July 10, 2023 – BBC Amharic 

የቭጌኒ ፕሪጎዢን
የምስሉ መግለጫ,የቭጌኒ ፕሪጎዢን የሩሲያዋን ከተማ ሮስቶቭን ለቆ ሲወጣ

10 ሀምሌ 2023, 15:30 EAT

ከሁለት ሳምንት በፊት የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን አመጽ ከከሸፈ በኋላ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቡድኑ መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ጋር ተገናኝተው እንደነበር ክሬሚሊን አስታወቀች።

የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እንዳሉት የቫግነር ቅጥረኛ ቡድንን የሚመራው ፕሪጎዢን፣ በሞስኮ በተካሄደው ስብስባ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙ 35 ግለሰቦች መካከል አንዱ ነበር።

ከአስራ አንድ ቀናት በፊት በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ወቅትም ፕሬዝዳንት ፑቲን የዩክሬንን ኃይል እና አመጹን መገምገማቸውን ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።

በቫግነር ቅጥረኛ ቡድኑ መሪ ፕሪጎዢን የተመራው የትጥቅ አመጽ የተቀሰቀሰው እንደ አውሮፓውያኑ ሰኔ 23 ሲሆን የቆየው ለ24 ሰዓታት ብቻ ነበር።

አመጹ እና ፍጥጫው በቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አማካይነት በተደረሰው ስምምነት መሠረት የቆመ ሲሆን፣ ፕሪጎዢን ላይ የቀረበው የአገር ክህደት ክስ ተነስቶ ወደ ቤላሩስ እንዲሄድ ተፈቅዶለትም ነበር።

በቅጥረኛ ቡድኑ ቫግነር እና በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር መካከል አለመግባባቶች የነበሩ ሲሆን ፕሪጎዢን ለቡድኔ ጥይት አልቀረበለትም ሲል ሚኒስቴሩን በተደጋጋሚ ከሷል።

ይሁን እንጂ አመጹ ከከሸፈ ከአምስት ቀናት በኋላ በክሬሚሊን በተደረገው ስብሰባ ላይ ከተጋበዙ ወታደራዊ አዛዦች መካከል አንዱ እንደነበር ፔስኮቭ ተናግረዋል።

የሩሲያ መንግሥት የዜና ወኪል ኢንተርፋክስ የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭን ጠቅሶ እንደዘገበው “ፕሬዚደንት ፑቲን በጦር ግንባር ላይ ቅጥረኛ ቡድኑ የፈፀመውን ድርጊት ገምግመዋል።”

ከዚህም በተጨማሪም በሰኔ 24 የተፈጠረውን ክስተት የገመገሙ ሲሆን፣ ፑቲን የጦር አዛዦቹ የሰጡትን ገለጻ አድምጠዋል።

ስለየወደፊቱ ቅጥር እና ወደፊት በጦርነት ውስጥ ስለሚጠቀሙባቸው የተለዩ አቅጣጫዎችም አስተያየት ሰጥተዋል ብለዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ ፕሪጎዢን ቅጥረኛው ቡድን ቫግነር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በታማኝነት እንደረዷቸው ለፑቲን ነግረዋቸዋል።

የቫግነር ቡድን የግል ቅጥረኛ ወታደሮች ያሉት ሠራዊት ሲሆን፣ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያካሄደችው ባለው ጦርነት ውስጥ ከአገሪቱ መደበኛ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ሲዋጋ ቆይቷል።

የቫግነር ቡድን አመጽን ተከትሎ የተፈጠረውን ወታደራዊ ፍጥጫ ለማብቃት የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ባደረጉት የሽምግልና ጥረት አመጹ መቋረጡ ይታወሳል።

በተደረሰው ስምምነት መሠረት ፕሪጎዢን ላይ የቀረበው የአገር ክህደት ክስ ተነስቶ ወደ ቤላሩስ እንዲሄድ እንደተፈቀደለት ተነግሮ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት የቭጌኒ ፕሪጎዢን ከሩሲያ ወጥቶ ወደ አገራቸው መግባቱን ተናግረው ነበር።

ነገር ግን ፕሪጎዢን ያለበት ስፍራ ሳይታወቅ ከቆየ በኋላ የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ ዛሬ ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች ፕሪጎዢን በአገራቸው ግዛት ውስጥ ሳይሆን እዚያው ሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ እንደሚገኝ ተናግረው ነበር።

ፕሪጎዢን የቡድኑን ተዋጊዎች በመጠቀም በሩሲያ ላይ አመጽ ባካሄደበት ወቅት፣ ዩክሬን ውስጥ የነበሩ ተዋጊዎቹን በማንቀሳቀስ በደቡባዊ ሩሲያ በምትገኝ ከተማ ውስጥ ያሉ አንዳንድ የደኅንነት ማዘዣ ማዕከላትን ተቆጣጥሮ ነበር።

ከዚያም በኋላ አማጺያኑ ወደ ዋና ከተማዋ ሞስኮ ማምራት በመጀመራቸው፣ የሩሲያ መንግሥት ሞስኮን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ የደኅንነት ጥበቃውን አጠናክሮ ነበር።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም በወቅቱ ቡድኑን በአገር ክህደት የከሰሱት ቢሆንም፣ አመጹን ለማስቆም በተደረሰው ስምምነት ለቡድኑ መሪ ፕሪጎዢን የደኅንነት ዋስትና በመስጠት በቫግነር ቡድን ላይ የቀረበውን የወንጀል ክስ ውድቅ ተደርጓል።

የቡድኑ ተዋጊዎችም የሩሲያ ጦርን ለመቀላቀል ኮንትራት እንዲፈርሙ፣ ካልፈለጉ ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ወይም ወደ ቤላሩስ እንዲሄዱ አማራጭ ቀርቦላቸዋል።