

July 2, 2023
ኢትዮጵያ በ2023 የዓለም አገሮች የወንጀል ሪፖርት ላይ 50ኛ ደረጃ ላይ ስሟ ሠፍሯል፡፡ የዓለም አገሮችን የወንጀል ደረጃ የሚያወጣው ‹‹The World Population Review›› ገጽ፣ የአገሮችን የወንጀል ደረጃ የሚለካው ሪፖርት የሚደረጉ የወንጀል ድርጊቶችን ለአጠቃላይ ሕዝብ ብዛት በማካፈል በ100 ሺሕ በማብዛት መሆኑን ገልጸዋል፡፡፡ በዚህም መሠረት 126 ሚሊዮን ሕዝቦች ያላት ኢትዮጵያ 49.3 ነጥብ አግኝታ፣ ከዓለም አገሮች በወንጀል ምጣኔ 50ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ሪፖርቱ ያብራራል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2012 የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው ከሆነ፣ በኢትዮጵያ በየ100 ሺሕ ሰው በአማካይ 8.79 የግድያ ወንጀሎች ይፈጸማሉ፡፡
የዓለም አገሮችን የኑሮ ውድነትና የኑሮ አመቺነት በማጥናት የሚታወቀው ኑምቢዮ፣ በኢትዮጵያ አሉ የሚላቸውን የወንጀል ተጋላጭነቶች በተለያዩ መንገዶች ያስቀምጣል፡፡ የኢትዮጵያን የወንጀል ደረጃ 50.57 ነጥብ በመስጠት መለስተኛ (Moderate) የሚል ብይን ይሰጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያለውን የወንጀል ጭማሪ 71.39 ነጥብ በመስጠት ከፍተኛ (High) ይለዋል፡፡
ኑምቢዮ ከመኪና ዘረፋ እስከ ንጥቂያና ስርቆት ኢትዮጵያ በመኖር (አገር ጎብኚ በመሆን) ሊያጋጥሙ የሚችሉ የወንጀል ሥጋቶችን በሰፊው ይዘረዝራል፡፡ ስድብና ጉንተላ ይገጥመኛል ብሎ ተሳቆ ከመሄድ ጀምሮ፣ በኢትዮጵያ ጎዳናዎች በእንቅስቃሴ ወቅት ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ የወንጀል ተጋላጭነቶች ከቀላል እስከ ከባድ ይዘረዝራል፡፡ በቀንና በማታ ለመንቀሳቀስ ኢትዮጵያ ያላትን አመቺነት ይጠቁማል፡፡ በብዙዎቹ መመዘኛዎች መለስተኛ (Moderate) የሚል ውጤት ኢትዮጵያ ማግኘቷን ድርጅቱ ይዘረዝራል፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በወንጀል ተጋላጭነት ሪፖርቶች ላይ ኢትዮጵያ ደህና የሚባል ነጥብ ሲሰጣት ማየት የተለመደ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ ሁኔታ እየተለወጠ የመጣ ይመስላል፡፡ ዘር ተኮር ጥቃት መባባሱ፣ የፖለቲካ ብጥብጡ፣ ግጭቱና ጦርነቱ የአገሪቱን የወንጀል ተጋላጭነት በእጅጉ እየጨመረው እንደመጣ ይነገራል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የዕገታ ወንጀል በእጅጉ መበራከቱ ይነገራል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ኢዜአ የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አየልኝ ታክሎን ጠቅሶ በሠራው ዘገባ፣ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ 18 ያህል የሰው ዕገታ ወንጀሎችን ማክሸፍ ስለመቻሉ ዘግቦ ነበር፡፡ በዚሁ ዘገባ በዕገታ ወንጀል የተጠረጠሩ 28 ሰዎች ስለመያዛቸውና 17 ተጠርጣሪዎች ደግሞ በፍለጋ ላይ ስለመሆናቸው መጠቀሱም አይዘነጋም፡፡
የዕገታ ወንጀል ስለመፈጸሙ ባለፉት ዓመታት ከሁሉ ቀድሞ ሲሰማባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል ጎንደርና ዙሪያው ተደጋግሞ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ በሒደት ግን የዕገታ ወንጀል ተፈጸመ የሚባልባቸው አካባቢዎች ቁጥራቸው መበራከት ጀመረ፡፡ በተለይ ኦሮሚያ ክልል በብዙ አቅጣጫዎች እስካሁንም የዕገታ ወንጀሎች መፈጸማቸው በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡
የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ዕገታ ጉዳይ እስከ ፓርላማው የደረሰ ከባድ የፖለቲካ ውዝግብ መፍጠሩ አይዘነጋም፡፡ ኦነግ ሸኔ በሚል ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን፣ እንዲሁም ከሌሎች የትጥቅ ኃይሎች እንቅስቃሴ መጨመር ጋር ተያይዞ የዕገታ ወንጀሎች መጨመራቸው ይነገራል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የሰደን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በቀለ ቃጫ ከሰሞኑ የገጠማቸው ሕልፈተ ሕይወት ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ አቶ በቀለ ባልታወቁ ሰዎች ያውም ከመኖሪያ ቤታቸው እንደታገቱ የዞኑ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብዶ ለዶቼቬሌ ተናግረዋል፡፡ አጋቾቹ ለቤተሰብ እየደወሉ ጭምር አቶ በቀለን ለመልቀቅ እስከ አሥር ሚሊዮን ብር ይከፈለን እያሉ ሲጠይቁ ነበርም ይላሉ፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ ሰኔ 13 ቀን 2015 ቀን ተገድለው ተጥለው አስከሬናቸው መገኘቱን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በአስጎሪ አካባቢ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ አለመኖሩን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ኃይሉ ቢናገሩም፣ ይሁን እንጂ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰላማዊ አርሶ አደሮች ጭምር እየታገቱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ለታገቱ ሰዎች በነፍስ ወከፍ ከ200 እስከ 500 ሺሕ ብር ማስለቀቂያ ክፍያ አጋቾቹ እንደሚቀበሉ አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ሰዎችን እያገቱ ገንዘብ መቀበል እየተለመደ የመጣ ወንጀል መሆኑ ይነገራል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም በሚወስደው ዋና መንገድ በተለያዩ ጊዜያት የሹፌሮች ዕገታ ስለመፈጸሙ በተደጋጋሚ ይወሳል፡፡ ከሰሞኑ በዚሁ መስመር በሰሜን ሸዋ ዞን አሊዶሮ አካባቢ በርካታ ሾፌሮች ታገቱ መባሉ ከባድ ውዝግብ አስነስቷል፡፡
በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ ለእርሻ ሥራ በሚል ከወጡ ሰዎች መካከል፣ ሦስት ታግተው ሦስት ተገደሉ የሚል ዜና ከሰሞኑ ተዘግቧል፡፡
በወንጂና በመተሃራ መካከል ባለው ዋና መንገድ ተደጋጋሚ የሾፌሮች ዕገታ ስለመፈጸሙ ይነገራል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ ለአምልኮ የሚጓዙ መንገደኞች ታገቱ የሚል ዜና ከሌላ የአገሪቱ አቅጣጫ ይሰማል፡፡ የጭነትም ሆነ የሰው መጓጓዣዎች የዕገታ ሰለባ ስለመሆናቸው በሰፊው ይሰማል፡፡ ከኢንዱስትሪዎች እስከ ቤተ እምነቶች የዕገታ ወንጀል ተቃጣባቸው መባሉ ተለምዷል፡፡ በቅርብ ዓመታት በሁሉም አቅጣጫዎች፣ በሁሉም አጋጣሚዎችም ሆነ በሁሉም መስኮች ዕገታ ተፈጸመ ሲባል መስማት ተለምዷል፡፡
