(አዲስ ማለዳ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የታጠቁ ኃይሎች በሕዝቡ በጀት እየተቀለቡ፤ ተመልሰው ሕዝቡ ላይ የስነልቦና ጫና፣ ዛቻ፣ ማስፋራሪያ፣ እስራት፣ ድብደባ እና ግድያ እየፈጸሙ ይገኛሉ ሲል ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ቦዴፓ/ ገልጿል፡፡
ፓርቲው ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ፤ በአጠቃላይ ክልሉ በተለይም ደግሞ መተከል ዞን ከቆየበት የሰላም ችግር እየወጣና ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡
ሆኖም የክልሉ መንግሥት ራሱን “የጉህዴን ታጣቂ” ብሎ ከሚጠራ ቡድን ጋር የሰላም ስምምነት ከተፈራረመ በኃላ በርካታ የቡድኑ ታጣቂዎች እጃቸውን ለመንግሥት ሰጠዋል ቢባልም፤ እስካሁን ትጥቅ አለመፍታታቸው ተገቢ አለመሆኑን ደጋግሞ መግለጹን ያስታወሰው ፓርቲው፤ “ታጣቂ ቡድኑ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ እንዳልሆነና የክልሉ መንግሥትም ትጥቅ ለማስፈታት ቁርጠኛ እንዳልሆነ ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡” ብሏል፡፡
“የታጣቂ ቡድኑ አባላት የበደሉትን ሕዝብ ይቅረታ ጠይቀውና ክሰው ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ በመንግስት የተሰጣቸውን ወርቃማ እድል ወደጎን በመተው በሕዝቡ በጀት እየተቀለቡ፤ ተመልሰው ሕዝቡ ላይ የስነልቦና ጫና፣ ዛቻ፣ ማስፋራሪያ፣ እስራት፣ ድብደባ እና ግድያ እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡” ሲልም ገልጿል፡፡
የቡድኑ አባላት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ግልገል በለስ ከተማ፤ ሰኔ 30/2015 በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ንፁኃን ዜጎች መገደላቸውና በርካቶች መቁሰላቸው በእጅጉ እንዳሳዘነውም በመግለጽ፤ “ድርጊቱ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለለው አስነዋሪና አሳፋሪ ነው፡፡” ሲል አውግዞታል፡፡
በንፁሀን ዜጎች ላይ ይህን የመሰለ ወንጀል የፈጸሙ አካላት በአፋጣኝ ለሕግ እንዲቀርቡም ፓርቲው ጠይቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ የታጣቂ ቡድን አባላት በመተከል እና ከማሽ ዞኖች ትጥቅ ሳይፈቱ በከተሞችና በገጠር ቀበሌዎች በመንግሥት ሎጀስትክስ እየተንቀሳቀሱ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ስጋት እየፈጠሩ እንደሚገኙ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
በዚህም መሰረት፤ “የመተከልን ሕዝብ ማህበራዊ እረፍት በመንሳት ቀጠናውን የጦርነት ማዕከል ለማድረግ የሚሰሩ አካላት ከድርጊታቸው እንድቆጠቡ፤ አርሶ አደሩን ለማስራብ በማለም የእርሻና የምርት ወቅት በመጠበቅ የሚደረግ አመራር ፈጠር ግድያ በእጅጉ እናወግዛለን” ሲል ፓርቲው ገልጿል፡፡
እንዲሁም፤ የጉህዴን ኃይሎች ትጥቅ ሳይፈቱ ማህበረሰቡ ውስጥ የሚያደረጉት እንቅስቃሴ በተለይም የመንግሥት የፀጥታ አካላትን ሚና ተክተው የሚያደረጉት እንቅስቀሴ በአስቸኳይ እንዲቆምና ትጥቅ በአስቸኳይ እንድፈቱ አሳስቧል፡፡
ፓርቲው አክሎም፤ ሰሞኑን በግልገል በለስ ከተማ በዜጎች ላይ የተፈፀመውን ዘግናኝ ግድያና ከድርጊቱ ጀርባ ያሉ አካላትን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የክልሉና የፌደራል ፖሊስ በማጣራት አጥፊዎችን ለሕግ እንዲያቀርቡና ለህዝቡ ይፋ እንዲያደረጉ ጠይቋል፡፡
የክልሉ መንግሥት በሰላም ውስጥ ልማትን ማሰብና መፈጸም የማይችሉ፣ በግጭት ውስጥ በሕዝብ ደም በስልጣን ላይ ለመኖር የሚፈልጉ ሀሳብና ውጤት አልባ ጊዜ ያለፈባቸው አመራሮችን በአስቸኳይ በማጥራት እንዲያስተካክልም ፓርቲው በመግለጫው አሳስቧል፡፡