ብሪክስ

ከ 5 ሰአት በፊት

እአአ በ2009 የፖለቲካ ስብሰባ በማድረግ ነው የተጀመረው። ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን ያቀፈው ብሪክስ።

ብሪክስ የሚለው መጠሪያ የእነዚህን አገራት ስም የመጀመሪያ ፊደል በመጠቀም የተፈጠረ ነው። የጎልድማን ሳክስ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጂም ኦ’ኔል ናቸው ቃሉን ያስተዋወቁት።

መጀመሪያ ላይ አፍሪካዊቷ ደቡብ አፍሪካ የስብስቡ አባል አገር አልነበረችም። በወቅቱ ስያሜው አንዳንዴ ‘ብሪክ’ አንዳንዴም ‘ብሪክስ’ እየተባለ ይጠራ ነበር። በስተመጨረሻ የምትገኘው ኤስ (S) ፊደል የአባል አገራቱን ብዛት ለማመልከት የገባች ነበረች።

በዚህም ሳቢያ የመጀመሪያው የአገራቱ ስብስብ ከአፍሪካ የሚሳተፍ አባል አገር አልነበረም። በቀጣዩ ስብሰባ ላይ ግን ደቡብ አፍሪካ ተጨምራ ብሪክስ የሚባለውን ስም ሙሉ አደረገችው።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ይህንን ኅብረት ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ባለፈው ሳምንት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መሥራቷን እንደምትቀጥል እና ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧን አሳውቀዋል።

“አሁን እየተለወጠ ባለው የዓለማችን ሁኔታ እና ከዓለም የአሰላለፍ አንጻር ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ የሚረዱ ዓለም አቀፍ ተቋሞች አባል እንድንሆን እንሠራለን። ከእነዚህ አንደኛው ብሪክስ ነው። ጥያቄ ቀርቧል” ብለዋል።

“ብሪክስ ከኢትዮጵያ ለቀረበለት ጥያቄ በጎ ምላሽ እንደሚሰጠን እንጠብቃለን” ያሉት አምባሳደር መለስ፤ “ከሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞችን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ተቋማት ጋር መሥራታችንን እንቀጥላለንም ብለዋል።

ብሪክስ ምን ያህል ጠንካራ ነው?

የብሪክስ አባል አገራት 40 በመቶውን የዓለም ሕዝብ ይይዛሉ። አምስቱ አገራት በጋራ ያላቸው ምጣኔ ሃብታዊ አቅም ደግሞ የዓለምን 26 በመቶ ይሸፍናል።

ይህ ምጣኔ ሃብታቸውም በየጊዜው እየጨመረ በዓለም የንግድ ልውውጥ ላይ ተጽዕኗቸው እያደገ ነው።

የብሪክስ አባል አገራት በተደጋጋሚ በምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ምጣኔ ሃብታቸውን በንግድ ትስስር ማሳደግ እንደሚገባም ደጋግመው መክረዋል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በአንድ ወቅት ለአባል አገራቱ ባደረጉት ንግግር “የዓለም ኢኮኖሚ ነጻ እንዲሆን መሥራት፣ በጋራ የንግድ ነፃነትን በማመቻቸት እና በማስተዋወቅ፤ አዲስ ዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት መፍጠር እና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ማሻሻያ ማድረግ አለብን” ማለታቸው ይታወሳል።

“የታዳጊ አገራት እድገት የማንንም ድርሻ አይነካም። ከዚህ ይልቅ የዓለምን የኢኮኖሚ ያሳድጋል” ሲሉም አክለዋል።

እሳቸው ይህን ቢሉም ብዙ አገራት ቻይና በወጭ ንግዶች ላይ ማግለል ትፈጽማለች በሚል ፖሊሲዎቿን ይተቻሉ።

በብሪክስ አባል አገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ከተመለከትን ወደ ቻይና ያደላ ይመስላል።

አባል አገራቱ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ ለመሠረተ ልማት እና ለዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶች ሃብት የማሰባሰብ ዓላማ ያለውን ‘ኒው ዲቨሎፕመንት ባንክ’ (ኤንዲፒ) በ2014 አቋቁመዋል።

መቀመጫውን ሻንግሃይ ቻይና ያደረገው ይህ ባንክ ትኩረቱን በንጹህ ኃይል፣ በትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣ በውሃ እና ንጽህና፣ ዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ማኅበራዊ መሠረተ ልማት ላይ አድርጓል።

አገራቱ በዓለም የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተባለለትን ኤንዲፒን ይፋ ማድረጋቸው እንደ መጀመሪያው ስኬታቸው ታይቷል።

ባንኩ በአባል አገራቱ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የመሠረተ ልማት የገንዘብ አቅርቦት ክፍተት ለመፍታት ያለመ ነው።

