July 9, 2023 – EthiopianReporter.com 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሐሙስ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ጉዳይ አንዱ ነበር

ዜናበአማራና በትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ላለባቸው አካባቢዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት አማራጭ መፍትሔ…

በአማራና በትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ላለባቸው አካባቢዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት አማራጭ መፍትሔ ተቃውሞ ገጠመው

ዮናስ አማረ

ቀን: July 9, 2023

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሐሙስ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ለፓርላማው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በአማራና በትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች ችግሮችን ለመፍታት በሕዝቡ ውሳኔ በማለት አማራጭ ሐሳብ ማቅረባቸው፣ በሁለቱ ክልሎች የፖለቲካ ልሂቃን ተቃውሞ ገጠመው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብ በሁለቱ ክልሎች መካከል ዘላቂ ሰላም ለመገንባት እንደማይበጅ፣ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ ልሂቃን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹ምክር እንግዳ ነው ከጋበዙት ያድራል፣ አልያም ግን ይሄዳል›› የሚል አገራዊ ብሂል ጠቅሰው ለሁለቱ ክልሎች አመራሮች በሰጡት ምክር፣ ችግሮቻቸውን በሰላምና በጥሞና እንዲፈቱ ጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹ለ30 ዓመታት ሁለቱን ክልሎች ሲያወዛግቡ የቆዩ የወሰን መሬቶችን ጉዳይ፣ ታላላቆቹ የአማራና የትግራይ ሕዝቦች በጥሞና እንዲያዩት እመክራለሁ፤›› ሲሉ የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በመሬት ምክንያት ኢትዮጵያውያን መገዳደል እንደማይኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

ሁለቱ ሕዝቦችና የሁለቱ ክልሎች አስተዳደሮች ተወያይተውና ተመካክረው ሁሉንም አሸናፊ በሆነ መንገድ ችግሩን መፍታት እንደሚችሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

‹‹ዚያድ ባሬ እስከ አዋሽ ድረስ ቢወርም የራሱ ግን አላደረገም፣ መነጣጠቅ አይጠቅምም፡፡ የተጎዳውን ጠግነን፣ የተፈናቀለውን መልሰን፣ የተጣለውን አስታርቀን በሕዝቡ ውሳኔ ነገሮችን በሕጋዊ መንገድ ለዘለቄታው መፍታት ካልተቻለ ጥፋት ነው፤›› ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ይህን በሚመለከት አስተያየት የተጠየቁ የትግራይና የአማራ የፖለቲካ ልሂቃን ግን፣ በሕዝቡ ውሳኔ ችግሩ ይፈታ መባሉ ለዘላቂ ሰላም እንማይበጅ ነው የተናገሩት፡፡

የትግራይ ክልል የቀድሞ ምርጫ ቦርድ ኃላፊ አቶ ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም፣ ችግሩ በሕዝበ ውሳኔ ሳይሆን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሳይሸራረፍ በመተግበር መፈታት አለበት ብለዋል፡፡ የቀድሞ የብአዴን ከፍተኛ አመራሩ ቹቹ አለባቸው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በሕዝቡ ውሳኔ ይፈታ የሚለው ብዙ ጦስ ይዞ የሚመጣና በጣም አደገኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የታሪክ ተመራማሪው አቶ ተስፋኪሮስ አረፈዓይኔ የትግራይ መሬት በኃይል ተይዞ ሳለ እንዲህ ዓይነት መፍትሔ መቅረቡ አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን በበኩላቸው፣ ሕዝቡ ባለፉት ዓመታት ያጣጣመውን ነፃነት ትቶ ወደ ቀደመ ተጨቋኝነት እንደማይመለስ ተናግረዋል፡፡

የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው የወልቃይትና የራያ አካባቢዎች የተነሳ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሰነድ ላይ የሁለቱ ክልሎች አጨቃጫቂ የወሰን ጉዳዮች በሕገ መንግሥታዊ አግባብ ዕልባት እንደሚያገኙ መሥፈሩ ይታወሳል፡፡

በስምምነቱ የሠፈሩ ጉዳዮች ባለፉት ስምንት ወራት ቢተገበሩም የአጨቃጫቂዎቹ የወሰን ጉዳዮች ግን እስካሁንም ዕልባት ሳያገኙ ቆይተዋል፡፡ ከሰሞኑ ይኼው ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክልሎቹን ‹‹ተነጋግራችሁ ፍቱት››፣ እንዲሁም ‹‹በሕዝቡ ውሳኔ ዕልባት ይሰጠው›› ብለው ነበር፡፡

የትግራይ ክልል የቀድሞ ምርጫ ቦርድ ኃላፊ አቶ ሙሉወርቅ፣ ‹‹ሲጀመር ምክረ ሐሳብ ለምን ይቀርባል? የፕሪቶሪያው ስምምነት ሳይሸራረፍ ይተግበር፡፡ የትግራይ ክልል ወደ ነበረበት ይመለስ፡፡ ‹‹ስታተስኮው›› ይጠበቅ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አንዱ ችግር ሳይፈታ ሌላ ችግር ይፈታ ማለት አይቻልም፡፡ ሌላ ምስቅልቅል መፍጠር ለአገሪቱ መረጋጋት ጥሩ አይሆንም፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

የፕሪቶሪያ ስምምነት አለመፍረሱን ያስታወሱት አቶ ሙሉወርቅ፣ በርካታ ሕዝብ ተፈናቅሎና ቦታዎቹ በትግራይ ክልል ሥር ሳይገቡ ሌላ መፍትሔ መደርደሩ ትርጉም እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡

