
July 5, 2023 – EthiopianReporter.com

ቀን: July 5, 2023
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሙስ ዕለት ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተነሳሽነት እየተገነቡ ባሉት የፓርኮችና የቤተ መንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ ሥጋት ያደረባቸውና ኦዲት መደረግ አለባቸው ብለው የሚያስቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ለምክር ቤቱ አመራሮችና አፈ ጉባዔ ጥያቄዎችን በማቅረብ ኦዲት ለማስደረግ መጠየቅ እንደሚችሉ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ማክሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በምክር ቤቱ አባላትና በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር፣ ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሎሚ በዶ ፕሮጀክቶቹ በአባላት ጥያቄ መሠረት ኦዲት ሊደረጉ እንደሚችሉ ሲናገሩ ነው፡፡
በምክር ቤቱ በተደረገ የፌዴራል መንግሥት የ2016 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ዝርዝር የውይይት መድረክ ላይ የተገኙ ሁለት የምክር ቤት አባላት፣ በአገሪቱ እየተገነቡ ባሉ ፓርኮችና የጫካ ፕሮጀክት በመባል በሚታወቀው አዲሱ የቤተ መንግሥት ግንባታ ላይ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡
አባላቱ መንግሥት ትኩረቱን እያደረገ ያለው ደሃ ተኮር የሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ሳይሆን ፓርኮችንና ቤተ መንግሥትን ጨምሮ ቅንጡ መሥሪያ ቤቶችን በመገንባት ላይ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ለተነሱት ጥያቄዎችም የገንዘብ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ለአዲስ ቤተ መንግሥት ግንባታ በሚል ለምክር ቤቱ የቀረበ የበጀት ጥያቄ አለመኖሩን፣ የጫካ ፕሮጀክት ልማት በርካታ የልማት ሥራዎች በጋራ የተቃዱበት በበጀት የማይለማ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የሕዝብን ገንዘብ ወደ ፓርኮቹና ቤተ መንግሥቱ ልማት በማዞር ሳይሆን ከልማት አጋሮች በተገኘ ድጋፍ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ብናይ፣ የሸገር ፓርክ ልማት ፋይናንስ የተደረገው በቻይና መንግሥት ድጋፍ ነው፡፡ የሳይንስ ፓርክን ጨምሮ የሠሩት ቻይኖች ናቸው፤›› ሲሉ አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡
ወዳጅ አገሮችና ባለሀብቶች ተጠይቀው ሀብት በማሰባሰብ የተሠሩ እንደሆነ ስለፓርኮቹ ያስረዱት ሚኒስትሩ፣ ያለምንም ብድር የተገኙና ንፁህና አረንጓዴ አካባቢን በማልማት መሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎትን እንደሚያሟሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራና ሳይንስን ሊያበረታታ የሚችል ተቋም መፍጠር መሠረታዊ የልማት ፍላጎት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የሚኒስትሩን ማብራሪያ በማቋረጥና የሥነ ሥርዓት ጥያቄ እንዳላቸው በማንሳት ሚኒስትሩ ለተጠየቀው ጥያቄ እየሰጡ የነበረው ምላሽ የሕግና የሥነ ሥርዓት ጉዳዮችን የጣሰ እንደሆነ የተናገሩት፣ የምክር ቤት አባልና የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ናቸው፡፡
አቶ ክርስቲያን ማንኛውም ግለሰብ በግሉ ገንዘብ የመሰብሰብ መብት ቢኖረውም፣ ገንዘቡን ለሕዝባዊ ዓላማዎች ሲያውለው ግን በመንግሥታዊ ሥነ ሥርዓት ውስጥ ማለፍ አለበት ብለዋል፡፡
‹‹ክቡር ሚኒስትሩ የሚናገሩት ይህንን ምክር ቤት ይመጥናል ብዬ አላምንም፡፡ ይህንን ንግግር በቀጥታ ለሚከታተል የኢትዮጵያ ሕዝብም ትክክል አይደለም፤›› ያሉት አቶ ክርስቲያን ምክንያታቸውን ሲገልጹ፣ ‹‹በግል የተሰበሰበ ገንዘብ ለሕዝብ ኢንቨስትመንት እስከዋለ ድረስ የመንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት እስከሆነ ድረስ ደግሞ በዚህ ምክር ቤት መፅደቅ አለበት፣ ቁጥጥርም ሊደረግበት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ከአቶ ክርስቲያን ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ለምክር ቤቱ መረጃውን ሲያቀርቡ ምንም ዓይነት የተጣሰ የምክር ቤት ሥነ ሥርዓት እንደሌለ፣ ‹‹አሁንም ቢሆን ለቤተ መንግሥቱ ግንባታ የተጠየቀ በጀት የለም፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ አበባው ደሳለው፣ ‹‹ደሃ ተኮር ኢኮኖሚ ነው የምናራምደው የምትሉት፡፡ ነገር ግን የሚታየው ያደጉ አገሮች ኢኮኖሚን የምንከተል ነው የሚመስለው፡፡ እያተኮርን ያለነው ትልልቅ ፓርኮችና ቅንጡ የሆኑ መሥሪያ ቤቶች ላይ ነው፡፡ እንዲሁም ቤተ መንግሥት ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ አህመድ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነበር አቶ ክርስቲያን የሥነ ሥርዓት ጥያቄ ያነሱት፡፡
ምክትል አፈ ጉባዔዋ በማሳረጊያ ንግግራቸው የምክር ቤቱን ደንብ በመጥቀስ፣ አባላቱ የሚጠራጠሩት ነገር ካለ ኦዲት መደረግ እንደሚችልና ጥያቄያቸውን ለምክር ቤቱ አመራር እንዲያቀርቡ አማራጭ አቅርበዋል፡፡
‹‹ሥጋት ያለው አካል ሁሌም መድረክ ሲኖር ከሚያነሳ ለምክር ቤት ይቅረብ፡፡ ከዚያም በአፈ ጉባዔ ደረጃ እንወያይና በአመራር ደረጃ ወስነን ኦዲት መደረግ ያለበት ጉዳይ ካለ ኦዲት ይደረጋል፤›› ሲሉ ወ/ሮ ሎሚ አስረድተዋል፡፡
ሐሙስ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ በመገኘት የበጀት ጉዳይን በሚመለከት ማብራሪያ እንደሚሰጡ፣ ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከልም የፓርኮችና የቤተ መንግሥት ግንባታ ጉዳዮች እንደሚገኙበት ምክትል አፈ ጉባዔዋ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