

June 28, 2023
ከአንድ ወር ቀደም ብሎ በደቡብ አፍሪካ ተካሂዶ በነበረው የፓን አፍሪካ ፓርላማ ሦስተኛው የአየር ንብረት ፖሊሲና ፍትሕ ስብሰባ ላይ የኬንያ ፕሬዚዳንት ያደረጉት ንግግር አስደናቂ ነበር፡፡
‹‹የአፍሪካ አጋሮች ብዙ ኢኒሼቲቭ አላቸው፡፡ የቻይና አፍሪካ ምክክር፣ የሩሲያ አፍሪካ ምክክር፣ የአሜሪካ አፍሪካ ጉባዔ፣ ወዘተ የሚሉ የትብብር ስብሰባዎች ላይ እንድንካፈል ይጠሩናል፡፡ አፍሪካዊያን በእንዲህ ያለው ስብሰባ ላይ ራሳችንን አደራጅተን ለመካፈል ተስማምተናል፣ ሕግም አበጅተናል፡፡ የኅብረቱ ሊቀመንበር፣ ኮሚሽነር፣ የአኅጉሩ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሪ በአጠቃላይ ከስድስትና ከሰባት ያልበለጡ ትሮይካ በሚል የሚጠሩት ወኪሎቻችን እንዲካፈሉ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ጋባዦቻችን ስብሰባ ሲጠሩን ከ50 ያላነሱ የአኅጉሩ መሪዎች እንዲመጡ ይፈልጋሉ፡፡ መሪዎቹ ካልመጡ አፀፋ እንዳለውም አጣቅሰው ነው መጥሪያ የሚልኩት፡፡ ነገር ግን 50 የአፍሪካ መሪ ተሰብስቦ ምን ሊፈጥር ይችላል? ተሠልፎ ፎቶግራፍ ከመነሳት በስተቀር የረባና ውጤታማ ውይይት ሳናደርግ ነው ተሰብስበን የምንመለሰው፡፡ ከስድስት ባልበለጡ ሰዎች በአኅጉራችን ችግር ላይ ጥልቅ ውይይት ማድረግ እየፈለግን፣ ነገር ግን ከ50 በላይ መሪዎች እየተጠራን ፎቶ ተነስተንና እራት ተጋብዘን ብቻ እንመለሳለን፡፡
‹‹እኛ አሁንም ቢሆን አጋሮቻችን እስኪያደምጡን ድረስ እንጮሃለን፡፡ በመጪው ወር ፓሪስ ጋብዘውናል፣ እዚያም ተገኝተን እንጮሃለን፡፡ መስከረም ላይ በናይሮቢ ኬንያ የአየር ንብረት ጉባዔ አለ፣ እዚያም ላይ እንጮሃለን፡፡ አፍሪካዊ መፍትሔያችንን እስኪቀበሉትና አፍሪካን እንደ አንድ አጋር እስኪያዩ ድረስ እንጮሃለን፡፡ አጋሮቻችን በጠሩን ቁጥር እየተገኘን ድምፅ ማሰማታችንን እንቀጥላለን፡፡ መደበቂያና መሸሸጊያ እስኪያጡ ድረስ እየተከታተልን እንጮህባቸዋለን፡፡ ሰብሰባውንም ሆነ ጥሪያቸውን እስኪተው ድረስ እንጮሃለን፣ እንረብሻቸዋለን፡፡ በእነሱ ስብሰባና የእራት ግብዣ ላይ ካልተገኘን ለእራት ከሚቀርበው ምግባቸው አንዱ እንደምንሆን አሳምረን እናውቃለን፡፡ በስብሰባቸው እከተገኘን ድረስ ግን የእኛን የጠራ አቋምና ፍላጎት በሚገባቸው መንገድ እንነግራቸዋለን፤›› በማለት ነበር የኬንያ ፕሬዚዳንት የተናገሩት፡፡
በደቡብ አፍሪካ ይህን ንግግር ሲያሰሙ ታላቅ ጭብጨባ የተከተላቸው ዊሊያም ሩቶ፣ ከወር በኋላ በፓሪስ በተደረገው ጉባዔ ላይም ተገኝተው ዓለምን የመሰጠ ንግግር አድርገዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ‹‹እንጮሃለን›› ሲሉ እንደፎከሩትም በፓሪሱ ‹‹አዲስ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ሥርዓት የመሪዎች ጉባዔ›› (Summit for a New Global Financial Pact) ላይ ተገኝተውም፣ የአፍሪካን ጩኸት ከፍ አድርገው አሰምተዋል፡፡
