አቡነ ማቲያስ እና አቶ ጌታቸው ረዳ
የምስሉ መግለጫ,አቡነ ማቲያስ እና አቶ ጌታቸው ረዳ

10 ሀምሌ 2023, 18:11 EAT

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያትክ የተመራው ቡድን መቀለ ውስጥ ባካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ የትግራይ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባቶች ሳይገኙ መቅረታቸው ተነገረ።

ለሁለት ዓመት በተካሄደው ጦርነት ምክንያት በቤተክርስቲያኑ አባቶች መካከል ሻክሮ የቆየውን ግንኙነት ለማሻሻል በፓትሪያርኩ የሚመሩ አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ሰኞ ሐምሌ 03/2015 ዓ.ም. ወደ መቀለ ማቅናታቸው ይታወቃል።

አባቶቹ ረፋድ ላይ መቀለ አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን ከጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ጋርም ተገናኝተዋል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጦርነቱ ወቅት የሚጠበቅበትን አላደረገም በሚል በተደጋጋሚ ወቀሳ ሲሰነዝሩ የነበሩት የትግራይ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶች በስፍራው እንዳልተገኙ ተገልጿል።

የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ጦርነቱን በማውገዝ እና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከጎናችን አልቆሙም ያሉት የትግራይ ቤተክርስቲያን አባቶች ከማዕከላዊው ሲኖዶስ በመነጠል የራሳቸውን ቤተክህነት ማቋቋማቸው ይታወቃል።

ዛሬ ወደ መቀለ ያመራው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የተመራው የልዑካን ቡድን፣ በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተፈጠረውን ቅሬታ ለማሻር ንግግር መጀመር እና በችግር ላይ ላሉ የክልሉ ነዋሪዎች ድጋፍ ማድረግ አላማው እንደሆነ በስፋት ሲነገር ቆይቷል።

በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ምዕመናን እና የቤተክርስቲያኗ አባቶች የሚጠብቁባትን ባለማድረጓ ቅዱስ ሲኖዶስ ባለፈው ሳምንት ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን፣ ያሉ ሁኔታዎችን በተመለከተም ለመነጋገር ወደ ትግራይ አባቶች እንደሚጓዙ መገለጹ ይታወሳል።

ከዚህ በፊት በነበረው ልምድ እና በተያዘው መረሃ ግብር መሠረት የቤተክርስቲያኗ አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች በክልሉ ባለሥልጣናት እና በሃይማኖት አባቶች አቀባበል እንደሚደረግላቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ የትግራይ ሃይማኖት አባቶች እንዳልነበሩ ተዘግቧል።

ከዚያም በኋላ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት አቡነ ማቲያስ የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ በጦርነት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲደርስ የሰጠውን የሃያ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ለአቶ ጌታቸው ረዳ አስረክበዋል።

በሥነ ሥርዓቱ አቡነ ማቲያስ “በሕዝቡ ላይ የደረሰው መከራ ከባድ እና ታይቶ የማይታወቅ ነው” በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ ይቅርታ መጠየቁን አስታውሰው፣ ድጋፉም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተወሰነ መሆኑን በመግለጽ “ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ተቀራርቦ መወያየት እና መነጋገር ይኖርብናል” ብለዋል።

በዚህ ወቅትም አቶ ጌታቸው ረዳ ድጋፉ ዘግይቶ የተሰጠ ቢሆንም ጥረቱን በአዎንታዊ መልኩ እንደሚመለከቱት ገልጸው፣ አስተዳደራቸው በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የማይገባ መሆኑን በመጥቀስ “በሕዝቦች መካከል ያለ ቅራኔ እና አለመግባባት በውይይት እንዲፈታ ቅዱስ ሲኖዶሱ የጀመረው ጥረት ተገቢ” መሆኑን መናገራቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

አቶ ጌታቸው በተጨማሪም በተፈጠረው ጦርነት ወቅት ቤተክርስቲያን ከአፈናቃዮች ጋር ቁማለች የሚል ቅሬታ እንዳለ በመግለጽ “ቅሬታው የሕዝብ በመሆኑ በችግሮቹ ዙሪያ መተማመን እና መግባባት እንደሚያስፈልግ” ተናግረዋል።

በፓትርያርኩ በኩል ከቤተክርስቲያኗ የተሰጠው የ20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለአቶ ጌታቸው በተሰጠበት ሥነ ሥርዓት ላይም የክልሉ የሃይማኖት አባቶች ያልተገኙ ሲሆን፣ የልዑካን ቡድኑ በመቀለ ከተማ የሚገኙ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን ጎብኝቷል።

ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት በአገሪቱ በተለይም በትግራይ ክልል ውስጥ ከባድ ውድመት ያስከተለ ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንደጠፋበት ይነገራል።

ጦርነቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከልም ቅሬታን በመፍጠር የክፍፍል በርን ከፍቷል።

ባለፈው ሳምንት የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተክርስቲያኗ ጦርነቱ እንዲቆም በወቅቱ ጥሪ ባለማቅረቧ፣ በጦርነቱ ወቅት በክልሉ የሚገኙ የቤተክርስቲያኗ አባቶችን እና የትግራይን ሕዝብ በአካል ባለመጠየቋ እንዲሁም ባለማጽናናቷ ይቅርታ ጠይቃለች።

የሽረ እንደ ሥላሴ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እና የመንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑትን ንቡረእድ ተስፋይ ተወልደ “ይቅርታ ጥሩ ጅምር ቢሆነም፣ በቂ ግን አይደለም” በማለት ተናግረዋል።

ነገር ግን እስካሁን የክልሉ ቤተክህነት አባላት በተናጠል በይቅርታው ዙሪያ ከሰጡት አስተያየት ውጪ፣ በይፋ ከአባቶቹ የተሰጠ ምላሽ የለም።