July 10, 2023

በትግራይ “አባቶች” ሁኔታ ግራ የተጋባችሁ ካላችሁ!

የሆነው እንዲህ ነው፦

ትህነግ “ኮሚኒስት ነኝ” ብሎ ነው ጫካ የገባው። ኮሚኒስቶች ደግሞ ኃይማኖትን “የድሆች ማደንዘዣ” ነው የሚሉት። ፀረ እምነት ናቸው። ትህነግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን በጠላትነት ፈርጆ ነው ጫካ የገባው። ይሁንና የራሱን ቤተ ክርስትያን ግን የፈጠረው ትግል በገባ በጥቂት አመታት ውስጥ ነው። ይህ መረጃ የመጀመርያው የትህነግ ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ በመፅሐፉ ያጋለጠው ነው።

1) በ1971 ትህነግ በየወረዳው የትግራይ ቄሶችን መለመለ። መልማዩ የጥላቻ አባት የሚባለውና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስነመለኮት የተማረው የትህነግ ታጋይ ገብረኪዳን ደስታ ነው። ሰውየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትናን የአማራ ነው ብሎ ፈርጆ፣ አማርኛ የጠላት ቋንቋ ስለሆነ በትግርኛ መስበክ አለብን ብሎ ንቅናቄ ጀመረ። የራሳችን ቤተ ክርስቲያን እንመሰርታለን ብሎ ሰራ። በየወረዳው ኮንፈረንስ አደረገ። የትህነግ አስተሳረብ ያጠመቋቸውን ቄሶች አደራጀ።

2) ስብሃት ነጋ የትህነግ ታጋዮችን መልምሎ ደብረዳሞና ሌሎች ገዳሞች መነኩሴ አስመስሎ አስገባ። እነዛ የትህነግ ታጋይ ሆነው መነኩሴ መስለው ገዳም የገቡት ለአሁኑ የኃይማኖት ካባ ለተከጀቦነ ንቅናቄ መሰረት ናቸው።

3) በ1978/9 ዓ/ም አካባቢ ትህነግ የገብረኪዳን ደስታን ምልምሎች አደራጅቶ “ብሔራዊ የትግራይ ቄሶች ኮንፈረንስ” አደረገ። ትግራይ እንደ አገር የራሷን ሲኖዶስ ማወጅ አለባት አሉ። አወጁ።

4) ትህነግ ይዟቸው በነበሩት የትግራይ አካባቢ ልክ በቅርቡ ኦሮሚያ እየተደረገ እንዳለው የትህነግ “ቄሶች” ቤተ ክርስቲያንን ሲኖዶስ ከመደባቸው አባቶች ቀሙ። ትግራይ ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት ከፈሏት። ደርግ በያዘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ ትህነግ በያዛቸው የትግራይ አካባቢዎች የትግራይ ቤተ ክርስቲያን ተባለ። የትህነግ/ህወሓት ቤተ ክርስቲያን ማለት ነው። ደርግ መቀሌን ሲለቅ መቀሌ የነበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች ወደ ደሴ እንዲሸሹ ተደገደዱ። የትህነግ ቄሶች ሙሉ በሙሉ የትግራይ ቤተ ክህነትን መመስራቸውን ይፋ አደረገ። ይህ ጉዳይ ትህነግ አዲስ አበባ እስኪገባ ቆየ።

5) ትህነግ ስልጣን ሲይዝ የትግራይ አገርነትን እንደተወው፣ የትህነግ ቄሶችም የተገንጣይ አላማቸውን ተውት። 2010 በኋላ ትህነግ ወደ መቀሌ ሲመለስ የኃይማኖት ፕሮጀክቱን እንደገና ጀመረው። በጦርነቱ ወቅት ሲያደርጉ የነበረው የሚታወቅ ነው። “አገረ ትግራይ” እያሉ ቀድሰዋል። ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ትህነግ ብሶት ማሰሚያ፣ የመገንጠል ጥያቄውን እንዳልተውት ማስታወሻ አድርጓቸዋል። ባለፈው የኢትዮጵያ መከላከያ ትግራይን ጥሎ ሲወጣ ፀጋዬ በርሄ “የትህነግን ቄሶች” እንዲመራ ተደርጎ በየአካባቢው ተዘዋውሮ “አገረ ትግራይ እያላችሁ ቀድሱ” ብሎ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የአክሱም አባቶች ብቻ “እናንተ አገረ ትግራይ ብላችሁ ካወጃችሁ እኛም እንላለን። እናንተ ሳታውጁ እኛ አገረ ትግራይ አንልም።” ብለው ተቃውመዋል። በበርካታ ቦታዎች አሁን ትግራይ አገር ተደርጋ “አገረ ትግራይ” እየተባለ ይቀደሳል። ጠርናፊው “አለቃ” ፀጋዬ በርሄ ነው።