ዊሊያም ሩቶ ባረጀና ባፈጀ የዓለም የፋይናንስ ሥርዓት አፍሪካ መቀጠል እንደማትችል አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የዓለም ፋይናንስ ሥርዓት የምዕራቡን ዓለም ፍላጎት በሚያስጠብቅና የበለፀጉ አገሮችን በሚጠቅም መንገድ የተገነባ መሆኑን ያመለከቱት ሩቶ ይህ ሥርዓት እንዲቀየር በይፋ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹አፍሪካዊያን ውሳኔ ሰጪነታችንና ተሰሚነታችን ካላደገ በስተቀር በዚህ መሰሉ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት መቀጠል እንቸገራለን፤›› ሲሉ የተደመጡት ሩቶ፣ በዕዳ ጫና ደሃ የአፍሪካ አገሮች ከመንኮታኮታቸው በፊት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስቸኳይ የለውጥ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት ሲያሳስቡ ተደምጠዋል፡፡
ይህን የሚጋራ አስተያየት የሰጡት የምጣኔ ሀብት አማካሪው አቶ ጌታቸው ተክለ ማሪያም፣ ‹‹ምዕራቡ ዓለም አፍሪካዊያን በሁለት መንገዶች እየተቀየሩ መምጣታቸው የገባው ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አፍሪካዊያን በእስከ ዛሬው የዓለም ፋይናንስ ሥርዓት መቀጠል እንደማይችሉ የገባቸው ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው አፍሪካዊያን በብዙ ጉዳዮች ያላቸውን የተሻለ ተፎካካሪነት (ኮምፓራቲቭ አድቫንቴጅ) በደንብ እየገባቸው መጥቷል፡፡ የዛምቢያው መሪ ሲናገሩ ከዚህ በኋላ እሴት ያልተጨመረባቸው ጥሬ ዕቃዎችን ብቻ እየላክን አንቀጥልም ብለዋል፤›› በማለት ነው ያስረዱት፡፡
የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በደገሱትና ከ40 በላይ የዓለም መሪዎች የታደሙበት የፓሪሱ ጉባዔ ዊሊያም ሩቶን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጭምር፣ ስለአፍሪካ አገሮች ችግር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የጮሁበት ስብሰባ ነበር፡፡ ስብሰባው የዓለም ፋይናንስ ድርጅቶች፣ አበዳሪዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የተለያዩ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት የታደሙበት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ስብሰባ ነበር፡፡
በማዕከላዊ ፓሪስ የተገነባው የዓለም አቀፍ ድርሻ ግብይት ይካሄድበት የነበረው ‹የፓሌስ ብሮግኒአርት› ሕንፃ ለሁለት ቀናት በ1,500 ታላላቅ ዓለም አቀፍ እንግዶች ጢም ብሎ ታይቷል፡፡ ምናልባትም የሩሲያው የጦር ድርጅት ዋግነር መሪና ወታደሮቹ አመፅ ጉዳይ የዓለም መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ባይቆጣጠረው ኖሮ፣ የፓሪሱ ጉባዔ የዓለምን ገጽታ ሊቀይሩ የሚችሉ እጅግ ጠንካራ ሐሳቦች የተነሳበት ታላቅ ስብሰባ በተባለ ነበር፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ መሪዎች ዕዳ ይቃለልልን ሲሉ ሞግተዋል፡፡ በዓለም የፋይናንስ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ድምፃችን ይሰማ የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በጥቅሉ ‹‹ግሎባል ሳውዝ›› በመባል የሚታወቁት በደቡባዊ የዓለም ክፍል የሚገኙ አዳጊ አገሮች የዕዳ ሸክም መቃለል ጉዳይ፣ ዋናውና ቅድሚያ የሚሰጡት አጀንዳ መሆኑ በዚህ ጉባዔ ጎልቶ ነው የታየው፡፡
