በፖሊስ የተያዙ ተቃዋሚዎች

ከ 26 ደቂቃዎች በፊት

ባለፈው ቅዳሜ በጀርመኗ ጊሰን ከተማ በተከሰተው ረብሻ ተሳትፈዋል በተባሉ 125 ኤርትራውያን ላይ የወንጀል ክስ መመስረቱን የአገሪቱ ፖሊስ ገለጸ።

ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም. ቅዳሜ በጊሰን ከተማ ከኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅት ጋር ተያይዞ በተፈጠው ሁከት በርካታ የጀርመን ፖሊስ አባላት ላይ እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።

ይህ በኤርትራውያን አማካይነት የተከሰተው ሁከት በከተመዋ ውስጥ ስጋትን ፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ የጀርመን ፖለቲከኞችን እና ባለሥልጣናትን አስቆጥቷል።

የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ናንሲ ፌይሰር ለበርካታ የጀርመን ፖሊስ አባለት መጎዳት ምክንያት የሆነውን ግጭት አጥብቄ አወግዛለሁ ብለዋል።

የጊሰን ከተማ ከንቲባ ፍራንክ ቲሎ ቢቸር ደግሞ የጊሰን ጎዳናዎች “የወንጀል ደርጊት ሲፈጸምባቸው ተመልክተናል” ካሉ በኋላ፣ በሁከቱ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ዕለታዊ እንቅስቃሴ ተገድቧል ብለዋል።

ፖሊስ ቅዳሜ ዕለት በተከሰተው ሁከት ተሳታፊ ናቸው ያላቸውን 131 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ያዋለ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል በ125ቱ ላይ የወንጀል ክስ መሥርቷል።

የአገሪቱ ፖሊስ በጊሰን ከተማ የተዘጋጀውን የባሕል ፌስቲቫል ለማወክ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያንን ለመበተን ዱላ እና ዐይን የሚያቃጥል ፈሳሽ ረጭቷል፤ ፖሊስ ሄሊኮተፕር ጭምር በአካባቢው አሰማርቶ ነበር።

የባሕል ፌስቲቫሉን በመቃወም ለማወክ ጥረት ቢደረግም፣ ፌስቲቫሉ በተያዘለት መረሃ ግብር መሠረት ተካሂዶ እሁድ ዕለት ተጠናቋል።

ሁከቱ የተፈጠረው በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች የተዘጋጀ ነው የተባለውን ዝግጅት ለማወክ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች ፌስቲቫሉ ወደሚካሄድበት ቦታ በኃይል ለመግባት ጥረት ማድረጋቸውን ተከትሎ ስለመሆኑ የጀርመን መገናኛ ብዙኃን በስፋት ዘግበዋል።

የባሕል ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱን በመቃወም አደባባይ የወጡ፤ ፌስቲቫሉ ለኤርትራ መንግሥት ፕሮፖጋንዳ የተዘጋጀ ነው ይላሉ።

የጀርመን ጊሰን ከተማ ቅዳሜ ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም. የተከሰተው ሁከት እና ግጭት ለሰዓታት መቆየቱን እና ቢያንስ 26 የፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት መድረሱ ገልጿል።

ሁከቱን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፖሊስ አባልት ተሰማርተው የነበረ ሲሆን፣ ጉዳት ከደረሰባቸው የፖሊስ አባላት መካከል በሰባቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አመልክቷል።

አሶሺዬትድ ፕሬስ የጀርመን ፖሊስን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ሁከቱን ለመቆጣጠር 1 ሺህ የፖሊስ አባላት፣ ሄሊኮፕተር እና ውሃ በከፍተኛ ኃይል የሚረጭ አድማ በታኝ መኪና ተሰማርቶ ነበር።

በጀርመኗ ከተማ የተከሰተውን ግጭት የሚያሳዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ በአብዛኛው ወጣት የሆኑ ኤርትራውያን ድንጋይ ወደ ፖሊስ ሲወረውሩ እና በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ ፖሊስ ሲያባርራቸው ታይተዋል።

ፖሊስም ተቃዋሚዎቹ በሕግ አስከባሪ ኃይል አባላት ላይ ጠርሙስ፣ ድንጋይ እና የጭስ ቦምብ መወርወራቸውን፣ ተሸከርካሪዎችን ማውደማቸውን እና ፌስቲቫሉ የሚካሄድበትን ስፍራ የመከለያ አጥር ማፍረሳቸውን አስታውቋል።

የ84 ሺህ ሕዝብ መኖሪያ በሆነችው ጊሰን ከተማ የተዘጋጀውን የባሕል ፌስቲቫል ለማወክ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኤርትራውያን ከተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ፖሊስ ገልጿል።

በቅርብ ዓመታት ጀርመን ከፍተኛ ቁጥር ላለቸው ኤርትራውያን ስደተኞች ጥገኝነት የሰጠች ሲሆን፣ ይህም በአውሮፓ ኅብረት ካሉ አፍሪካውያን ማኅብረሰቦች ኤርትራውያኑን ከቀዳሚዎቹ ተርታ አስልፏቸዋል።

በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኤርትራ መንግሥት በዜጎቹ ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጽም ይገልጻሉ።

በዚህም ምክንያት በኤርትራ ያለውን የፖለቲካ እና የእምነት ነጻነት ጭቆና እንዲሁም የጊዜ ገደብ የሌለውን አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት በመሸሽ በርካቶች ኤርትራውያን አገር ጥለው ይሰደዳሉ።