ሁኔታው በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ብቻ ሲከሰት የሚታይ ሳይሆን፣ አዲስ አበባንም መጎብኘቱ ይነገራል፡፡ የዕገታ ወንጀል በሚል የሚጠረጠሩት እነዚህ የወንጀል አጋጣሚዎች ከዕገታ በተጨማሪ፣ የግድያና የንብረት ዘረፋን ቀላቅለው መፈጠራቸው በርካቶችን እያሳሰበ ነው፡፡
የዕገታ ወንጀል በኢትዮጵያ እንዲሁም በአዲስ አበባ እየተበራከተ መጥቷል የሚለውን ጉዳይ፣ የፌዴራልም ሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባለሥልጣናት አይስማሙበትም፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጄይላን አብዲ፣ የዕገታ ወንጀሎቹ በተለየ ሁኔታ የበዙባቸው አካባቢዎች አለመኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ ዕገታዎቹ የሚፈጸሙባቸው ዓይነትና ሁኔታ እንደሌለ በመጥቀስም፣ የፌዴራል ፖሊስ ከመደበኛ የወንጀል መከላከል ሥራ ውጪ የተለየ የዕገታ መከላከል ሥራ እንደማይሠራ ገልጸዋል፡፡
‹‹ዕገታዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ነው የሚፈጸሙት፡፡ አንዳንዱ ከፆታዊ ፍላጎት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሰሞኑ በእንግድነት ያደረበት ቤት ሠራተኛን አስገድዶ የደፈረ አንድ ግለሰብ ጉዳዩ ሲጋለጥበት ልጅቱን አግቶ የወሰደበት ሁኔታ አጋጥሞናል፡፡ ወንጀሉን ለመደበቅ ልጅቷ ላይ የከፋ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ ቢገመትም፣ ነገር ግን ቤተሰቡ ሲታሰርበት እጁን ለፖሊስ ሰጥቷል፣ ልጅቷንም ሳይጎዳ መልሷል፤›› በማለት አቶ ጄይላን ማሳያ ያሉትን የወንጀል ድርጊት አስረድተዋል፡፡
አንዳንዴ ደግሞ ለገንዘብ ተብሎ ዕገታ ይፈጸማል ብለው፣ ‹‹ለገንዘብ ብላ ከጓደኞቿ ጋር የምተሠራበት ቤት ልጆችን የሰረቀች የቤት ሠራተኛ ተይዛለች፡፡ በድንበር አካባቢ ሥራ ፍለጋ የሚሰደዱ ዜጎችን እያገቱ ቤተሰባቸውን ገንዘብ ላኩ የሚሉ አጋቾች አሉ፤›› በማለት ነው ማሳያ ጉዳዮችን የጠቃቀሱት፡፡
‹‹ትልቁ ነገር እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ፖሊስ ጠንክሮ እየሠራ ነው፤›› የሚሉት አቶ ጄይላን፣ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከእስካሁኑ በበለጠ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ዕገታ ጨመረ ወይም ተባባሰ የሚለውን እንደማይቀበሉት ይናገራሉ፡፡
‹‹አንዳንዱ ታገተ እየተባለ የሚነገረው ከራሱ የወንጀል ጉዳይ ጋር በተገናኘ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዱ በራሱ መንገድ ይሄድና ታገትኩ ይላል፡፡ ነገርየው ጨመረ የሚባለው አሳማኝነት የለውም፤›› በማለት ነው ኮሚሽነሩ ምላሽ የሰጡት፡፡
በተናጠል አንዳንድ አጋጣሚዎችን እየጠቀሱ የዕገታ ወንጀል በአዲስ አበባ በዝቷል ማለት እንደማይቻል ያስረዱት ኮሚሽነር ጌቱ፣ እነዚህን ዕገታ እየተባሉ የሚነሱ ጉዳዮችን ቢሆን ከሌላ ወንጀል ምርመራ ጋር የተገናኙ መሆን አለመሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡
‹‹በቅርቡ ከሕገወጥ ማዕድናት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ የወንጀል ድርጊቶችን ምርመራ ላለማበላሸት ሲባል መረጃ ላይሰጥ ይችላል፡፡ አንድ የምርመራ ሥራ ጀምረናልና ሥራውን አገባደን መረጃ እስክንሰጥ ልትታገሱን ይገባል፤›› በማለት የገለጹት ኮሚሽነር ጌቱ፣ ይህ መረጃም በኮሙዩኒኬሽን ዴስክ በኩል እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰም ቢሆን ይህንኑ ደግመው ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንድ የተጀመረ የምርመራ ሒደት አለ፣ እሱን ላለማደናቀፍ ሥራው ጥንቃቄ ስለሚጠይቅ ብትታገሱ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከሰሞኑ ዕገታ እየተባሉ ሲገለጹ የሰነበቱ የወንጀል ድርጊቶች ከሌሎች የምርመራ ሒደቶች ጋር ሊገናኙ እንደሚችሉ አክለዋል፡፡
ማክሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት በተለምዶ ሰሚት 72 ከሚባል ቦታ የጫናቸውን ሦስት ሰዎች ወደ ቦሌ አራብሳ ገብርኤል በሜትር ታክሲ ለማድረስ ይስማማል፡፡ የ48 ዓመቱ የሁለት ልጆች አባት አቶ ዘላለም ዘገየ ያስፈራቸውን ሰዎች የጠየቁት ቦታ ማድረሱን በፈረስ መተግበሪያው ቢያረጋግጥም ላይመለስ በአጋች ወንጀለኞች ተወስዶ ነበር፡፡
አጋቾቹ ገድለውት አራብሳ አካባቢ ጥለውት መኪናውን ይዘው ተሰወሩ፡፡ ከቀናት ፍለጋ በኋላ መኪናው ቡራዩ አካባቢ ሲያዝ አንድ ሳምንት ከቆየ ፍለጋ በኋላ አስከሬኑም አቃቂ ወንዝ ውስጥ መገኘቱን ፖሊስ ይፋ አድርጓል፡፡
በአዲስ አበባ በተለይ በሜትር ታክሲ አሽከርካሪዎች በዋናነት የምሽት ሥራ በሚሠሩ ሹፌሮች ላይ የሚፈጸመው ዕገታ ሲደጋገም ይሰማል፡፡ ይህን ለመከላከል በቴሌግራምና በሌሎች ማኅበራዊ መገናኛዎች መረጃ መለዋወጫ ግሩፕ ሾፌሮቹ ፈጥረዋል፡፡ ወደ 5,000 አባላትን ባሰባሰበው የሜትር ታክሲ ‹‹ፍሬንድስ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ማኅበር›› የቴሌግራም ግሩፕ ላይ በየቀኑ የአሽከርካሪዎች ዕገታና የመኪና ዘረፋ ሪፖርት ይደረጋል፡፡ አንዳንዶቹ ሾፌሮች በሕይወት ተርፈው ከዕገታ መለቀቃቸውን እንደ ታላቅ ዕድለኝነት ሪፖርት ሲያደርጉ ብዙ ጥያቄ ያስነሳል፡፡
በሜትር ታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ በዛ ብሎ ቢታይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ታግቶ በሕይወት መትረፍ፣ በሁሉም መስክ እንደ ዕድለኝነት እየተቆጠረ ነው የሚገኘው፡፡ ከሰሞኑ ሰፊ ትኩረት አግኝቶ የሰነበተው የሠዓሊ ሙሉጌታ ገብረ ኪዳን ታግቶ መገደል መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ አሁን አሁን የዕገታ ወንጀል ድርጊቶች በተፈጸሙ ቁጥር የንብረት ወይም የመኪና ዘረፋና የግድያ ወንጀሎች ተያይዘው መፈጸማቸው እየተለመደ ነው፡፡
ዕገታና ተያያዥ ወንጀሎችን ለመከላከል ፖሊስ የተለየ ዕቅድ፣ የተለየ ግብረ ኃይል፣ ወይም የተለየ ጥረት እያደረገ ይሆን ወይ የሚል ጥያቄ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄይላን ግን ኮሚሽናቸው ለሁሉም ወንጀሎች ከሚተገብረው የተለየ ዕቅድ በዕገታ ላይ እንደሌለው ነው የተናገሩት፡፡
‹‹ዕገታው በተለያየ ቦታ፣ በተለያየ ጊዜና ሁኔታ ነው የሚፈጸመው፡፡ ለብቻው አቅዶ ለመከላከል ፈታኝ ነው፡፡ ሌላው ፖሊስ ሁሉም ቦታ አይደርስም፡፡ ትልቁ ፖሊስ ሕዝብ ነውና ሕዝቡ እነዚህን የዕገታ ወንጀሎች ለማስቆም ከፖሊስ ጋር ይተባበር፤›› ሲሉ አቶ ጄይላን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ በበኩላቸው፣ በአሰቃቂ ሁኔታ በተገደለው የራይድ አሽከርካሪ ጉዳይ ፖሊሶች የሚመሠገን ሥራ መሥራታቸውን ይናገራሉ፡፡ በተናጠል በየአጋጣሚው በከተማዋ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ግን የዕገታ ወንጀል በአዲስ አበባ በዝቷል እንደማያስብሉ ነው ኮሚሽነሩ የሞገቱት፡፡