የፈረንሣይ መሪ ኢማኑኤል ማክሮን፣ የአይኤምኤፍ መሪ ክሪስቲና ጆርጊቫ፣ እንዲሁም የዓለም ባንክ መሪ አጄይ ባንጋም ሆኑ የአሜሪካ ገንዘብ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ጃኔት ዬለን የአፍሪካዊያንን ሐሳብ የደገፈ አስተያየት አስተጋብተዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል ምዕራባዊያኑ የአፍሪካዊያንን የዓለም ፋይናንስ ሥርዓት ይሻሻል ጥያቄ እየተቀበሉ መጥተዋል የሚል ግምት ስብሰባው ያሳደረው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት አቶ ጌታቸው ግን ይህን አይጋሩትም፡፡ ‹‹በአፍሪካ ደረጃ የሚሠራው የፋይናንስ ሥርዓት ግልጽነት ተቋም ኃላፊ ሆኜ እንደ መሥራቴ ብዙ ነገሮችን በቅርበት ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ በሚዲያ የሚራገበውና ውስጥ ውስጡን የሚሠራው ነገር አንድ አለመሆኑን እረዳለሁ፡፡ ምዕራቡ ዓለም ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲሻሻልና እንደ አይኤምኤፍ ያሉ ተቋማት ሪፎርም እንዲደረጉ ፍላጎት አለው የሚለውን ጉዳይ እጠራጠራለሁ፡፡ ለአድቮኬሲ ብቻ እንደሚባለው እንደማይሠራ አውቃለሁ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ አገሮች በፊት አማራጭ ነበራቸው፡፡ በቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ቻይና ደክማለች፣ ለውጭ አገሮች በገፍ የምትበትነው ብድርና ድጋፍ የለም፡፡ እሱ መጥበቡ ለታዳጊ አገሮች ፈተና ሆኗል፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፣ አፍሪካዊያን በምዕራባዊያን ላይ የብድር ሽግሽግ ጥያቄውን ያበረቱት በዚህ መነሻነት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
የቡድን 20 አገሮች በመባል የሚታወቁት ፈጣን የኢኮኖሚ አዳጊ አገሮችና የበለፀጉ አገሮች የተካተቱበት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችና አበዳሪዎች ያሉበት የዓለም ደሃ አገሮችን ዕዳ ሸክም የማቃለል ጥረት በሚፈለገው መንገድ እየሄደ አመሆኑን የፓሪሱ ስብሰባ አመላክቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 በዕዳ ጫና የተነሳ እጅግ ለከፋ ቀውስ ተጋላጭ የነበሩ ታዳጊ አገሮች ቁጥር 30 በመቶ ነበር፡፡ ዛሬ ግን የኮሮና ወረርሽኝና ሌሎችም ችግሮች ባስከተሉት ተፅዕኖ የተነሳ በዕዳ ጫና ለቀውስ ተጋላጭ የሆኑ ታዳጊ አገሮች ወደ 60 በመቶ አሻቅበዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የበለፀጉ አገሮች የዕዳ ምሕረት አልያም የዕዳ ሽግሽግ እንዲያደርጉላቸው ብቻ ሳይሆን፣ ተጨማሪ ብድርና ዕርዳታ እንዲፈቅዱላቸው የሚጠይቁ ደሃ አገሮች እየተበራከቱ ነው፡፡ ከአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ቻድና ዛምቢያ በጂ20 ማዕቀፍ መሠረት የዕዳ ሽግሽግ በመጠየቅ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ እስካሁን በተደረጉ ጥረቶች ግን የሁለቱ ማለትም የቻድና የዛምቢያ ዕዳ ሽግሽግ ብቻ የተፈቀደ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ መቼ ዕድሉን እንደምታገኝ የታወቀ ነገር የለም፡፡
