
July 9, 2023 – EthiopianReporter.com

በቋራና በመተማ ወረዳዎች ታጣቂዎች ታጋቾችን መግደላቸው ተነገረ
July 9, 2023
- የሸዋ ሮቢት ፖሊስ ባልደረባም ተገድለዋል
በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን በቋራና በመተማ ወረዳዎች፣ ታጣቂዎች ላገቷቸው ሰዎች ክፍያ ካልተጸመላቸው እንደሚገድሏቸው ቤተሰቦች ተናገሩ፡፡
የታጋች ቤተሰቦች ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት ታጣቂዎች በርካታ ሰዎችን አግተዋል፡፡ ለእያንዳንዳቸው ታጋቾች ከ300 ሺሕ ብር እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደሚጠይቁ ገልጸው፣ የጠየቁትን ገንዘብ ካላገኙና ታጋቾች ለማምለጥ ጥረት ካደረጉ ይገድሏቸዋል ብለዋል፡፡
ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው ሦስት የቋራና የመተማ ወረዳ ነዋሪዎች፣ ታጣቂዎች ሰዎችን ስለሚያግቱ ማኅበረሰቡ ሥጋት ውስጥ ናቸው ብለዋል፡፡ ታጣቂዎች የጠየቁትን ገንዘብ ባለማግኘታቸው ሦስት ሰዎችን መግደላቸውን፣ በዕገታ ወቅት ለማምለጥ ሲሞክሩ የሞቱ ሰዎች እንዳሉም አስረድተዋል፡፡
ምን ያህል ሰዎች እንደታገቱ፣ ታጣቂዎቹ እነማን እንደሆኑ፣ የታገቱበት ቦታ የት እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቤተሰቦች በሰጡት ምላሽ ጥቃቱ በየወቅቱ ስለሚፈጸም የታጋቾችን ብዛትና የታጣቂዎቹን ማንነት በትክክል ማወቅ አይቻልም ብለዋል፡፡ የእነሱ ቤተሰብ አባላት የታገቱት በተለይ በምዕራብ ጎንደር መተማ ወረዳ ‹‹ለምለም ተራራ›› በተሰኘ አካባቢ እንደሆነ፣ ጥቃት ፈጻሚዎቹና አጋቾቹ ደግሞ የቅማንት ታጣቂዎች መሆናቸውን መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ታጣቂዎቹ በመተማና በቋራ ወረዳዎች፣ በተለይ በሱዳን ድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች ዕገታ እንደሚፈጽሙ አክለው ተናግረዋል፡፡
የምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ፈንታሁን ዓለሙ፣ በታጣቂዎች እየደረሰ ነው የተባለውን ጥቃት በማስመልከት ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዞኑ በተለይም በሱዳን ድንበር አካባቢ ዕገታና ግድያ እንዳለም ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. አማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ወቅት ከተማ አባ ጀምበር ቀበሌ ታጣቂዎች ሾፌርና ረዳት መግደላቸውን፣ የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መረጃ መሠረት ግድያውን ፈጸሙ ከተባሉ ሁለት ሰዎች መካከል ፖሊስ ባደረገው ክትትል፣ ዓርብ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. አንዱ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ማንነታቸው አልታወቀም የተባሉ ሰዎች፣ በሸዋ ሮቢት ከተማ የፖሊስ ባልደረባ ምክትል ሳጅን ያለለት ደጉ ላይ ግድያ መፈጸማቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት የከተማው የፀጥታ ኃላፊ በታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል ከሁለት ሳምንታት በፊት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ በተባለ ቦታ የሸኔ ታጣቂዎችና አገቷቸው የተባሉ በርካታ ሾፌሮች ከፊሎቹ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እየከፈሉ እንደተለቀቁ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ እንዳልተለቀቁ ሪፖርተር ከሾፌሮች ቤተሰብ አረጋግጧል፡፡
ዕገታውን በተመለከተ ምን እየተደረገ እንደሆነ ሪፖርተር በተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀረበላቸው የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አራርሳ መርዳሳ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሐሙስ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በነበራቸው የፓርላማ ውሎ፣ የፀጥታውን ችግር የከፋ ደረጃ እንደደረሰ ገልጸው መንግሥት መፍትሔ እንዲፈልግ ሲጠይቁ ተደምጠዋል፡፡
ለአብነትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ ‹‹ዜጎች በጠራራ ፀሐይ ይታገታሉ፣ በሚሊዮን ብር ይጠየቅባቸዋል፣ ሙሉ አማራ ክልል አዲስ የጦርነት ቀጣና ተደርጓል፣ ከፊል ኦሮሚያ ክልል በጦርነት ባጅቷል፣ መንግሥት ብልፅግና አመጣለሁ ቢልም በተግባር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያመጣለት ጉስቁልና ሆኗል፤›› ብለው ነበር፡፡
ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ አኔሳ መልኮ፣ ‹‹የአመራሮችና የዜጎች ግድያና ዕገታ፣ የፀጥታ ኃይሎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት በተቀናጀ መንገድ እየተፈጸመ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ታጣቂዎች የሚፈጽሙትን ዕገታና ግድያ በተመለከተ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹በየቦታው ሽፍቶች አሉ፡፡ በእኛ በኩል የሚሠራውን መሥራት ይኖርብናል፡፡ በእነሱ በኩል ደግሞ ሕግ ማስከበርና በድርድር የሚመለስ ካለም እያዩ መሄድ ጠቃሚ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡
በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ዘውዱ ታደለና ምክትላቸው ኢንስፔክተር ወርቁ ሽመልስ፣ ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በግለሰብ ግድያ ሲፈጸምባቸው፣ ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውንና ጥቃቱን በተመለከተ ፖሊስ ምርመራ መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