July 10, 2023 – Konjit Sitotaw
በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ በታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ 18 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ በታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ 18 ሰዎች መገድላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ችግሩ የተከሰተው አርብ ሰኔ 30/2015 ሲሆን፤ ከ8 በላይ ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ እንደሚገኙም ታውቋል፡፡
እንደነዋሪዎቹ ገለጻ የችግሩ መነሻ፤ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለሥራ በወጣበት ተገድሎ በመገኘቱ አስከሬኑን ለማምጣት በሄዱ የጸጥታ አካላት ላይ በአካባቢው የሚገኙ የጉምዝ ታጣቂዎች ተኩስ በመክፈታቸው ሲሆን፤ በዚህም በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል፡፡
ተኩሱን የከፈቱት ሽፍታ የነበሩ እና የሰላም ተመላሽ ተብለው ትጥቃቸውን ሙሉ ለሙሉ ለመንግሥት እንዲያሰረክቡ ከተጠየቁ ታጣቂዎች መካከል ትጥቅ ያልፈቱ እና በጫካ የሚኖሩ ታጣቂዎች መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
ተኩሱ የተከፈተው አርብ ምሽት 12 ሰዓት አካባቢ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ በተከፈተው ተኩስ አራት የጸጥታ አካላትና 14 በትራንስፖርት መኪና ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎች መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱ የተፈጸመው ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ፓዊ መወጫ ቻይና ካምፕ ተብሎ በሚጠራ ቦታ እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን፤ ከተገደሉት 18 ሰዎች በተጨማሪ ከ8 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሶ ወደ ፓዊ ሪፈራል ሆሰፒታል መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በግልገል በለስ ከተማ እና አካባቢዋ የትራንሰፖርት እና የሰው እንቅስቃሴ መታገዱን አክለዋል፡፡
ሥማቸውን መግለጽ ያለፈለጉ የመተከል ዞን የግልገል በለስ ከተማ የፖሊስ አባል፤ አርብ ዕለት በተከፈተው ተኩስ ማታ ላይ ከአንድ አካባቢ ከአራት በላይ ሰዎች ሞተው መገኘታቸውን ጠቁመው፤ የጸጥታ አካላት ወደ አካባቢው ሂደው የማረጋጋት ሥራ እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡
“በታጣቂዎቹ በተከፈተው ተኩስ ምን ያክል ሰዎች እንደሞቱ እስካሁን በትክክል አልታወቀም።” ሲሉ ነው የፖሊስ አባሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፡፡
አካባቢው ባለፉት ተከታታይ ሦስተትና አራት ዓመታት በከፍተኛ የጸጥታ ችግር ውስጥ ከቆየ በኋላ፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምንት ካደረጉ በኋላ የሰዎች ግድያ ቆሞ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ታጣቂዎቹ ትጥቅ አለመፍታታቸውን ተከትሎ በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች ስጋቶች መኖራቸውን አዲስ ማለዳ ከሰሞኑ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላትን ጠቅሳ መዘገቧ የሚታወስ ነው፡፡