አቶ ጌታቸው እንደሚናገሩት፣ የቡድን 20 ማዕቀፍን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አሠራሮች ጉድለቶች ለታዳጊ አገሮች ዕዳ መሸጋሸግ እንቅፋት ያለባቸው ናቸው ይላሉ፡፡ ቡድን 20 ማዕቀፍ ሲመጣ ከፍተኛ የብድር ምንጭ የሆኑ የግል አበዳሪዎችን ያላካተተ መሆኑ አንዱ ችግር መሆኑን ያወሳሉ፡፡ ሥራው በጥቅሉ ለታዳጊ አገሮች ተብሎ የሚሠራ ሳይሆን በተናጠል እያንዳንዱን አገሮች በመፈተሽ የሚካሄድ ነውም ይሉታል፡፡ የአንዳንድ አገሮች ይፈጥናል፣ የሌሎቹ ይዘገያል፡፡ እስካሁን የሦስት አገሮች ብቻ ነው የተሸጋሸገው በማለትም ያክላሉ፡፡
‹‹ሌላው ደግሞ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች እንደ አይኤምኤፍ ያሉት ቴክኒካዊ በሆነ መመዘኛ ነው አገሮቹን የሚፈትሹት፡፡ እንዲሁም በጣም ተጋላጭ የሆኑ አገሮችን በማስቀደም ነው ሽግሽጉን የምንመራው ይላሉ፡፡ ነገር ግን አገሮቹ ለምዕራባዊያኑ ያላቸውን ቀረቤታና የምዕራባዊያኑን ፍላጎት ለማስፈጸም ያላቸውን ፈቃደኝነት ነው የሚፈትሹት፡፡ የኢትዮጵያን መዘግየት ችግር ብናየው ከቻይና የብድር ሁኔታ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ነው ይባላል፡፡ የቻይና ብድር መንግሥታዊና የግል የሆነው ግልጽነት የለውም፡፡ አበዳደሩና አመላለሱ በምን መንገድ እንደተፈጸመ በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ ቅድሚያ ተሰጥቶት የሚከፈል ብድር አለ፣ ዘግይቶ እንዲከፍል ሊደረግ የሚችል ብድር አለ፡፡ ሌላው ቅድሚያ የሚሰጠው አበዳሪ አለ፣ ይዘግይ የሚባል አበዳሪ አለ፡፡ የብድር ዓይነትና የአበዳሪዎች ሁኔታ ቅደም ተከተል ወይም ደረጃ ይወጣለታል፡፡ አበዳሪዎቹ ይህን ለማድረግ ተቸግረዋል፡፡ ‹ቲር› በሚባለው አሠራር ብድርም ሆነ አበዳሪዎች ደረጃ ይሰጣቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአይኤምኤፍ የሚካሄድ የሚታይ ፕሮግራም የላትም፡፡ ችግሮች ወደፊት እንደሚስተካከሉ ማረጋገጫ የሚሰጥ የሪፎርም ፕሮግራም የላትም፡፡ አበዳሪዎች ዛሬ ብናሸጋሽግ ነገ እንደምትከፍለን ምን ማረጋገጫ አለን ይላሉ፡፡ አይኤምኤፍ ይህን ዓይነት ፕሮጀክት ለመጀመር ወደኋላ ሲል ቆይቷል፡፡ ከዚያ ጦርነቱ መጣ፣ የአሜሪካ መንግሥት መጣ፣ በአጠቃላይ ፖለቲካዊ ነው መነሻው፤›› በማለት የቡድን 20 ማዕቀፍ አሠራርን በጥልቀት አብራርተዋል፡፡
የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ሀካዩንዴ ሂቺሌማ አገራቸው ከፓሪሱ ጉባዔ ቀድማ የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ላይ በመድረሷ ደስተኛ ነበሩ፡፡ አገሪቱ ልትከፍለው የነበረው የስድስት ቢሊዮን ዶላር ዕዳ በመሸጋሸጉ ተደስተው ቢታዩም፣ ይሁን እንጂ ሰውየው ሒደቱ የጠየቃቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ ልምድ እንዲሆን በስብሰባው ለሌሎች መሪዎች አካፍለው ነበር፡፡
‹‹እኛ የዕዳ ሽግሽጉ 21 ወራት የፈጀ ጥረት ጠይቆናል፡፡ የቡድን 20 ማዕቀፍ ዕዳ ሽግሽግ ለማግኘት ጥረት ስናደርግ ሒደቱ እጅግ ዘገምተኛና ፈታኝ ሆኖብን ነበር፡፡ ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ተሸጋሽጎልናል፣ ሆኖም ሌሎች የጠየቁ አገሮች አሉና ሒደቱ እኛን ከጠየቀን ባጠረ ጊዜ የማይካሄድ ከሆነ አገሮቹ የሚገጥማቸው ፈተና የከበደ ይሆናል፤›› በማለት ሒደቱ እንዲፋጠን ጠይቀዋል፡፡
