

ዜና የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋን ስንብት በተለያየ ስሜት እንደተቀበሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋን ስንብት በተለያየ ስሜት እንደተቀበሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ
ቀን: June 28, 2023
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በድንገት ከሥራ መልቀቃቸው ያልጠበቁት እንደሆነና የተለያየ ስሜት እንደፈጠረባቸው፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡
በተለይ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች የሰብሳቢዋ ከኃላፊነት መልቀቅ ይመሩት በነበረው የምርጫ ቦርድ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ የሚተርፍ ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር)፣ ‹‹የብርቱካን ከሥራ መልቀቅ ለብዙ ፓርቲዎች ያልጠበቅነውና ዱብ ዕዳ ነው የሆነብን፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሐፊ ራሔል ባፌ (ዶ/ር)፣ ምርጫ ቦርድ በሴት ሰብሳቢ በመመራት ሊያገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ ቢያጣም፣ ነገር ግን የግለሰቦች ከኃላፊነት መልቀቅ ከመድበለ ፓርቲው ጋር የሚገናኝ ተፅዕኖ አይኖረውም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተቀዳሚ ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት በበኩላቸው፣ ወ/ሪት ብርቱካን ምርጫ ቦርድ ጠንካራ ተቋም እንዲሆን መልፋታቸውን ተናግረዋል፡፡ የእናት ፓርቲ አመራር የሆኑትና አሁን በእረፍት ላይ እንደሚገኙ በመጥቀስ በግላቸው አስተያየት የሰጡት አቶ ጌትነት ግርማ፣ ‹‹ብርቱካን የአቋምና የሥራ ሰው መሆናቸውን አውቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡
በለውጡ ማግሥት በአሜሪካ ከቆዩበት የስደት ኑሮ በመመለስ ባለፉት አራት ዓመታት የምርጫ በርድ ሰብሳቢ ሆነው የሠሩት ወ/ሪት ብርቱካን፣ ሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋዊ የማኅበራዊ ገጻቸው በጤና ምክንያት ከሥራ ለመልቀቅ መገደዳቸውን ይፋ ማድረጋቸው ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ መብራቱ (ዶ/ር)፣ ወ/ሪት ብርቱካን የቦርድ አመራር ዘመን የተቃዋሚ ፓርቲዎች በጀትና ሥራ ማስኬጃ በአግባቡ ሲሰጥ መቆየቱን ያወሳሉ፡፡ ሰብሳቢዋ በተናጠል ከፓርቲዎች ጋር በቅርበት መሥራታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከጋራ ምክር ቤቱ ጋርም ተቀራርቦ ለመሥራት ጥረት ማድረጋቸውን በመልካምነት ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹በእሳቸው ቦታ በጣም የተሻለ ልምድ ያለውና ቆራጥ ሰው መመደብ ካልተቻለ፣ በእሳቸው መልቀቅ የሚፈጠረው ክፍተት ቦርዱንና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን ሊፈትነው ይችላል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ምርጫ የዴሞክራሲ መገለጫ መሆኑን የገለጹት፣ መብራቱ (ዶ/ር)፣ ይህን በአግባቡ ለመምራት የሚችል ምርጫ ቦርድ መገንባት ደግሞ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን በዚህ ረገድ ቦርዱን ለማጠናከር ያደረጉትን ጥረት እንደሚያደንቁ በመጥቀስ፣ በእሳቸው ስንብት ሊፈጠር የሚችለው ክፍተት እንደሚያሠጋቸው ጠቁመዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሐፊ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ብርቱካን የቦርድ ሰብሳቢ መሆናቸው ፆታ የራሱ ተፅዕኖ ያለው በመሆኑ በአንድ ጎን በበጎ ይታያል፡፡ ሴቶች ቻይና ታጋሽ በመሆናቸው፣ ግልጽነትና ቀጥተኝነት ያላቸው በመሆኑ፣ እንዲሁም በለውጥ ፈላጊነታቸው የተነሳ የብርቱካን ወደ ቦርድ ኃላፊነት መምጣት ለዚህ ጠቃሚ ጎን ነበረው፤›› ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የግለሰቦችን ጉዳይ በቀጥታ ከመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ጋር ማያያዝ ጠቃሚ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ የቦርዱ ሰዎች በመቀያየራቸው በመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ላይ የሚፈጠር ተፅዕኖ እንደሌለ አክለዋል፡፡
‹‹የፓርቲዎችና የምርጫ አዋጅ ቁጥር 1162 ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ቢጠቀስም፣ ተቋቁሟል ተብሎ እንኳ ሕጋዊ ሰውነት አልተሰጠውም፤›› በማለት ራሔል (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ‹‹ምርጫ ቦርድ ሲወደስባቸው የቆዩ አንዳንድ ውሳኔዎችም ቢሆኑ ለአፍና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር፣ በክልሎችና በወረዳ ደረጃ መድበለ ፓርቲው በተግባር ተተርጉሞ አላየንም፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የኢሕአፓ ተቀዳሚ ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብረሃም በበኩላቸው፣ በአስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎች ወቀት ቦርዱን እየመሩ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማድረግ በግል ጥረት ያደረጉ ሰው እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
‹‹የብርቱካን ከምርጫ ቦርድ ኃላፊነት መልቀቅ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ይጎዳዋል፡፡ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ እንድንገባና ተጠራጣሪ እንድንሆን ያደርጋል፡፡ ለቀጣይ ምርጫ ለመዘጋጀት አንድ መነሻ ምክንያት የሚሆኑትን ጠንካራ የቦርድ አመራር ማጣት ለእኛ ያሳስበናል፡፡ የእሳቸው ከኃላፊነት መልቀቅ ውስጣዊ ጫና ሊኖረው እንደሚችል እንጠራጠራለን፡፡ ማን ይተካቸዋል የሚለውም ሥጋት ሆኖብናል፤›› በማለት ነው መጋቢ ብሉይ አብርሃም የተናገሩት፡፡
በግል አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ጌትነት ግርማ በበኩላቸው፣ ‹‹ብርቱካን በምርጫ ቦርድ ውስጥ ጠንካራ ሠራተኞችን በማዋቀር ጠንካራ የሥራ መንፈስ ለማምጣት ጥረት ማድረጋቸውን፣ ለእኛ በሚሰጡን አገልግሎት ማረጋገጥ እችላለሁ፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ጌትነት፣ ‹‹መላዕክት እንኳ ለቦርዱ ቢሾሙ ተቋሙ አይቀየርም፡፡ መንግሥት እስካልፈቀደ ድረስ ቦርዱ ምንም ሊቀየር አይችልም፤›› ይላሉ፡፡
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆነው ቦርዱ ለውጥ እንዲያመጣ ጥረት ማድረጋቸውን ያስረዳሉ፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር በበኩላቸው፣ የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን መሾም ሲቃወሙ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሴትየዋ ወደ ቦርዱ የመጡት ለመንግሥት የገጽታ ግንባታ ፍጆታ እንዲሆን ነበር፤›› ያሉት አመራሩ፣ የፖለቲካ ሥርዓቱ መቀየር እንጂ የቦርድ ተሿሚዎች መለዋወጥ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ፋይዳ እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡
አስተያየት ቢጠየቁም ኢዜማና ኦነግ በዚህ ጉዳይ የሚሉት አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