July 10, 2023 – Abebe Bersamo

ከሁመራ እስከ ምንጃር አረርቲ፣ ከጃዊ እስከ ኮምቦልቻ፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ፣ የአማራ ክልል ህዝብ፣ በገጠር በሉ በከተማ፣ ትንሹ በሉ ሽማግሌው፣ ሙስሊሙ በሉ ክርስቲያኑ፣ ጎጃም በሉ ጎንደር፣ ሸዋ በሉ ወሎ፣ ሴት በሉ ወንድ፣ በሁሉም፣ በሁሉም ቦታ፣ ለመብቱ፣ ለነጻነቱ፣ ለህልውናው ድምጹን እያሰማ፣ የህዝብ ኃይል ምን ማለት እንደሆነም እያሳየ ይገኛል፡፡

ለአገር፣ ለህዝብና ለሰላም ሲል፣ በህወሃት ጊዜ ጀምሮ፣ በብልጽግና ዘመን የቀጠለው የማያባራው፣ በአማራ ላይ የሚፈጸመውን ግፍ፣ ሰቆቃ፣ ኢፍትሃዊነት፣ ሲስተማቲ አፓርታይዳዊና ናዚዛዊ ጥቃትን ለረጅም ጊዜ ታግሶ ቆይቷል፡፡ ሆኖም በተለይም የአሁኖቹ ናዚዛዊ የኦሮሙማ ገዢዎች ፣ የህዝቡን ትእግስት እንደ ፍርሃት፣ የህዝቡን ለአገር ብሎ ግፍን ተሸክሞ ለመቀጠል ትከሻዉን ማስፋቱን እንደ ደካማነት፣ ቆጥረው፣ ህዝቡን ንቀውት፣ ገደብ የለሽ፣ ዘረኛና ሰይጣናዊ ተግባራቶችን በመፈጸም፣ የአማራ ማህበረሰብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር ሆኖ ከገነባትና ካቆማት አገሩ ሊያጸዱት ተነስተውበታል፡፡ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጻዳት ናዚዛዊና ኢንተርሃይሚያዊ ስራቸውን ጀምረዋል፡፡

ከዚህም የተነሳ የግፍ ጽዋ ሞልቶ ስለፈሰሰ፣ ትእግስትም ልክ ስላለው፣ የአማራው ማህበረሰብ እምቢኝ ብሎ ተነስቷል፡፡ አምሯል፡፡ በተለይም በአማራ ክልል ነገሮች ተደበላልቀዋል፡፡ አሳዳጅ የነበሩ መሳደድ ጀምረዋል፡፡ ህዝባዊ አብዮት፣ የህዝብ ቁጣ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ነው፡፡ ሰዎቹ የተኛውን አንበሳ ቀስቅሰውታል፡፡

በአማራ ክልል የተደረጉ ሰልፎችና ተቃውሞዎች በሶስት የሚከፈሉ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ በወረዳ የብልጽግና አመራሮች ድጋፍና እውቅና የተደረጉ ሰልፎችና ተቃውሞዎች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ያለ ብልጽግና አመራሮች በፍቃድ ህዝብ ገንፍሎ ወጥቶ የተደረጉ ሰላማዊ የ እምንቢተኝነት እንቅስቃሴዎችን ሰልፎች ሲሆኑ፣ ሶስተኛው የትጥቅ ትግል ውጊያ የተደረገባቸው እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡

በወረዳ ብልጽግናዎች እውቅና የተደረጉ ሰለፎች
===========================
አቶ አደም ፋራ የፊዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዬ የነበረ ጊዜ ፣ እንዲሁም በኋላ አቶ አገኘው ተሻገር ቦታውን ሲይዝ፣ የባጀት ቀመር የመፍቀድ ስልጣን ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ሁለት ጊዜ ለወልቃያት ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ባጀት እንዲለቅ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ሆኖም የሶማሌ ብልጽግና ነኝ የሚለው የቦረናው ሰው፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ፣ አህመድ ሺዴና የኦህዴዱ የገንዝብ ሚኒስቴር ዴኤታው እዮብ ታረቀኝ፣ በቀጥታ በአብይ አህመድ ትእዛዝ፣ ህገ ወጥ በሆነ መልኩ፣ ባጀት እንዳይለቀቅ አድርገዋል፡፡ በአጭሩ አነጋገር አብይ አህመድ ፣ በኢኮኖሚ የወልቃይት፣ የራያንና የጠለምትን ህዝብ አንቆ ፣ ለማንበርከክ ፣ ከህወሃት ጋር ተባብሮ እየሰራ ነው፡፡