ይህን የዛምቢያ መሪ ጥያቄም የኬንያ ፕሬዚዳንት በተመሳሳይ ሁኔታ አጉልተውታል፡፡ ‹‹መፍትሔ የምንፈልገው አሁን ነው፤›› በማለት አገራቸው ኬንያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚገኙበትን የዕዳ አጣብቂኝ ገልጸዋል፡፡
የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክሪስቲና ጂኦርጊቫ፣ ‹‹ከፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ሙሉ ለሙሉ እስማማለሁ፡፡ የደሃ አገሮች ዕዳ ሸክም መቃለል ጉዳይ ከሁሉ ሊቀድም የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን እጋራለሁ፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ በመጀመሪያ ለቻድ ቀጥሎ ደግሞ ለዛምቢያ ዕዳ መሸጋሸጉን የጠቀሱት ኃላፊዋ፣ በጂ 20 ማዕቀፍ መሠረት በሒደት የሌሎች አገሮች ዕዳ ሸክም እንደሚቃለል ቃል ገብተዋል፡፡ ስሪላንካና ሱሪናም በዚህ አሠራር ተጠቅመዋል የሚሉት ክርስቲና ሒደቱ ፍጥነት እንዲኖረው እንደሚፈልጉ አመልክተዋል፡፡ ሴትየዋ ከዚህ በተጨማሪም የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄ ያቀረቡ አገሮች ቢያንስ ሒደቱ እስኪገባደድ፣ በድርድር ወቅት ዕፎይታ እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ለአፍሪካዊያን ይበጃል የሚሉትን ተጨማሪ ሐሳብ ሲያነሱ የሚከተለውን ያስቀምጣሉ፡፡
‹‹አፍሪካዊያን የገንዘብ ምንጫቸውን ማስፋት አለባቸው፡፡ ከፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች ጫና መላቀቅ አለባቸው፡፡ ሌላው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አሠራር እንዲቀየር መሥራትም አለባቸው፡፡ የዓለም አቀፍ አየር ንብረት ፋይናንስን በደንብ መጠቀም የሚያስችል አሠራር አፍሪካዊያን መዘርጋት አለባቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለ የታክስ ማስተካከያ ንቅናቄም አለ፡፡ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 30 ቀን 2022 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጣ ዓለም አቀፍ የታክስ የውሳኔ ሐሳብ አለ፡፡ ይህን መሰል ዕድልም ለመጠቀም መጣር ያስፈልጋል፤›› ብለዋል
የቡድን 20 ማዕቀፍ የተለያዩ የግልና የመንግሥት አበዳሪዎችን ከተበዳሪዎች ጋር ለማቀራረብ አስችሏል ይባላል፡፡ የደሃ አገሮች የዕዳ ሸክም ችግር የፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች፣ ከፓሪስ ክለብ ውጪ እንደ ቻይና፣ ህንድ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ብራዚል ያሉ አበዳሪዎች በአንድነት ተሳባስበው እንዲመክሩበት ያደረገ መሆኑ ይነገራል፡፡ የአይኤምኤፍ ኃላፊም ሆነ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ይህን አጉልተው ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተቀራርቦ ከማውራት በዘለለ የደሃ አገሮች ዕዳ ጉዳይ አጣዳፊ መፍትሔ የሚፈልግ መሆኑ፣ ችግሩ ከዚህ በላይ ትኩረት እንዲሰጥ የሚያስገድድ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡
የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ማክሮን የሁለት ቀናቱ ጉባዔ በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት መሻሻል ጉዳይ ላይ መግባባትን ስለመፍጠሩ ተናግረዋል፡፡ በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ መሠረታዊ ለውጦችን ለማካሄድ የሚያስችል የጋራ ፖለቲካዊ መግባባት የፈጠረ ዝርዝር ሐሳቦችን ያቀፈ አንድ ዶክመንት ለማዘጋጀት መንገድ የጠረገ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ከዓለም አቀፍ መፍትሔዎች ጎን ለጎን የዕዳ ሽግሽግ የጠየቁ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ማድረግ የሚጠበቅባቸውን ጉዳይ ይመክራሉ፡፡
‹‹ዕዳ መክፈሉ የማይቀር ከሆነና ዕዳ ሽግሽግ አይደረግላቸሁም ከተባለ ፈተናችን ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን ዕዳው ቢሸጋሸግልንም እንኳን ለጊዜው እንጂ መተንፈሻ የምናገኘው፣ ዕዳውን መክፈላችን ለሌላ ጊዜ እንደማይቀር ማወቅ አለብን፡፡ ዕዳው ቢሸጋሸግ ትልቅ ዕፎይታ ነው፣ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ነገር ግን የመክፈል ግዴታችን የማይቀር በመሆኑ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ የፋይናንስ ሥርዓት ዝግጅት ያስፈልገናል፡፡ እጅግ ሥነ ምግባር የተከተለ የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት አለብን፡፡ መንግሥት ወጪውን መቆጠብ አለበት፡፡ መንግሥት ያሉ የገቢ ማሳደጊያ አማራጮቸን በሙሉ አሟጦ መጠቀም አለበት፡፡ ውጤታማ/ስማርት የሆነ የፋይናንስ፣ የፕሮጀክት አፈጻጸምና የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ያስፈልገናል፡፡ በአጠቃላይ ደግሞ ለረዥም ጊዜ የሚሆን የተቀናጀ የኢኮኖሚ ሪፎርም ሥራ ያስፈልገናል፡፡ ጦርነቱ፣ ግሽበት፣ ሙስና፣ የገበያ አለመረጋጋት፣ ግጭት በሁሉም አቅጣጫ የኢኮኖሚ ፈተናዎች ያለብን በመሆኑ ለዚህ ሁሉ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የተቀናጀ የኢኮኖሚ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም ያስፈልገናል፤›› በማለት ነው የኢኮኖሚ አማካሪው ሐሳባቸውን ያካፈሉት፡፡
ዓለም አቀፋዊ ለውጦች ላይ በተለይም የኢኮኖሚ ፍትሕ ላይ አተኩሮ የሚሠራው ኦክስፋም የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት፣ እጅግ አስደንጋጭ አኃዞችን የያዘ ነበር፡፡ ድርጅቱ ሀብታም አገሮች ቃል ገብተው ያልከፈሉት ዕርዳታ 13 ትሪሊዮን ዶላር መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1970 ጀምሮ ሀብታም አገሮች የጥቅል ኢኮኖሚያቸውን (የጂዲፒያቸውን) 0.07 በመቶ በዕርዳታ ለመለገስ ቃል ቢገቡም እስካሁን ይህን በትክክል ተግባራዊ አላደረጉም፡፡ ቃል ገብተው ያልከፈሉት የተከማቸ 13 ትሪሊዮን ዶላር የዕርዳታ ገንዘብ እስካሁን እንዳለ ኦክስፋም ይፋ አድርጓል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ ቀውስና ለሰብዓዊ ረድኤት ቀውስ መሸፈኛ ደሃ አገሮች ገንዘብ አጥተው ሀብታሞቹ ይቀማጠላሉ ይላል