
July 5, 2023 – EthiopianReporter.com

July 5, 2023
በአማራ ክልል ተገደሉ በተባሉት የምሥራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥና ምክትላቸውን በተመለከተ ፖሊስ ምርመራ መጀመሩን፣ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ለሪፖርተር ገለጸ፡፡
‹‹ወንጀል ማኅበራዊ ክስተት ስለሆነ፣ በየደረጃው ሊፈጸም ይችላል፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ጥቃቱን በተመለከተ ፖሊስ ምርመራ መጀመሩን፣ በሚያደርገው ምርመራ መሠረት ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥ የተናገሩት የቢሮው ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ናቸው፡፡
እስካሁን ስለተደረገው ክትትል ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት አቶ ደሳለኝ፣ ‹‹ወንጀለኛን ለመያዝ የሚደረግ ሥምሪት በንፁኃን ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል፣ በጉዳዩ ላይ የተሟላ መረጃ ሲገኝ ይፋ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡
የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ዘውዱ ታደለና ምክትላቸው ኢንስፔክተር ወርቁ ሽመልስ፣ ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በግለሰብ ግድያ ሲፈጸምባቸው፣ ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል፡፡
ቆስለዋል የተባሉት የሟቾቹ ሾፌርና ሌላ አንድ የገልባጭ ተሽከርካሪ ሾፌር መሆናቸውን፣ ጥቃቱን አደረሰ የተባለው ተጠርጣሪ እንዳልተያዘ፣ ተጠርጣሪው ጥቃቱን ያደረሰው በደጀን ወረዳ ‹‹ገልግሌ ደንበዛ›› በምትባል ቀበሌ የፖሊስ አዛዡና ምክትላቸው በጉዞ ላይ በነበሩበት ወቅት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ በክልሉ እየተስተዋለ ያለውን የፀጥታ ችግር አሁናዊና የቀጣይ ሁኔታ አቅጣጫን በተመለከተ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ እንዲሁም ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ውይይት ማድረጉን አቶ ደሳለኝ አስረድተዋል፡፡
የፀጥታ መዋቅሩ የክልሉን፣ የዞኑንና የወረዳቸውን ቀጣና ባለቤትነትና ኃላፊነት በመውሰድ ከጥፋት ኃይሎች ጋር በመነጋገር ልማትን የሚያደናቅፉ አስተሳሰቦችና ውንጀላዎችን እንዴት በጋራ መፍታት እንደሚቻል፣ በዚሁ ረገድ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ፣ በአጠቃለይ በክልሉ የሚስተዋለውን የእርስ በርስ ግጭት ማስወገድ ውይይት የተደረገባቸው ዋነኛ ነጥቦች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የእርስ በእርስ ግጭት ላይ በማተኮር፣ ዕርቀ ሰላምና የውይይት ሥራዎችን ለመሥራት ዕቅድ መያዙም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር የፀጥታ ቢሮው እስካሁን ለምን ምክክር እንዳላደረገ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ዕርቀ ሰላም ለማድረግ ውይይት መደረጉን ከመግለጽ ባሻገር የሰጡት ማብራሪያ የለም፡፡
ከተከሰተ ውሎ ያደረው የፀጥታ ችግር በሰብዓዊ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚው ላይ ያደረሰውን አጠቃላይ ቀውስ እንዲያስረዱ ሲጠየቁም፣ የፀጥታ ችግር ካለ በሰላም ወጥቶ መግባትና የልማት እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር እንደሚያስከትል አስረድተው፣ ስለሌላው ጉዳይ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
‹‹ሕዝባችን ትልቅ ነው፤›› ያሉት አቶ ደሳለኝ፣ ‹‹በውስጡ ባሉት ባህላዊ እሴቶችና ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ሕግን በማስከበርና በማክበር ሒደት ውስጥ ዕምቅ ሀብት ቢኖርም፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ በየአካባቢው እየተፈጠረ ያለው ሥርዓተ አልበኝነት ሕዝቡ የላቀ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዳይኖረው የፀጥታው ችግር እየፈተነው ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ከምንም በላይ የእርስ በእርስ ጉዳት ማንንም አሸናፊ የማያደርግ መሆኑን በደንብ መክረን፣ ተባብረን፣ የጋራ ግንዛቤና ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ሕዝቡ ከተጋረጠበት ሥጋት፣ የደኅንነት ጉስቁልና የሚያወጣ አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ የፀጥታ ችግር በመፈጠሩ ነዋሪዎች በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መሆናቸውን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