ሞባይል

ከ 5 ሰአት በፊት

ትንሽ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች የሪዮ ግራንዴ ወንዝን ቡናማውን ድፍርስ ውሃ ሲመለክቱ ፈገግ አሉ።

ይህ ማለት ስንት በረሃ አቋርጠው የመጡለት የአሜሪካ ድንበር ከጥቂት መቶ ሜትሮች በኋላ ይገኛል ማለት ነው።

“ወንዙን በጥንቃቄ ስንሻገር” ይላል ይህን ትዕይንት ያዘለው ተንቀሳቃሽ ምስል።

በስፓኒሽ ቋንቋ የአሜሪካ ሕልም (#AmericanDream) ከተለጠፈበት መልዕክት ሥር “ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ይፃፉልኝ” የሚል ጥቆማ ሰፍሯል።

ይህ ቪድዮ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ “ወደ አሜሪካ ጫፍዎ ሳይነካ በትንሽ ገንዘብ እናስገባዎታለን” ከሚሉ በርካታ ቪድዮዎች አንዱ ነው።

ምንም እንኳ እኒህ ቪድዮዎች ከጀርባቸው ምንም ያለ ባይመስል፤ ኧረ እንደውም በጣም ጠቃሚ መረጃ ያዘሉ ቢመስሉም አደገኛ መልዕክት ይዘዋል ይላሉ ባለሙያዎች።

“ይህ እኮ ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር ማስታወቂያ ነው። ያም ሆኖ ያለማንም አጋጅ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ይዘዋወራል።”

ይህን የሚለው ድንበር አካባቢ ያለውን ሁኔታ በደንብ የሚያውቀው የቀድሞ የሜክሲኮ ፖሊስ መኮንኑ ኤድ ካልዴሮን ነው።

ሙያተኞች እንደሚሉት እኒህ ቪድዮዎች ቲክቶክ፣ ዩቲዩብ እና ዋትስአፕን በመሳሰሉ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ይዘዋወራሉ።

ከቪድዮዎቹ ጀርባ በቅርቡ የተቀየረውን የአሜሪካ ፖሊሲ ተገን አድርጎ ግርታ በመፍጠር እና የተዛባ መረጃ በማስፋፋት የተካነ የቢሊዮን ዶላሮች ኢንዱስትሪ አለ።

ስደተኞች አሜሪካ-ሜክሲኮ ድንበር አካባቢ

ግንቦት 11/2023 (እአአ) ከመድረሱ በፊት ገበያው ጦፎ ታይቷል።

“ታይትል 42” የተባለው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ያወጁት ማንኛውም ስደተኛ የጥገኝነት ጥያቄው ሳይሰማ ይመለስ የሚለው ሕግ ማብቂያው ግንቦት 11 ነበር።

በአዲሱ ሕግ መሠረት ስደተኞች ሕጋዊ መንገድ ተጠቅመው እንዲገቡ ይፈቅድላቸዋል፤ በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲመጡ ግን በፍፁም አይፈቀድም።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ታይታል 42 ተግባራዊነቱ ካበቃ በኋላ በሕገ-ወጥ መንገድ የመጡ ስደተኞች ቁጥር እሥር በ70 በመቶ ቀንሷል። በርካቶች በሕጋዊ መንገድ እየመጡ ነው።

ይህ ማለት ግን ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ቢዝነሳቸው ቀነሰ ማለት አይደለም።

“ለሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ጊዜው ልክ እንደ ገና በዓል ነው” ይላል ካልዴሮን።

የስደተኞች እና የድንበር ባለሙያው አዳም ኢካሶን፤ ታይትል 42 ከተሰረዘ በኋላ “ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በሕገ-ወጥ መንገድ መግባት የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል” ይላል።

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የሚታዩ በርካታ ቪድዮዎች በተለያየ ዓይነት የሚቀርቡ ናቸው።

አንዳንዶቹ ከቢዝነሱ የተጠቀሙ እና እርካታ ያገኙ ደንበኞችን ምስክርነት የሚያሳዩ ናቸው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ተሳካልን የሚሉ ሰዎች ከቤት ውስጥ እና በአሜሪካ ከተሞች መንገድ ዳር ሆነው የሚታዩ ናቸው።

“እነሆ ኒው ዮርክ ከተማ ነው ያለነው” ይላል አንድ የቬኒዝዌላ ዘየ የሚጫነው ተራኪ የማንሐታን መንገድን እያቋረጠ።

“ምንም ነገር ሳልሆን እዚህ ያደረሱኝን ሰዎች ላመሰገን እወዳለሁ።”