ድርጅቱ፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ሀብታም አገሮች ለአየር ንብረት አደጋ መቋቋሚያ ለታዳጊ አገሮች 100 ቢሊዮን ዶላር ሊደጉሙ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ ይህን ግብ አላሳኩም ይላል፡፡ የሀብታሞቹ አገሮች በካይ የካርበን ጋዝ ልቀት በመካከለኛና ደሃ አገሮች ወደ 8.7 ትሪሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ኪሳራ አድርሷል በማለት ነው ኦክስፋም አስደንጋጩን አኃዝ ያወጣው፡፡
ኦክስፋም ሪፖርቱን ሲቀጥል ቡድን ሰባት አገሮች በቅርቡ ወደ 21 ቢሊዮን ዶላር ለዓለም ሰብዓዊ ረድኤት ለመስጠት ቃል ቢገቡም፣ ተመድ ግን 55 ቢሊዮን ዶላር ነበር ለዚህ የጠየቀው ይላል፡፡ የታዳጊ አገሮች መሠረተ ልማትን ችግር ለመደጎም 600 ቢሊዮን ዶላር ተመድ ጠይቆ ነበር፡፡
ይህም ሆኖ ሀብታም አገሮች በተለይ ቡድን ሰባት የሚባሉት የበለፀጉ አገሮችና ባንኮቻቸው በየቀኑ ከደሃ አገሮች 232 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ እንዲከፈላቸው ያደርጋሉ ሲልም ነው ኦክስፋም ይፋ ያደረገው፡፡ ይህ እ.ኤ.አ. እስከ 2028 የሚቀጥል ሲሆን፣ ሀብታም አገሮች ሊሰርዙት የሚገባ ዕዳ ግን አጥጋቢ አይደለም በማለት ነው ያስረዳው፡፡
ኦክስፋም እንደገለጸው፣ ዓለም አቀፍ ረሃብ ለአምስተኛ ተከታታይ ዓመት ጨምሯል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በ58 አገሮች 258 ሚሊዮን ሕዝቦች ተርበዋል፡፡
እነዚህን ሁሉ ዘርፈ ብዙ ዓለም አቀፍ ቀውሶች ለመቋቋም የሀብታም አገሮች ቢሊየነሮችና ሚሊየነሮች ላይ አነስተኛ ታክስ በመጨመር ከፍተኛ ሀብት ማሰባሰብ እንደሚቻል ኦክስፋም ከእነ መፍትሔው ያስቀምጣል፡፡ በሀብታም አገሮች ሚሊየነሮች ላይ የሁለት በመቶ፣ እንዲሁም በቢሊየነሮቻቸው ላይ ደግሞ የሦስት በመቶ ታክስ በመጣል የዓለም ችግሮችን መቅረፍ እንደሚቻል ይናገራል፡፡ በሚሊየነሮቹና ቢሊየነሮቹ ላይ የሀብት ግብር በመጨመር ብቻ ለዓለም አቀፍ ቀውሶች መታደጊያ የሚውል በትንሹ 900 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ማመንጨት ይቻላል በማለት ኦክስፋም ያሳስባል፡፡
ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከዚህ ይልቅ ዓለም አቀፋዊ ቀውሶችን ማባባስ ላይ እየተጋ መሆኑን ድርጅቱ ይጠቅሳል፡፡ የቡድን ሰባት አገሮች ለዩክሬን ጦርነት ቢሊዮን ዶላሮች እያፈሰሱ፣ ደሃ አገሮች የሚፈልጉትን ዕርዳታ ግማሹን እንኳን አይሰጡም በማለት ነው ኦክስፋም ያለ ይሉኝታ የተናገረው፡፡
የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ሀካዩንዴ ሂቺሌማ በፓሪሱ ጉባዔ ላይ፣ ‹‹የዓለምን ሀብት፣ ጊዜ፣ ገንዘብና ቴክኖሎጂ በሙሉ ጦርነት ላይ በማዋል ለውጥ ልናመጣ አንችልም፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡ አሁን እንደሚታየው ከሆነ ግን የበለፀጉ አገሮች በዕዳ ጫና ስም ደሃ አገሮች ላይ ጫና እያሳደሩ ናቸው፡፡
በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት አፍሪካዊያን ምዕራባዊያኑ የሚፈልጉትን አቋም እንዲከተሉ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ ይታያል፡፡ በአፍሪካ አሥር ኤምባሲ ያላት ዩክሬን 40 ኤምባሲ ከከፈተችው ሩሲያ ጋር የአፍሪካዊያንን ድጋፍ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ሲታደርግ ይታያል፡፡ ከዚህ ቀደም ኤርትራና ማሊ ሩሲያን ደግፈው አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ ግማሽ የአፍሪካ አገሮች ግን ዩክሬንን ደግፈው ሩሲያ ከያዘችው መሬት ለቃ እንድትወጣ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ላይ በተመድ በተሰጠ ውሳኔ ድምፅ ላይ ድምፀ ተአቅቦ ካደረጉ 32 አገሮች ውስጥ፣ ግማሾቹ የአፍሪካ አገሮች መሆናቸው ለምዕራባዊያኑ አልተዋጠላቸውም ይባላል፡፡ ስድስት አገሮች ጭራሽ በድምፅ አሰጣጡ ዕለት አለመገኘታቸው ደግሞ ዩክሬንና ምዕራባዊያኑን ግራ አጋብቶ እንደነበር ይነገራል፡፡
በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት የአፍሪካዊያን ገለልተኛ አቋም ማንፀባረቅ ያልተዋጠላቸው ምዕራባዊያኑ፣ ይህን አጋጣሚ ከዕዳ ጫና ማቃለል ጉዳይ ጋር አስተሳስረው ለማንሳት መፈለጋቸው በሰፊው እየተነሳ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከዚህ ጉዳይ ጋር አያይዘው በፓሪሱ ስብሰባ ላይ ትኩረት የሚስብ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ሲሪል ራማፎሳ አፍሪካ እንደ ለማኝ መታየት እንደሰለቻት ለምዕራባዊያኑ በቀጥታ ነግረዋቸዋል፡፡ በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ጉዳይ አፍሪካ የሰላም አማራጭን ስትከተል ስለመቆየቷ ተናግረዋል፡፡ አፍሪካ በእህል፣ በማዳበሪያና በሌሎች ምርቶች እጥረት መቸገሯን በማውሳት የጦርነቱ ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽ መሆኗን አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሁሉም መንገድ ቢሆን አፍሪካ እንደ ተረጂና ምፅዋት ጠያቂ ለማኝ ሳይሆን በአቻ ግንኙነት የሚያምኑ አጋሮችን እንደምትፈልግ በጉልህ ተናግረዋል፡፡
ግሪክ እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ ከዓለም የፋይናንስ ቀውስና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ አጋጥሟት ነበር፡፡ የአውሮፓ ኅብረት አበዳሪዎችና አይኤምኤፍ ፈጥነው ሊደርሱላት መወሰናቸው አይዘነጋም፡ እ.ኤ.አ. በ2010 የ110 ቢሊዮን ዩሮ መታደጊያ ተሰጣት፡፡ በ2011 ደግሞ ሌላ ዙር 130 ቢሊዮን ዩሮ ተሰጣት፡፡ ሁለት ተከታታይ የመታደጊያ ገንዘብ ከመስጠት በተጨማሪ በቀጣዩ ዓመት በ2012 የዕዳ ሽግሽግ ተደረገላት፡፡
የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ ይህን የሚያጎላ ሐሳብ በፓሪሱ ጉባዔ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እንግሊዝ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ቀውስ እንድትወጣ ለመቶ ዓመታት ዕዳ ተራዝሞላታል፡፡ ጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንድታገግም ዕዳ ተቀንሶላታል፡፡ እኛም ልክ እንደ እነሱ አገር ነን፡፡ እኛም ልክ እንደ እነሱ የዕዳ ሽግሽግ እንፈልጋለን፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