
የህዘብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን በማከሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተገኙ ሲሆን ከአባላቱ በኩል በርከት ያሉ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡ ከእረሱም መካከል የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) አባሉ ደሳለኝ ጫኔ የጠየቋቸው ጥያቀዌች ይገኙበታል፡፡
ሰፊ ጊዜ ወስደው የዐብይን መንግስት የተቹት ደሳለኝ ‹ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መንግስት የወደቀ › ሲሉ በይነውታል፡፡
ደሳለኝ በማብራሪያቸው ‹ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን ከወጡበት መጋቢት 2010 ዓመት ጀምሮ እየተወሳሰቡ የመጡት የሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ወደሁለንታዊ ቀውስ መሸጋገራቸውን መሸፋፈን በማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል › ብለዋል፡፡
‹ ብልፅግና መራሹ መንግስትዎ የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላም ወጥቶ የሚገባበት፣ ነጋዴው ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ፣ ሰርቶና ነግዶ የሚኖርበት፣ ገበሬው አርሶ የሚበላበትና ከተሜውን የሚቀልብበትን ሁኔታ መፍጠር አልቻለም › ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
‹ የኢትዮጵያ ህዝብ በችጋር እየተጠበሰ፣ በረሃብ እየተሰቃየ ነው › ሲሉም ተናግረዋል፡፡
‹ የኑሮ ውድነቱ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ወገናችን ከእጅ ወደአፍ የሆነውን ኑሮ እንኳ መግፋት ወደማይችልበት ደረጃ ደርሷል፤ ኢኮኖሚው ታምሟል፤ መካከለኛ ነዋሪ የነበረውም ተመትቶ ወደ ድህነት ወለል ወርዷል › ሲሉ አብራርተዋል፡፡
‹ ስራ አጥነት ተስፋፍቷል፤ ወጣቶች ስደትን ምርጫ አድርጓል፤ ዜጎች በጠራራ ፀሃይ ይታገታሉ፤ ሚሊዮን ብር ይጠይቅባቸዋል የመንግስት የፀጥታ መዋቅር በተለይም ፖሊስ አማራ ዎችንና የአማራ ሊህቃንን የአማራን ህዝብ ጥያቄዎችን በመንሳታቸው መንግስትን በተለያየ መንገድ በመጠየቃቸው ብቻ የፈጠራ ወንጀል እየተሰጣቸው በማንነታቸው በጅምላ ይታሰራሉ፣ በጅምላ ይከሰሳሉ፤ ፍርድ ቤትም ነፃ ሲላቸው ፖሊስ ግለሰቦችን አስሮ ያቆያል › ሲሉ የፍትሕ ስርዓቱን ኮንነዋል፡፡
‹ የኢትዮጵያ መልዓካ ፖለቲካ በሙሉ ያደረሰ በሚባል ደረጃ ሀገራችን ሁሉም አካባቢዎች የደም ምድር ሆኗል፤ ሙሉ አማራ ክልል አዲስ የጦርነት ቀጣና ተደርጓል፤ ከፊል የኦሮሚያ ክልል ሆኖ ባጅቷል፤ ትግራይ፣ አማራና አፋር ፋይዳ ባልነበረው የብልፅግናና ህወሓት የስልጣን ጦርነት ምክንያት ደቅቋል፡፡ ቤኒሻንጉል ጋምቤላ… የተለዩ አይደሉም › ሲሉ የሀገሪቱን ሁኔታን የተረዱበትን መንገድ አስረድተዋል፡፡
‹ ከሁለት መቶሺህ በላይ ሰዎች ቤት አልባ ሆነዋል፤ በብፅልግና ሹማምንት አገላለፅ ህጋዊ ደሃ ተደርገዋል › ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
‹ ለዚህ ቀውስና ሀገራዊ መክሸፍ ዋነኛ ተጠያቂ የብልፅግና መንግስት እና የእርስዎ የወደቀ አመራር ነው › ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የወነጀሉት ደሳለኝ ‹ መንግስትዎ ብልፅግናን አመጣለሁ ቢልም ያመጣው ግን ጉስቁልና ነው › ሲሉ ገልጸውታል፡፡
‹ ለወደቀው የእርስዎና የበልፅግና አመራር መፍሔው ምንድን ነው › ሲሉ የጠየቁት የምክር ቤት አባሉ የእርሳቸውን መፍትሔን ግን ካማመላከትአላመነቱም፡፡
‹ እንደ አንድ ህዝብ ተወካይ ብልፅግናም ሆነ ፓርላማው ኢትዮጵያ ከገባችበት ፖለቲካ ቅርቃር ማውጣት ስለማይችሉ ስልጣኑን ለጊዜያዊ ሲቪል አስተዳደር እንዲያስረከቡ፣ የሕዝብ እንደራሰዌች ምክር ቤት አባላትም በምክር ቤቱ ፍቃድ ምክር ቤቱን እንዲበተኑ ለአዲስ ምርጫ መንገዱን እንዲጠርጉ መጠየቅ እፍለጋለሁ፡፡ › ብለዋል፡፡
ደሳለኝ ይህን ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት የምክር ቤቱ አበላት ሲስቁ ተስተውሏል፡፡ ከዚህ ወደም በተመሳሳይ መልኩ የአብን የምክር ቤት አባል ክርስቲያን ታደለ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ‹ ስልጣን የመልቀቅ ሃሳብ እንዳላቸው › ጠይቀዋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ ‹ ስልጣን ልቀቅ ሳይሂን አብረን እንልቀቅ ነው የሚባለው › ማለታቸው ይታወሳል፡፡