የስፔን የአደጋ ጊዜ መርከብ

ከ 4 ሰአት በፊት

የስፔን አደጋ ጊዜ ሠራተኞች 200 አፍሪካዊያን ስደተኞች ጭና በከኔሪ ደሴት የጠፋችውን ጀልባ እያፈላለጉ መሆኑ ተገለጸ።

ጀልባዋ ከጠፋች ከአንድ ሳምንት በላይ ሆኗታል።

ዎኪንግ ቦርደርስ የተሰኘው የተራድዖ ድርጅት እንደሚለው ዓሣ አጥማጇ ጀልባ 1700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው የደቡብ ሴኔጋል የባሕር ዳርቻ ካፉንቲን ነው የተነሳችው።

ድርጅቱ አክሎ እንደገለጠው ጀልባዋ በርካታ ሕፃናትን አሳፍራለች።

ሁለት ተመሳሳይ ጀልባዎችም በርካታ ግለሰቦችን እንደጫኑ መጥፋታቸው እየተነገረ ነው።

200 ስደተኞችን አሳፍራ ከካፉንቲን በፈረንጆቹ ሰኔ 27 የተነሳችው ጀልባ ወደ ከኔሪ ደሴቶች እያቀናች ነበር።

ስለሌሎቹ ሁለት የጠፉ ጀልባዎች እስካሁን ብዙ መረጃ አልተገኘም።

ሮይተርስ፤ የዎኪንግ ቦርደርሷን ሄሌና ማሌኖን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው አንደኛው ጀልባ 65፤ ሌላኛው ደግሞ 60 ገደማ ሰዎች አሳፍረዋል።

በጠቅላላው የጠፉት ሶስት ጀልባዎች ቢያንስ 300 ሰዎች ጭነዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በግሪክ ድንበር እንዲት መርከብ ሰጥማ 78 መሞታቸው፤ እንዲሁም 500 ያክል ደግሞ መጥፋታቸው ይታወሳል።

ከምዕራብ አፍሪካ ወደ ከኔሪ ደሴቶች በጀልባ የሚደረገው ጉዞ ለስደተኞች እጅግ አደገኛ ነው።

አብዛኛዎቹ ስደተኞች አነስ ባለች ዓሣ አስጋሪ ጀልባ ስለሚጓዙ በአትላንቲክ ባሕር ነፋስ የመገልበጥ ዕድላቸው የሰፋ ነው።

ባፈው ዓመት ቢያንስ 559 ሰዎች ወደ ስፔን ደሴቶች ለመሻገር ሲሞክሩ መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት [አይኦኤም] ይገልጣል።

በ2021 ደግሞ በተመሳሳይ በዚህ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሞከሩ 1126 ሰዎች የውሃ ሲሳይ ሆነዋል።

ድርጅቱ እንደሚለው በፈረንጆቹ 2022 ከ15 ሺህ በላይ ስደተኞች በከኔሪ ደሴቶች በኩል አቋርጠው መጥተዋል።

ከኔሪ ደሴቶች የሰፔን አካላት ሲሆኑ መነሻቸውን ምዕራብ አፍሪካ ያደረጉ ስደተኞች አውሮፓ ለመድረስ በደሴቶቹ አቅጣጫ ያልፋሉ።

ይህ የምዕራብ አፍሪካ-አትላንቲክ የስደተኞች መተላለፊያ መንገድ እጅግ አደገኛው ተደርጎ ይወሰዳል።

በዚህ አቅጣጫ የሚጓዙት መርከቦች መነሻቸው ብዙ ግዜ ከሞሮኮ፣ ማሊ፣ ሴኔጋል እና ኮት ዲቯር ያደረጉ ናቸው።