
ከ 4 ሰአት በፊት
በአመጽ ስትታመስ የቆየችው ፈረንሳይ በቅርቡ ለሚከበረው ‘ባስቲል ደይ’ በዓል ርችት መግዛትም ሆነ ማከማቸት አሊያም ማጓጓዝ ታግዷል አለች።
የሃገሪቱ መንግሥት ዕሑድ ዕለት በፈረንጆቹ ሐምሌ 14 ለሚከበረው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቀን ማንኛውም ሰው ተቀጣጣይ ነገር መግዛት እንደማይችል ገልጧል።
ባለፈው ወር የ17 ዓመቱ ታዳጊ ናሄል ኤም በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ በሃገሪቱ ከባድ አመፅ ተነስቶ ነበር።
መንግሥት በዓል ማድመቂያ ተቀጣጣይ ቁሶች ሽያጭና ግዥን የከለከለው ይህን ተከትሎ ነው።
ነገር ግን በመንግሥት የሚዘጋጁ የርችት ማቀጣጠል ሥነ-ሥርዓቶች በተያዘላቸው ጊዜ መሠረት እንደሚለኮሱ ተገልጧል።
“ሐምሌ 14 ለሚከበረው በዓል የሕዝቡ ሰላም እንዲጠበቅ ሲባል ርችትና ሌሎች ተቀጣጣይ ቁሶችን መግዛት፣ ማጓጓዝና መጠቀም የተከለከለ ነው” ሲል መንግሥት አውጇል።
- በጀርመን የኤርትራ ፌስቲቫል ላይ በተከሰተ ግጭት 26 ፖሊሶች ሲጎዱ 100 ኤርትራውያን ታሰሩ9 ሀምሌ 2023
- የአገሪቱ ባለሥልጣናት መነጋገሪያ የሆነው ከነፍሳት የሚሠራው የጣልያን ፓስታከ 5 ሰአት በፊት
- ምዕራባውያን አገራት አሜሪካ ክላስተር ቦምቦችን ለዩክሬን ለመላክ መወሰኗ አሳሰቢ ነው አሉ9 ሀምሌ 2023
ፈረንሳይ ባለፉት 20 ዓመታት ካየቻቸው የከተማ አመፆች እጅግ የከፋው ነው የተባለለት ባለፈው ወር የተከሰተው አመፅ በርካታ ውድመት አስከትሏል።
በዚህ አመፅ ወቅት በርካቶች ርችትን እንደመሣሪያ ሲጠቀሙ ተስተውለዋል።
ለወትሮውም ቢሆን የባስቲል ደይ አከባበር ታዳጊዎች መንገድ ላይ በሚለኩሱት ተቀጣጣይ ቁስ ምክንያት ይረበሻል።
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሊሳቤት ቦርን ተቀጣጣይ ነገር መከልከሉም ብቻ ሳይሆን በበዓሉ ቀን “እጅግ በርካታ” የፀጥታ ሰዎች እንደሚሰማሩ አሳውቀዋል።
“ሰላም እንዲሰፍንና በዓሉ በሚከበርባቸው ሁለት ቀናት ፈረንሳይን ለመጠበቅ” ነው ይህን የምናደርገው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሯ።
ሌ ፓሪዚያን ለተሰኘው ጋዜጣ ድምፃቸውን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሯ ‘ባስቲል ደይ’ ሲከበር ድጋሚ አመፅ እንዳይቀሰቀስ በርካቶች “ስጋት ገብቷቸዋል” ይላሉ።
ባለፈው ወር በተከሰተው አመፅ ምክንያት 3700 ገደማ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ከእነዚህ መሐል 1160 የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች ናቸው።
‘ባስቲል ደይ’ የተሰኘው የፈረንሳይ ብሔራዊ ክብረ በዓል፤ ከ200 ዓመት በፊት የተቀሰቀሰውን የፈረንሳይ አብዮት የሚዘክር ነው።