ኤንዲፒ እስከ 2017 ድረስ በ11 ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት አድርጓል። እስከ 2016 ብቻ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ማበደር ችሏል።

ባንኩ በድረገጹ ላይ እንዳመለከተው ከሆነ እስካሁን 96 ፕሮጀክቶችን እና 32.8 ቢሊዮን ዶላር ማጸደቁንም አስታውቋል።

የመኖሪያ ቤት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በተመለከተም የድጋፍ ይሁንታ መስጠቱንም ይገልጻል።

ያም ሆኖ ግን ባንኩ ከዓለም ባንክ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ቻይና ትልቁን የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ትመራለች። በዚህ ምክንያት አንዳንዶች አገሪቱ ለኤንዲፒ ያላትን ቁርጠኝነት ይጠራጠራሉ።

ካርታ

ብሪክስን መቀላቀል የጠየቁ አሉ?

ይህንን በማደግ ላይ የሚገኝ ኅብረት ለመቀላቀል በርካታ አገራት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑ ይገለጻል።

አንዷ ደግሞ የብራዚል ጎረቤት የሆነችው አርጀንቲና ናት። ቻይና ለጥያቄው ድጋፍ መስጠቷም ተገልጿል።

ከምዕራባዊያን ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ የምተገኘው ኢራንም ይህንን ኅብረት ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረቧን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

“አሜሪካ ማዕቀብ ለመጣል በማሰብ አሁን ደግሞ ምን ላድርግ በምትልበት ወቅት፣ ኢራን እና አርጀንቲና ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል” ሲሉ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ተናግረው ነበር።

እአአ በ2022 ደግሞ አልጄሪያ በይፋ ብሪክስ ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርባለች። አልጄሪያ ላቀረበችው ጥያቄ ቻይና እና ሩሲያ ድጋፍ መስጠታቸውን በፍጥነት አስታውቀዋል።

ሳዑዲ አረቢያ፣ አረብ ኢምሬትስ፣ ቱርክ እና ግብፅ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ካቀረቡ አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

ጥያቄ ከማቅረብ ውጭ እስካሁን ቀዳሚዎቹን አምስት አገራት ለመቀላል የቻለ አገር ግን የለም።

ከአፍሪካ አልጄሪያን እና ግብፅን ተከትሎ የብሪክስ አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረባቸውን በይፋ ካሳወቁ አገራት መካከል ኢትዮጵያ ሦስተኛዋ ትሆናለች።

አስካሁንም ስብስቡ ለቀረቡለት የአባላነት ጥያቄ የሰጠው ምላሽም ሆነ፣ ሊሰጥ ስለሚችለው ውሳኔ ምንም ፍንጭ አላሳየም።

 ቡድን 7 (ጂ7) አባል አገራት መሪዎች
የምስሉ መግለጫ,ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ አባል የሆኑበት ቡድን 7 (ጂ7) የአውሮፓ ኅብረት የማይቆጠር አባል ነው። ፎቶው የአገራቱ መሪዎች ባለፈው ግንቦት ጃፓን ውስጥ በተሰበሰቡበት ጊዜ።

ቡድን 7 (ጂ7) እና ብሪክስ

ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ጣሊያን እና ካናዳ ያካተተው ጥምረት ጂ7 (ቡድን 7) በመባል ይታወቃል።

ብሪክስ ደግሞ የዚህ የቡድን ሰባት ተፎካካሪ ግልባጭ ሆኖ ይታሰባል።

ቡድን ሰባት፣ አምስት አገራትን ካቀፈው ብሪክስ በኩል ፉክክር እንደሚገጥመው እንዲህ ያሉት የአገራት ስብስቦች የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

እንደጂ7 አባል አገራት ሁሉ የብሪክስ አባላትም በየዓመቱ ስብሰባ ያደርጋሉ። ጠንከር ያለ አጀንዳ አቅርቦ በመወያየትም የብሪክስ አባል ሃገራት ተጠቃሽ ናቸው።

የራሳቸውን የልማት ባንክ በማቋቋም ትልቅ እምርታ አስመዘግበዋል ተብለው የሚወደሱትን ያህል፣ በመካከላቸው ያለው አለመተማመንም አብሮ ይነሳል።

በሶሪያ እና በሊቢያ በነበረው ጦርነት ምክንያትም አባል አገራቱ የተለያዩ አቋሞችን ሲያራምዱ ተስተውሏል።

በምሳሌነት የሚነሳው ደግሞ ቻይና እና ሕንድ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ውስጥ የሚገኙ አባል አገራት መሆናቸው ነው።

የብሪክስ አባል አገራትን ከፖለቲካ ይልቅ ምጣኔ ሃብት እንዳስተሳሰራቸው ተደጋግሞ ታይቷል።

ከሰሞኑ የአባል አገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በደቡብ አፍሪካ ተገናኝተው ነበር። በዚህ ወቅትም ዓለም በምዕራባዊያን ከሚዘወረው ሥርዓት መውጣት እንዳለባት አንስተዋል።

የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር እንዳሉት ቡድኑ በጂኦፖለቲካ ውጥረት፣ በእኩልነት አለመኖር እና በደኅንነት ስጋት ውስጥ ላለው ዓለም መሪ ሃሳብ ይዞ መቅረቡን ገልጸዋል።

የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሻንካር ስብስቡ “ዓለም ባለብዙ መልክ ስለሆነች ባረጀው መንገድ አዲሱን አጀንዳ መፍታት አይቻልም” ብለዋል።

“ከምንጋፈጣቸው ችግሮች አንዱ የምጣኔ ሃብት ጉዳይ ሲሆን ብዙ አገራት በጥቂቶች በጎ ፈቃድ እንዲኖሩም ሆነዋል” ብለዋል።

በዚህ በኩል የጂ7 አባል አገራት በፖለቲካውም ሆነ በምጣኔ ሃብቱ ረገድ እምብዛም ልዩነት የላቸው።

በአባል አገራቱ መካከል የጎሪጥ የሚያስተያይ ይህ ነው የሚባል አጀንዳ አለመኖሩም ይነገራል።

የብሪክስ አገራት የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ፤ ከግራ ጀምሮ፡ ማ ዦዡ (የቻይና ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር)፣ ማውሮ ቪየራ (የብራዚል)፣ ናሌዲ ፓንዶር (የደቡብ አፍሪካ)፣ ሰርጌይ ላቭሮቭ (የሩሲያ)፣ ሱብራህማንያም ጃይሻንካር
የምስሉ መግለጫ,የብሪክስ አገራት የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ፤ ከግራ ጀምሮ፡ ማ ዦዡ (የቻይና ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር)፣ ማውሮ ቪየራ (የብራዚል)፣ ናሌዲ ፓንዶር (የደቡብ አፍሪካ)፣ ሰርጌይ ላቭሮቭ (የሩሲያ)፣ ሱብራህማንያም ጃይሻንካር

ቀጣዩ የብሪክስ ስብሰባ ለምን ትኩረትን ሳበ?

በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው የብሪክስ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ የዩክሬን ጦርነት ያጠላበት ነበር።

በነሐሴ ወር ደግሞ አገሪቱ የብሪክስ መሪዎችን ስብሰባ ታስተናግዳለች። ይህ ደግሞ ደቡብ አፍሪካን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከታትን ጉዳይ ይዞ ብቅ ብሏል።

ሞስኮ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ተፈጽመዋል በተባሉ የጦር ወንጀሎች በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሚፈለጉት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ጉባኤ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል እንደመሆኗ መጠን የጦር ወንጀል ማዘዣውን ተግባራዊ በማድረግ ፕሬዝዳንት ፑቲንን በቁጥጥር ስር እንድታውል ይጠበቃል።

ሆኖም ደቡብ አፍሪካ በነሐሴ ወር በምታዘጋጀው የብሪክስ አገራት ጉባኤ ላይ ለሚገኙ የውጭ አገር ባለሥልጣናት ዲፕሎማሲያዊ ያለመከሰስ መብት አወጃለች።

ይህም በጉባኤው ላይ ይሳተፋሉ ተብለው ለሚጠበቁት ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን መንገድ ያመቻቻል።

‘ዲፕሎማሲያዊ ያለመከሰስ መብቶች እና ልዩ መብቶች’ በሚል የታወጀው ይህ መመሪያ ያለመከሰስ መብቱ ለተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት እና ባለሙያዎች፣ ለየትኛውም ልዩ ኤጀንሲ ወይም ድርጅት እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ በተጠራ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ወይም ስብሰባ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ የየትኛውም አገር ተወካዮችን ያካትታል ተብሏል።

የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ የሆኑት ክሌይሰን ሞኒዬላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አዋጅ “የተለመደ” እና እንዲህ አይነት አዋጆች በደቡብ አፍሪካ ተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተደረጉ ቁጥር እንደሚወጡ መናገራቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ኃይል እንዳስታወቀው ፕሬዝዳንት ፑቲን በብሪክስ ጉባኤ ላይ ቢገኙ በቁጥጥር ስር ለማዋል ሥልጣን ስለሌለው እና እንደማይያዙም አስታውቋል።

የመከላከያ ኃላፊው ሩድዛኒ ማፍዋኒዋ ለአይሲሲ የእስር ትዕዛዝ ዕውቅና ቢሰጡም ሠራዊቱ በዓለም አቀፍ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ እንደሚሠራ እና የዲፕሎማሲያዊ ያለመከሰስ መብቶችን እንደሚያከብር ተናግረዋል።