የአብይ አገዛዝ ከህወሃት ጋር በመሆን፣ የህዝቡን ጥያቄ ለማፈንና ለመጨፍለቅ፣ እነዚህ አካባቢዎችም መልሶ በህወሃት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ ለማድረግ እያሴረ ያለውን በመቃወም፣ ለማንም የኢትዮጵያ ወረዳዎች የሚሰጠውን፣ እንደ ዜጎች ፍትሃዊ መብታቸውም ስለሆነ፣ ለነርሱም የፌዴራል ባጀት እንዲሰጥ፣ የፖለቲካ እውቅና እንዲሰጣቸው በመጠየቅ፣ በወልቃይት ጠገዴ ካፍታ ሁመራ፣ ጠለምትና ራያ ባሉ 18 ከተሞች ህዝብ ተቃውሞ አስምቷል፡፡ በሁመራ፣ ማይካድራ፣ አደባይ፣ ባእከር፣ቃፍታ፣ ወፍ አርግፍ (አዲረመጽ) ፣ አምባ ብርቱካን፣ ዳንሻ፣ ማክሰኞ ገበያ(ከተማ ንጉስ)፣ ቤትሞሎ፣ ማይጠምሪ፣ ዋልድባ፣ ዲማ፣ ፍየል ውሃ፣ ኮረም፣ ዓላማጣና ዋጃ፡፡

በወልቃይት፣ ራያና ጠለምት የተደረጉ ተቃውሞዎች፣ ከህዝብ ወገን በሆኑ በወረዳዎቹ የብልጽግና አመራሮች ድጋፋን እውቅና የተደረጉ ተቃውሞዎች ስለነበሩ፣ ምንም እንኳን ኦህዴዶች በፋና፣ ኢቢሲ፣ ዋልታ በመሳሰሉ የመንግስት ሜዲያዎች፣ ሰልፎችን በተመለከተ ምንም አይነት ሽፋን እንዳይሰጥ ቢያግዱም፣ የአማራ ክልል መንግስት ሜዲያ የሆነው አሚኮ ሰላማዊ ሰልፎችን በስፋት ዘግቧል፡፡

ሰላማዊ እምቢተኝነት ዘመቻዎች
===================
በብልጽግና አመራሮች እውቅናና ፍቃድ ሳይሰጥ፣ ህዝብ ገንፍሎ በመውጣት ተቃውሞ የተደረጋቸው አካባቢዎች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ህዝቡ በእምቢተኝነት ምሬቱን ቁጣውን የገለጸባቸው ፣ ከተሞች ብዛት ቢያንስ ስድሳ የሚደርስ ነው፡፡

ህዝቡ “ብልጽግና ይውደም፡፡ አብይ አህመድ ከስልጣኑ ይልቀቅ” በሚል አራት ኪሎ እየገዛ ላለው ለተረኛው፣ ዘረኛውና ናዚዛዊው ብልጽግና አገዛዛ ያለውን ምሬት፣ ጥላቻና፣ ተቃውሞ በአደባባይ በመውጣት፣ መንገዶች በመዝጋት አሰመቷል፡፡ እያሰማም ነው፡፡

በጎንደር ክፍለ ሃገር፣ መተማ፣ ደባርቅ፣ ዳባት፣ አምባ ጊዮርጊስ፣ አዲስ ዘመን፣ ወረታ፣ አብድራፊ፣ኢጀሬ/ጃኖራ፣ ጎንደር ከተማና እብናት፣ በወሎ ክፍለ ሃገር ሰቆጣ፣ ላሊበላ፣ ቆቦ፣ ወልዲያ፣ ሮቢት፣ መርሳ፣ ኡርጌሳ፤ መካነ ሰላም፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ሙጃ፣ ተኩለሽ፣ ጎብዬ፣ ወለግጤና፣ አጅባር(አማራ ሳይንት) እና አምባሰል፣ በሸዋ ክፍለ ሃገር ፣ ደብረ ሲና፣ራሳ፣ ሸዋ ሮቢት፣ አጣዬ፣ ማጀቴ፣ አንጾቂያ፣ ገምዛ፣ ዓለም ከተማ፣ ሚዳ፣ ጀማ፣ አረርቲ እና ደብረ ብርሃን፣ በጎጃም ክፍለ ሃገር፣ ባህር ዳር፣ መራዊ፣ ዳንግላ፣ እንጀበራ፣ ቡሬ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ጂጋ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሉማሜ፣ደጀን፣ደምበጫ፣አማኑኤል፣ ደብረ ኤሊያስ፣ ቢቸና፣ ደብረ ወርቅ፣ ግንደ ወይን፣ መርጦ ለማሪያም፣ ሞጣ፣ ፈረስ ሜዳ፣ ቋሪት፣ ፍልቅልቅና ጃዊ ነው ህዝብ ለአገዛዙ እምቢኝ እያለ ያለው፡፡

የትጥቅ ትግል የተደረገባቸው ወይም እየተደረገባቸው ያሉ
=================================
ከላይ ከተዘረዘሩት ከስድሳ በላይ ከሚሆኑ ከተሞች፣ ቢያንስ በ39 ከተማቾና የከተሞቹ ገጠራማ አካባቢዎች ፣ የአብይ አገዛዝ የአማራን ማህበረሰብ ትጥቅ አስፈታለሁ፣ አንገት አስደፋለሁ በሚል እብሪትና ጥጋብ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት፣ ከፍተኛ ወታደራዊ ትንቅንቆችና ውጊያዎች ተደርገዋል፣ እየተደረጉም ነው፡፡ አገዛዙ እያከታተለ እጅግ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት በመላክ፣ ከባባድ መሳሪያዎችን ሳይቀር በመጠቀም፣ ያለ የሌላ ኃይሉን በመጠቀም ላይ ይገኛል፡፡

