በኢቲ 302 አደጋ ሕይወታቸውን ካጡት መካከል እንግሊዛዊው የ25 ዓመት ወጣት ሳም ፔግራም አንዱ ነው።
የምስሉ መግለጫ,በኢቲ 302 አደጋ ሕይወታቸውን ካጡት መካከል እንግሊዛዊው የ25 ዓመት ወጣት ሳም ፔግራም አንዱ ነው።

9 ሀምሌ 2023

ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር በተከሰከው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተሳፍረው ከነበሩት መካከል ብሪታኒያውያን የሟች ቤተሰቦች ዘመዶቻቸው በሕግ ተቀባይነት በሌለው ሁኔታ ተግድለዋል የሚል ውሳኔ ፍርድ ቤት እንዲሰጥ ጠየቁ።

በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈው የሦስቱ ብሪታኒያውያን ቤተሰቦች ነገ ሰኞ በሆርሻም ሰሴክስ የሚሰየመው ፍርድ ቤት፣ በዘመዶቻቸው ላይ በአውሮፕላን አደጋው ምክንያት በተከሰተው ሞት ላይ ውሳኔ ይሰጣል ብለው ተስፋ አድርገዋል።

ከሳሾች በአውሮፕላን አደጋው ሕይወታቸውን ላጡት የቤተሰብ አባሎቻቸው ሞት ተጠያቂ የሚሆን በግድየለሽነት ነፍስ በማጥፋት ወንጀል ተከሶ በፍርድ አደባባይ የሚጠየቅ ሰው መኖር አለበት ብለው ነው እየተከራከሩ ያሉት።

ከአራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲያቀና ነበር ከቦሌ እንደተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ተከስክሶ 157 ሰዎች በሙሉ ያለቁት።

ለቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን መከስከስ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ዲዛይን ስህተት መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ለአደጋው ተጠያቂ ተደርጎ ነበር።

ከኢትዮጵያ አየር መንግድ አደጋ አንድ ወር ቀደም ብሎ ሌላ የኢንዶኔዢያ ተመሳሳይ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ተከስክሶ 189 ቢሞቱም፣ አውሮፕላኑ አገልግሎት መስጠት እንዲቀጥል መደረጉ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ላይ ተገጥሞ የነበረው ኤምካስ የተባለው የመቆጣጠሪያ ሥርዓት የአውሮፕኑን አፍንጫ ከአብራሪዎች ቁጥጥር ውጪ ወደታች በመዘቅዘቅ ለአደጋው መንስዔ ሆኗል።

ቦይንግ ዘግይቶም ቢሆን በኢቲ-302 ላይ ለጠፋው ሕይወት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አምኖ፣ ማክስ አውሮፕላኖችም የዲዛይን ማሻሻያ እስኪደረግላቸው ድረስ በመላው ዓለም እንዳይበሩ ታግደው ነበር።

ይህ ተከትሎ ቦይንግ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር እአአ 2021 ላይ በደረሰው ስምምነት ኩባንያው በአደጋው ምክንያት በሕግ እንደማይጠቅ እና ለተጎጂዎች ቤተሰቦች ካሳ እንዲሁም ለቅጣት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማምቶ ነበር።

ይህ ስምምነት ከመገናኛ ብዙኃን ተደብቆ፤ የተጎጂ ቤተሰቦች ሳያውቁ በስውር የተከናወነ ነበር። የአሜሪካ መንግሥት እና ቦይንግ የደረሱት ስምምነት ተፈጻሚ እንዳይሆንም የፍርድ ቤት ክርክር ሲደረግ ቆይተዋል። እስካሁን ግን የተገኘ ውጤት የለም።

ታዲያ ብሪታኒያውያኑ የቤተሰብ አባላት አሁን ላይ ለዘመዶቻችን ሞት ተጠያቂ ተደርጎ እስር ቤት መውረድ የሚኖርበት ሰው መኖር አለበት ብለው ተነስተዋል።

በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት መካከል አንዱ ሳም ፔግራም ይባላል። የሳም ወንድም የሆነው ቶም ፔግራም ቤተሰቡ ባለፉት አራት ዓመታት ለወንድሙ ፍትሕ እና ለእነርሱ ካሳ ለማስገኘት ትልቅ ተጋድሎ ቢያደርግም እስካሁን ፍትሕ አላገኘንም ይላል።

ቶም በወንድሙ ሳም ሞት እስካሁን ተጠያቂ የሆነ ሰው አለመኖሩ እጅግ እንደሚያበሳጨው ይናገራል።

“በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ተጠያቂ መሆን የነበረበት ሰው እያለ ምንም አለመደረጉ እንዴት በፍትሕ እንመን? ፍትሕ ቢኖር ኖሮ በሳምንታት ወይም በወራት ውስጥ መታሰር የነበረበት ሰው ነበር። ግን እስከ ዛሬ ዕለት ድረስ ይህ አልሆነም” ይላል።

በዩናይትድ ኪንግደም ሕግ መሠረት ፍርድ ቤት ተሳፋሪዎቹ ሕይወታቸው ያለፈው በሕግ ተቀባይነት በሌለው መንገድ ነው የሚል ውሳኔን የሚያሳልፍ ከሆነ ፖሊስ በወንጀሉ ጥፋተኛ የሆነው ለመለየት እና ለመክሰስ ምርመራ እንዲከፍት ያደርጋል።