሆኑት አቶ ሙሉቀን፤ የእነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች “የገንዘብ አሰባሰብ እና አወጣጥ” የመንግስትን የፋይናንስ አዋጅ፣ ደንብ እና መመሪያ ተከትሎ እየተፈጸመ ስለመሆኑ የፌደራል ዋና መስሪያ ቤት የኦዲት ስራ አከናውኖ ከሆነ ግኝቱ እንዲገለጽ ጠይቀዋል። አቶ ሙሉቀን አስከትለውም፤ “ኦዲት ካላደረጋችሁ ደግሞ ኦዲት ላለማድረግ ምክንያታችሁ ምንድነው?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል።
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ወ/ሮ መሰረት፤ የሚመሩት ተቋም በእነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ የኦዲት ስራ አለማከናወኑን አስታውቀዋል። የመስሪያ ቤቱ “የመጀመሪያ ተግባር እና ኃላፊነት” በተወካዮች ምክር ቤት “የጸደቀውን በጀት ኦዲት ማድረግ” መሆኑን ዋና ኦዲተሯ አስረድተዋል። “በተጨማሪ ደግሞ የመንግስት ተቋማትም ይሁን የልማት ድርጅቶች በአዋጅ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት፤ አዋጃቸውን መሰረት አድርገን የክዋኔ ኦዲት እናደርጋለን” ሲሉ የሚመሩትን ተቋም ተጨማሪ ኃላፊነት ጠቅሰዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር በዚህ መልኩ በተሰጠው “ስልጣን እና ኃላፊነት” መሰረት ሪፖርት እንደሚያቀርብ የገለጹት ወ/ሮ መሰረት፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ “አስተባባሪነት” ይሰራሉ የተባሉት ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ግን “በግልጽ ጥያቄ” የሚቀርብ ከሆነ ተቋሙ ኦዲት ለማድረግ “ዝግጁ” መሆኑን ለምክር ቤቱ አባላት አስታውቀዋል።
“እነዚህን ፕሮጀክቶች በተመለከተ የተመዘበረ ነገር ካለ፣ የጠፋ ነገር ካለ፣ ምንጩ ከየት እንደሆነ ካለ፤ ጥያቄው በግልጽ ይቅረብልን። ለማየት ዝግጁ ነን። ከኦዲት exempt የሚደረግ ስለሌለ” ሲሉም ዋና አዲተሯ ምላሽ ሰጥተዋል። የሜጋ ፕሮጀክቶቹ ኦዲት እንዲደረጉ ጥያቄ ሲቀርብም “እነዚህ ፕሮጀክቶች፣ ይሄንን ይሄንን ያህል በጀት አለ፣ ይሄንን ያህል ጎድሏል” የሚለው “በግልጽ እንዲቀርብ” ወ/ሮ መሰረት ጠይቀዋል። (
ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)