ቢያንስ በጎንደር ክፍለ ሃገር በአብድራፊ፣ኢጀሬ/ጃኖራ፣ ጎንደር ከተማ ፣ አዘዞ፣ ማክሰኚትና እብናት፣ በወሎ ክፍለ ሃገር በሙጃ፣ተኩለሽ፣ ጎብዬ፣ወለግጤና፣ አጅባር(አማራ ሳይንት) ፣ መካነ ሰላም እና አምባሰል፣ በሸዋ ክፍለ ሃገር ደብረ ሲና፣ ራሳ፣ ሸዋ ሮቢት፣ አጣዬ፣ ማጀቴ፣ አንጾቂያ፣ ገምዛ፣ ዓለም ከተማ፣ ሚዳና ጀማ፣ በጎጃም ክፍለ ሃገር ደምበጫ፣አማኑኤል፣ ደብረ ኤሊያስ፣ ቢቸና፣ ደብረ ወርቅ፣ ግንደ ወይን፣ መርጦ ለማሪያም፣ ሞጣ፣ ፈረስ ሜዳ፣ ቋሪትና ፍልቅልቅ ከመለስተኛ እስከ ከፍተኛ ውጊያዎች ተደርገዋል፡፡

በሶስት ሳምንት ህወሃትን አሸንፎ መቀሌን መቆጣጠር የቻለው የአብይ የኦህዴድ ጦር፣ ከሁለት ወር በላይ በብዙ ግንባሮች፣ በጀነራሎች ሳይቀር የተመራ ጦርነቶች አድርጎ፣ በሁሉም ቦታ ማለት ይቻላል፣ ከፍተኛ ሽንፈትን ነው ያስተናገደው፡፡ “የአማራ ኃይሎችን ትጥቅ አይደለም ሱሪ እናስፈታለን ፣ ልካቸውን እናስገባዋቸለን” ያሉት እነ አብይ አህመድ፣ እነርሱ ራሳቸው ሱሪያቸው እንዲፈቱ እየተደረገ ነው፡፡ ልካቸውን እያገኙ ነው፡፡ ህዝብን ማሸነፍ እንደማይቻል ሲነገራቸው አልሰማም ብለው፣ ከፍተኛ ውድቀት ውስጥ እየገቡ ነው፡፡

አብይ አህመድና የኦህዴድ ጎዶቹ አንድ ምርጫ ብቻ ነው የሚኖራቸው፡፡ በሰላም ከስልጣናቸው መልቀቅና ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ማድረግ፡፡ የአማራ ማህበረሰብ ጥያቄው እኩልነት ነው፡፡ በአገሩ በሰላም መኖር ነው፡፡ ትግሬ፣ ኦሮሞ አማራ እየተባክለ የተዘረጋው ዘረኝነትና የዘር መከፋፈል እንዲቆም ነው፡፡ አማራው ልዩ ጥቅም ይሰጠኝ፣ አማራ የበላይ ይሁን እያለ አይደለም፡፡ ዜጎች ዘራቸው፣ ጎሳቸው፣ ኃይማኖታቸው ሳይታይ በማንኛው የአገሪቷ ግዛት የመስራት፣ ሃብት የማፍራት፣ የመኖር፣ የመመረጥ፣ የመመረጥ መብታቸው ይከበር ነው የሚለው፡፡

አማራው በአዲስ አበባ ፣ በአራት ኪሎ ጨፍላቂ፣ ናዚዛዊ አገዛዝን በጭራሽ አይታገስም፡፡ አዲስ አበባ መሽገው ህዝብን የሚያሸብሩ የጥላቻ የኦሮሙማ ኃይሎች ፣ እነ አብይ አህመድ፣ አልሰማ ካሉ፣ ካሉበት ቦታ ተንጠልጥለው ይወጣሉ፡፡ አሁንም ከህዝብ ጠላቶች ጋር ሆነው ህዝብን እየበደሉ ያሉ፣ የአማራ ብልጽግናዎች፣ እንደ ብርሃኑ ነጋ፣ በለጠ ሞላና ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ያሉ፣ “አብይ አህመድ አስገድዶን ነው፣ አታሎን ነው ፣ ለአገር ብለን ጥሩ የሰራን መስሎን ነው” ወዘተ የሚል ምክንያት ቢዘርዝሩ የሚሰማቸው አይኖርም፡፡ አሁን ከገዳዮችና አስገዳዮች ፣ ከናዚዎች ግፈኞች ጎን በመቆማቸው እነርሱን ዋጋቸውን ያገኛሉ፡፡