6) የትግራይ ጳጳሳት በጦርነቱ ወቅት እንኳን ደሞዝ አልተቋረጠባቸውም። የባንክ አገልግሎት ስላልነበር ማውጣት ባይችሉም ቤተ ክርስቲያን ግን ከፍላቸዋለች። አሁንም ደሞዝ ይላክላቸዋል። ደሞዛቸውን እየወሰዱ ነው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር አንቀጥልም የሚሉት። ትህነግ በጦርነቱ ወቅት “ጦርነቱን እቀጥላለሁ። በጀት ግን ላኩ።” እንዳለው መሆኑ ነው።

ከስር መሰረቱ ካየነው የትግራይ አባቶች ኩርፊያ ኃይማኖታዊ አይደለም። ባለፈው አመት ጀምረው በጠላት ቋንቋ አማርኛ አንሰብክም ብለዋል። ይህ ተጀምሮ የነበረው በ1971 ነው። አላማው ፖለቲካዊ ነው። የኮሚኒስት “ቄሶች” ፕሮጀክት ነው የቀጠለው። የጥላቻ አባቱ ገብረኪዳንና ስብሃት ነጋን ፕሮጀክት ነው አፈሩን አራግፈው ያመጡት። አሁን ፀጋዬ በርሄ ነው የሚመራው። ገብረኪዳን ደስታን “መምህር” ይሉት የነበረው ኃይማኖት ማዕረግ ሰጥተውት ነው። ፀጋዬን ደግሞ አለቃ ፀጋዬ” ይሉታል። ሁለቱም የኃይማኖት ትምህርት አላቸው። ርዕዮት አለማቸውን ቢጠየቁ ግን ድሮ ኮሚኒስም፤ በቅርብ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው የሚሉት። ዞሮ ዞሮ ፀረ እምነት ናቸው። ገብረኪዳንም ሆነ ፀጋዬ ኃይማኖተኞች አይደሉም። አላማቸው የትህነግ አላማ ነው። ፀረ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ነው። በኃይማኖት ስም ከወደ ትግራይ የሚጎሰመው ልዩነት መነሻው ተገንጣይ ብሔርተኝነት እንጅ ኃይማኖት አይደለም። ለበለጠ የአረጋዊ በርሄን መፅሐፍ ማንበብ ይቻላል።

መንበረ ከሳቴ ወዘተ የሚሉት የትህነግን ማንፌስቶ አላማቸው አድርገው ጫካ የገቡ፣ ጫካ የገቡት በፀረ ኦርቶዶክስነት ያደራጇቸው፣ እንጅ ኃይማኖተኞች አይደሉም። መነሻውም ትህነግ ከተመሰረተ ሶስትና አራት አመት ውስጥ እንጅ ባለፈው ሁለት አመት ጦርነት ምክንያት የተጀመረ አይደለም። ጦርነቱ ሰበብ ነው። ትህነግ ስልጣን ሳይዝ ጫካ ሆነው የራሳችን ሲኖዶስ አዋቅረናል ብለው አውጀው ነበር። አሁን የኦሮሚያው እንደማያደርገው የትህነግ ታጣቂን አስከትለው ቤተ ክርስቲያን ነጥቀው ገብተው ነበር። የኦሮሚያው “መልካም ተሞክሮ” ብሎ የወሰደው ከአርባ አመት በፊት ከነበረው ነው። ትህነግም ድሮ መታገያ ያደረገውን ነው አሁን እንደ አዲስ የጀመረው።

(ከወር በፊት ከፃፍኩት የተወሰደ ነው) ጌታቸው ሽፈራው