ይህ የለጠፈው የጉዞ ወኪል (ትራቭል ኤጀንት) ሌሎችም ወደ አሜሪካ ያለምንም ቪዛ መግባት ከፈለጉ በውስጥ መስመር መልዕክት እንዲያስቀምጡ ይመክራል።

አንዳንዶቹ ደግሞ የወታደር ልብስ ያደረጉ ሰዎች በረሃ ለበረሃ ስደተኞችን ይዘው ሲጓዙ፤ አሊያም የአሜሪካ ድንበር ላይ የቆመውን አጥር በመሰላል ሲወጡ ያስመለክታሉ።

አብዛኛዎቹ ወኪሎች ከደቡብ አሜሪካ ጫፍ ድረስ እስከ አሜሪካ ድንበር ድረስ ያለምንም ሰቀቀን እንደሚያደርሱ ቃል ይገባሉ።

ሁሉም ማለት ይቻላል የዋትስአፕ ቁጥር የተካተተባቸው ማስታወቂያዎች ናቸው። ለበለጠ መረጃ እዚህ ቁጥር ላይ ይፃፉልን ከሚል መልዕክት ጋር ነው የሚለጠፉት።

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የሚለጠፉ መልዕክቶችን ተመልክቶ የትኛው ትክክለኛ፤ የትኞቹስ ሐሰተኛ? ምን ያክል ሰውስ እኒህን ተማምኖ ይጓዛል? የሚለውን ለመለየት አዳጋች ነው።

ዘርፉን የሚያጠኑ ሙያተኞች እንደሚሉት የሕገ-ወጥ ሰው ዝውውር ዋጋ በስደት ከአንድ አገር ወደ ሌላ ለመዘዋወር እንዳቀደው ግለሰብ የመክፈል አቅም ይለያያል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚሉት መክፈል የማይችሉ ስደተኞች አንዳንድ ጊዜ ለዕፅ አዘዋዋሪዎች ተላልፈው ይሰጣሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ሴተኛ አዳሪ ይሆናሉ።

የተቀሩት ማጎሪያ ውስጥ ተቀምጠው አገር ቤት አሊያም አሜሪካ የሚገኝ ዘመድ እስኪከፍል ድረስ ይጠብቃሉ።

ስደተኞች አሜሪካ-ሜክሲኮ ድንበር አካባቢ

“ትልቅ ኢንዱስትሪ ነው። ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወር በጣም ገቢ የሚያስገኝ ሆኗል” ይላል ካልዴሮን።

የቀድሞው የፖሊስ መኮንን እንደሚለው ከሜክሲኮ ተነስቶ አስከ አሜሪካ ድንበር ለመሄድ አራት ሰዎችን ለያዘ ቤተሰብ ዝቅተኛው ዋጋ ከ5 እስከ 8 ሺህ ዶላር ይደርሳል።

የደኅንነት ሙያተኞች እንደሚሉት ደግሞ አሁን መደበኛው ዋጋ 15 ሺህ ዶላር ደርሷል። ከደቡብ አሜሪካ ውጭ ለሚመጡ ደግሞ እስከ 50 ሺህ ሊጠየቅ ይችላል።

ቢቢሲ ስደተኞች ለሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች የሚከፍሉትን ገንዘብ መጠን በራሱ ሊያረጋግጥ አልቻለም።

ሕገ-ወጥ ዝውውርን በተመለከተ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ትኩረት ስበዋል።

“ታይትል 42” የተባለው ሕግ ተግባራዊነቱ ከማብቃቱ በፊት የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትሩ አሌሃንድሮ ማዮርካስ ስደተኞች በሐሰተኞች እንዳይታለሉ አስጠንቅቀው ነበር።

አልፎም የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴር በመካከለኛው እና ደቡብ አሜሪካ ስለሰዎች ዝውውር የሚያስተምር ማስታወቂያ በማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ ለቋል።

ቲክቶክ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ የሚሰራጩ ይዘቶችን “እንደማይታገስ” ገልጦ፣ መሰል መልዕክቶችን ለማስወገድ እና አካውንቶችን ለመዝጋት “በቂ ኢንቨስትመንት” መመደቡን አስታውቋል።

እዚህ ፅሑፍ ላይ የተጠቀሱት ሁለት ቪድዮዎች ቢወገዱም፣ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው በርካታ ምስሎች አሁንም ይንሸራሸራሉ።

ብዙውን ጊዜ አዘዋዋሪዎቹ የሚጠቀሙት መንገድ “አሁን ካልሄዳችሁ ሁኔታዎች እየባሱ ይሄዳሉ” የሚል እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ የሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችን ሥራ እንዳያባብሰው ተሰግቷል።