‹‹የትግራይ ክልል በኢፌዴሪ ምክር ቤቶች ገና አልተወከለም፡፡ ክልሉ ወደ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፉ መመለስ አለበት፡፡ ትግራይ በሌለበት ይህን ወስነልንሃል ማለት መፍትሔ አይሆንም፤›› ሲሉ ነው አቶ ሙሉወርቅ ያስረዱት፡፡

አቶ ሙሉወርቅ አክለውም፣ ‹‹ከአማራ ክልል ጋር ችግር የለም፡፡ የትግራይን መሬት ያስወረረውም ሆነ ፋኖን ያስታጠቀው የፌዴራል መንግሥቱ ነው፡፡ እርሱ ራሱ የፈጠረውን ችግር ለምን ወደ ክልሎቹ ይመልሳል?›› በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ ቹቹ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በሰላም ተነጋግሮ ችግሮችን መፍታት ወይም በሕዝቡ ውሳኔ አማካይነት ዕልባት መስጠት ተብለው የቀረቡ ምክረ ሐሳቦች የሚጠሉ ሐሳቦች አለመሆናቸውን፣ ነገር ግን በሁለቱ ክልሎች መካከል ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር እንደማያስችሉ ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ክልሎች አመራሩም ሆነ ሕዝቡ አጨቃጫቂ የወሰን ጉዳዮችን የሞት ሽረት ጉዳዮች እንዳደረጓቸው ጠቁመው፣ በዚህ የተነሳ በንግግር ተግባብቶ ለመፍታትም ሆነ በሕዝቡ ውሳኔ ግልግል ለማድረግ እንደሚያስቸግር አስረድተዋል፡፡

‹‹ሁለቱም ካልሆኑ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው በሕግ መፍታት ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲህ ያሉ አወዛጋቢ ጉዳዮችን የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ታሪክ፣ ባህልና አኗኗር በማገናዘብ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን አለው፤›› ሲሉ ቹቹ (ዶ/ር) አማራጭ ያሉትን መፍትሔ አቅርበዋል፡፡

በሕዝብ ውሳኔ ተብሎ የቀረበውን መፍትሔ አደገኛና ብዙ ጦስ ያለው መሆኑ እየታወቀ፣ ለማለት ብቻ ተብሎ የቀረበ ሐሳብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የወልቃይትም ሆነ የራያ ሕዝብ በራሱ ላይ ዕጣ እንደማይጣጣል አክለዋል፡፡ ‹‹የፌዴራል መንግሥቱ ከዳር ቆሞ ይዋጣላችሁ ማለት ካልፈለገ በስተቀር ጉዳዩን በሕግ ይፍታ፤›› ብለዋል፡፡

የታሪክ ተመራማሪው አቶ ተስፋኪሮስ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደሙ የተሻለ አቋም ቢያንፀባርቁም ችግሩን የሚፈታ ግልጽ መፍትሔ ግን አለማቅረባቸውን ነው የተናገሩት፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጀመርያ የወሰን አካባቢዎቹ ወደ ትግራይ ይመለሱ ብለው በግልጽ መናገር አለባቸው፡፡ በመጀመርያ ኢሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ የተያዘው መሬት መለቀቅ አለበት፡፡ ወደ ነበረበት ወደ ትግራይ ከተመለሰ በኋላ ሕገ መንግሥታዊ አፈታቱ መታየት ይችላል፤›› በማለት ነው አቶ ተስፋኪሮስ ሐሳባቸውን የሰጡት፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉዓለም፣ ‹‹የወልቃይት ሕዝብ አማራ ነኝ እንጂ አማራ ልሁን አላለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕወሓት ጫና የደረሰባቸው ሲመስላቸው ሰኔ 2013 ዓ.ም. እንዳደረጉት የወልቃይት ሕዝብ አነስ ሲል በጌምድር፣ ከፍ ሲል ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ነው ይላሉ፡፡ ሕወሓት ለሥልጣን አሥጊ አይደለም ብለው ባሰቡ ጊዜ ደግሞ ሰኔ 2015 ዓ.ም. እንዳደረጉት ችግራችሁን በሕዝቡ ውሳኔ ፍቱ በማለት ይናገራሉ፡፡ ይህ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ዓይነት አቋም ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሕወሓት ሥር ለ30 ዓመታት በቆዩ አካባቢዎች ያለው ሕዝብ ባለፉት ሁለት ዓመታት አንፃራዊ ነፃነትና ሰላም ማግኘቱን ያወሱት አቶ ሙሉዓለም፣ ሕዝቡ ወዳሳለፈው ሰቆቃ የሚመልሰው ነገር እንደማይፈልግ ገልጸዋል፡፡

‹‹በተለይ የወልቃይት ጉዳይ የሃይማኖት አክራሪነት፣ አደገኛ ኮንትሮባንድና ደካማ አስተዳደር ካላቸው የቀጣናው አገሮች ጋር ሊተሳሰር ይችላል፡፡ አካባቢው የጎረቤት አገሮችን የሚያዋስን በመሆኑ ወደ ቀጣናዊ ቀውስ እንዳይሸጋገር ጥንቃቄ ይደረግ፤›› ሲሉ ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

የአማራና የትግራይ ክልሎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአመራር ደረጃ መቀራረብ መጀመራቸው አጨቃጫቂ የወሰን ጉዳዮችን ይፈታል የሚል ትልቅ ተስፋ አሳድሯል፡፡ መቀራረቡ የፖለቲካ መተማመን ለመፍጠር ጥሩ ጅማሮ ቢሆንም፣ የወልቃይትና የራያ ጉዳይን ለመፍታት ገና ብዙ መንገድ እንደሚቀር በርካቶች ያምናሉ፡፡